Connect with us

Ethiopia

ኢትዮጵያ፡ የባሩድ በርሜል! | በማዕረግ ጌታቸው

Published

on

ኢትዮጵያ፡ የባሩድ በርሜል! | በማዕረግ ጌታቸው

ኢትዮጵያ፡ የባሩድ በርሜል! | ማዕረግ ጌታቸው

ኦስትሪያዊው ጸሀፊ ሮማን ፕሮቸስካ በ1927 ዓ.ም ለንባብ ባበቃው Abyssinia; The powder Barrel መጽሐፉ ኢትዮጵያን የባሩድ በርሜል ሲል ይገልጻታል፡፡ በጣሊያን ወረራ ዘመን ዋዜማ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለተመለከተ ሰው በርግጥም በፕሮቸስካ አገላለጽ ይሳማማል፡፡ በየቦታው የጦር መሳሪያ ንግድ ጡፏል፡፡

ጣሊያን ወልወልን ሳትቆጣጠር የሸገር ነዋሪዎች መሀል አዲስ አበባን ምሽግ እየቆፈሩ ትልቅ የጦር አውድማ አድርገዋታል፡፡ የውጭ ዜጋ የሆነ ሁሉ ጠላት ተደርጎ በየቦታው በደቦ ይደበደባል፡፡ በዚህ ድባብ ውስጥ ሁኖ የአድኑኝ ኑዛዜውን ለዓለም ህዝብ ለማድረስ የተጣጣረው ፕሮቸስካ ኢትዮጵያን የጥይት በርሜል ሁናለች ይለናል፡፡

በ Abyssinia; The powder Barrel ውስጥ የተከተበው ሀሳብ የዛሬም ዘመን ዕውነታችን ነው፡፡ ሀገራችን አሁንም የባሩድ በርሜል እንደሆነች ነው፡፡ የአሁኑን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ለተመለከተ ሰው ስምንት አስርታትን ተጉዘንም ቢሆን የታሪክን አቀበት አለመውጣታችንን ይገነዘባል፡፡

ዛሬም የዚች ሀገር የአዘቦት ወሬ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ መያዙ ሆኗል፡፡ ምሽግ አንቆፍር እንጅ ጦርነት እንዳለብን ያስታውቃል ፡፡ የውጭ ዜጋ በደቦ መደብድብን በሀገር ውስጥ ተክተናል፡፡

ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ እራሱን ከጠላቶቹ እንዲከላከል ጦር መሳሪያ መታጠቅ ሊፈቀድለት ይገባል ሲል ሙግት ጀምሯል፡፡(የድርጅቱ ቃል አቀባይ ለጀርመን ድምጽ ከተናገሩት) ኢሳት የትግራይ ክልል የጦርነት ልምምድ እያደረገ ነው የሚል ወሬ ደጋግሞ ያሰማል፡፡

የአማራ አክቲቪስቶች የክልሉ ህዝብ ለማይቀረው ጦርነት በደንብ መታጠቅ አለበት ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ ሀገር ወደየት እየሄደ ነው? ትናንት የባሩድ በርሜል የተባልነው ከውጭ ጠላቶች ጋር ለመፋለም ስንዘጋጅ ነበር፡፡ ዛሬስ? የኦሮሞ ህዝብ ጠላቱ ማነው ?የአመራና ትግራይ ህዝብ ይታጠቅ የሚባለው ማንን ሊወጋ ነው?

እኔ እስከሚገባኝ አማራ ሚስት ያለው ኦሮሞ የትዳር አጋሩን ቤቱ አስቀምጦ ዘመዶችሽን ወግቼ ልምጣ ሊል አይችልም፡፡የትግራይ ተወላጅ ያገባ ሰው የልጆቹን ዘመዶች በጦርነት ሊደመስስ ጦሩን አይሰብቅም፡፡ እንዲህ ያለ የደም ትስስር አለ ማለት ግን የነገውን መጥፎ መዳረሻችንን ያስቆመዋል ማለት አይደልም፡፡ የደቦ እብደት ውስጥ የገባ ህዝብ መዳረሻው እርስ በዕርስ መገዳደል መሆኑን ከኢትዮጵያዊያን በላይ ምስክር የሚሆን ያለ አይመስለኝም፡፡

የ1960ዎቹ ትውልድ አባላት እህት ወንድማቸውን በፖለቲካ አመለካከቱ ብቻ መግደልን ለሀገር ከመታመን ጋር ያነጻጽሩት ነበር፡፡ በትግል ውስጥ ያለ ታማኝነትም በፖለቲካ አቋም የተለየ ወንድምን እህትን አብሮ አደግን በመግደል የሚረጋገጥ ሆኖ ነበር፡፡

ዛሬ ወደዚህ አዙሪት ዳግም እየገባን ነው፡፡ ብሄሬን እወዳለሁ የሚል ሁሉ ለብሄሩ መታመኑን የሚገልጸው ጓደኛውን እያስከፋ ሆኗል፡፡ ከዛም ከፍ ሲል በፖለቲካ አቋም የተለየው ወዳጁ ጋር መራራቅን አማራጭ የሚያደርገው ሰው በዝቷል፡፡ ዛሬ በብሄር የተነሳ ወዳጅ ዘመድ ጋር በመጣላት ወፈፍ ማለት የጀመረው ሰው ነገ መገዳዳል የሚሉት እብደት ውስጥ መግባቱ አያጠያይቅም፡፡

ባሩድ በያዘ በርሜል የምትወከለው ኢትዮጵያ ዙሪያዋ በእሳት ተከቧል፡፡ ጥያቄው እኔ እና አንተ ከየትኛው ወገን ነን የሚለው ነው፡፡ እሳቱን ወደ ባሩዱ በርሜል አስጠግቶ ሀገር ለማጋየት ከሚጥሩት ወይንስ ከሚያርቁት?

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close