Connect with us

Art and Culture

የሹማምንቶቻችን ዐብይ ችግር…ለግል ክብርና ዝና መጨነቅ! | በጫሊ በላይነህ

Published

on

የሹማምንቶቻችን ዐብይ ችግር…ለግል ክብርና ዝና መጨነቅ!

የሹማምንቶቻችን ዐብይ ችግር…ለግል ክብርና ዝና መጨነቅ! | በጫሊ በላይነህ

ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በቅርብ የካቢኔ ሹመት ሲሰጡ እንደዋዛ ጣል ያደረጉዋት ንግግር ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡

ጠ/ሚኒስትሩ ሚኒስትሮቻቸውን ራሳቸውን ዝቅ አድርገው እንዲሰሩ፣ ማልደው እንዲገቡ፣ ሊፍት ሲጠቀሙ ሠራተኞችን እንዳያባርሩ የመከሩበት ነው፡፡ ነገሩ ለሚገባው ጥሩ ቁንጥጫ ነው፡፡ አዎ!.. በተሾሙ ማግስት ራሳቸውን ቆልለው እንኳንስ ሊፍት ላይ ቀርቶ ባለፉ ባገደሙ ቁጥር በአጃቢዎቻቸው ወከባ የሚፈጥሩ ሚኒስትሮች ይህ አባባል ጥሩ ልምጭ ነው፡፡

ጥቂት የማይባሉ ሚኒስትሮች በራቸውን ለባለጉዳይ፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ለጋዜጠኞች ጭምር ዘግተው ምን ሲሰሩ እንደሚውሉ ግራ የሚገባ ነው፡፡ አንድ ሠራተኛ ሚኒስትሩን፣ ዋና ዳሬክተሩን… ለግልም ይሁን ለስራ ጉዳይ ለማነጋገር ቢፈልግ ከጸሐፊ የሚቀርብለት የመጀመሪያ ጥያቄ “ቀጠሮ አለህ ወይ” የሚል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ቀጠሮ ከሌለህ ጥፋ ዓይነት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ሠራተኞችና ሙያተኞች የቱንም ያህል ውሳኔ የሚፈልግ ጉዳይ ቢኖር ወደሚኒስትሩ፣ ዋና ዳይሬክተር፣ ኮምሽነር… ቢሮ ሄዶ ደጅ መጥናትን ባለመፈለግ ሥራን ለመወዘፍ ይገደዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ቤቱ የስራ መሆኑ ቀርቶ የወሬና የሐሜት ቤት ይሆናል፡፡

በሊደርሺፕ ቲዎሪ አንድ የሥራ መሪ የብቃት መለኪያው ሰርቶ ማሰራት መቻሉ ነው፡፡ ራዕይ ያለው፣ ለሠራተኞቹና ለደንበኞች ወይንም ለተገልጋዮች ምቾትና ደህንነት ሌት ተቀን የሚሰራ ነው፡፡ ብቃት ያለው መሪ ወርዶ፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚሰራ እንጂ ላይ ቁጭ ብሎ የሚኮፈስ አይደለም፡፡

አንድ በሥራ አጋጣሚ በቅርብ የማውቀውን አብነት ልጥቀስ፡፡ ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በሥሩ 26 ኩባንያዎች ያሉት የግል ኩባንያ ነው፡፡ ሲኢኦው ዶ/ር አረጋ ይርዳው ለየት ያለና ሊጠቀስ የሚችል የሊደርሺፕ ኳሊቲ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በየዕለቱ ወደሥራ ገበታቸው ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት በፊት ይገባሉ፡፡ ሠራተኞቻቸውን ሲርቪሶች ይዘው ሲገቡ ደጅ ቆመው ይቀበላሉ፤ “እንዴት አደራችሁ” ብለው በአባታዊ ፈገግታ ወደቢሮአቸው ይሸኛሉ፡፡

በአንዳች የሥራ ምክንያት ካልተመቻቸው በስተቀር ሥራ ጨርሰው ሲወጡ በተመሳሳይ ሁኔታ ደጅ ወጥተው ቆመው ሠራተኞቻቸው በሰርቪስ ካልሸኙ በስተቀር ቀድመው ግቢውን አይለቁም፡፡ በየዕለቱ ትንሽ ፋታ ባገኙበት ደቂቃዎች ተጠቅመው በእግር ረጅሙን ግቢ እየተዘዋወሩ በየኩባንያዎቹ ሠራተኞቻቸውን ያናግራሉ፣ ስለሥራ፣ ስለግልህይወት ሳይቀር ይጠይቃሉ፡፡ ችግር ካለ በአስቸኳይ እንዲፈታ ያደርጋሉ፡፡ ቢሮአቸው ሁሌም ክፍት ነው፡፡ ማንኛውም ሠራተኛ እና ባለሙያ፣ ባለጉዳይ ያለአንዳች ቀጠሮና መንገላታት እሳቸውን ማግኘትና ማነጋገር ይችላል፡፡ ሌላው ቀርቶ በቅጥር ግቢ ውስጥም ቢሆን መንገድ ላይ ከሠራተኞቻቸውና ባለጉዳዮች ጋር መነጋገርና ችግሮችን በፍጥነት መቅረፍ የዕለት ተዕለት ሥራቸው አካል ነው፡፡

ሴት ሠራተኞች እንዳይቸገሩ ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው የሚያቆዩበት፣ በየሰዓቱም ልጆቻቸውን የሚያጠቡበት በባለሙያና ቁሳቁስ የተደራጀ ማዕከል አዘጋጅተዋል፡፡ይህ ማዕከል ለመንግሥት ተቋማትም በአርአያነቱ እንደሞዴል የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ ሠራተኞችን ከሥራ ሰዓት ውጭ አካላቸውንና እዕምሮአቸውን እንዲያነቃቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ገንብተዋል፡፡ ዓመታዊ የስፖርት መርሀግብር ዘርግተዋል፡፡

ዶ/ር አረጋ ሶፍትዌር ያለሀርድ ዌር ሊሰራ እንደማይችል ሁሉ ሠራተኛውና ማኔጅመንቱ ካልተቀናጀ ውጤታማ መሆን እንደማይቻል ሁሌም ይናገራሉ፡፡ እየተገበሩ ያሉትም የሚናገሩትን ነው፡፡

ወደመንግሥት ተቋሞቻችን ስንመጣ እንዲህ ዓይነት የሥራ መሪዎች በብዛት ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ ዝቅ ብሎ ሰርቶ ማሰራት የራስ ክብርን እንደመንካት የሚያስቆጥር ደካማ የሥራ ባህል ተገንብቷል፡፡ ይህን ደካማ የሥራ ባህል ለመገርሰስ ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ ያላቸው ብርቱ ፍላጎት በቀላሉ የሚሳካ አይመስልም፡፡ ምክንያቱም ችግሩ በአደገኛ ሁኔታ ሥር የሰደደ ነውና፡፡

ሌላ አብነት እናክል፡፡ መንግሥትን ከፍተኛ ወጪ ያስወጣሉ በሚል ቪ8 መኪኖችን ባለሥልጣናት ከተማ ውስጥ እንዳይጠቀሙ የሚከለክለው ደንብ በቅርቡ አውጥቷል፡፡ ይህ ደንብ የወጣው ተሽከርካሪዎቹ ለነዳጅና ለዘይት ግዥ ከፍተኛ ወጪ ስለሚያስወጡ ወጪን ለመቀነስ ታስቦ ነው፡፡

በተጨማሪም መንግሥት አንድ ቪ 8 መኪናን ለመግዛት አምስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ያደርግ የነበረውንም አነስተኛና ነዳጅ ቆጣቢ የሆኑ ተሽከርካሪዎችን በመግዛት የመንግሥትን ወጪ መቆጠብ እንደሚቻል ታሳቢ ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህ እሳቤ መሠረት 400 ባለ ሦስት ሲሊንደር ተሽከርካሪዎች እስከ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ እንዲገዙ ተደርጎ ተሽከርካሪዎቹን ለተቋማት የማስተላለፍ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የወጣው ደንብ ሚኒስቴር መ/ቤቶቹ ለዕለት ሥራቸውን ነዳጅ ቆጣቢ ተሽከርካሪዎቹ ብቻ በመጠቀም፤ ለከተማ የተከለከሉት ቪ8፣ ጂ ናይን ወይም ባለ 4 ሲሊንደር ፕራዶ፣ ፓጃሮ እና መሰል ተሽከርካሪዎች ለመስክ ሥራ ብቻ እንዲውሉ የሚደነግግ ነበር፡፡

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች የሚጠቁሙት ይህ ደንብ በአብዛኞቹ መ/ቤቶች እየተተገበረ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ከቪ8 ተሽከርካሪ መውረድ ለሹማምንቶቻችን ክብርን ዝቅ የማድረግ ያህል እየተቆጠረ መምጣቱን ነው፡፡

በአጭሩ ሕዝብን ከማገልገል ይልቅ ለራስ ክብር መጨነቅ ክፉ ልማድ እየሆነ ነው፡፡ ጠ/ሚ ዐብይ ይህን ስር የሰደደ የአስፈጻሚ አካላት በሽታ በምን ያክመው ይሆን? ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡

እናም ጠ/ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እንዲህ ዓይነቱን ተኮፋሽና ለግል ክብርና ዝና ሟች የሆነ አመራር አዝለው የት ድረስ ሊጓዙ ይችላሉ የሚለው ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close