Connect with us

Ethiopia

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍራንክፈርት የነገሩን ምሥጢር

Published

on

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍራንክፈርት የነገሩን ምሥጢር

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍራንክፈርት የነገሩን ምሥጢር፤ / ጠብመንጃ እየገዛ ያለው ክልል ማነው?
(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጀርመን አቅንተው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቡድን 20 ሀገራትም ሆነ ከአንጌላ መርክል ጋር ያደረጉት ውይይት ብዙም የወሬ አጀንዳ አልሆነም፡፡ ትልቁ አጀንዳና ‹ሰበር› ዜና ሆኖ የሠነበተው የፍራንክፈርቱ ንግግራቸው ነበር፡፡ እንደ አሜሪካና መሠል አገራት መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በፕሮምፕተር በተነበበው ንግግራቸው ‹‹ተስፋ አለኝ›› የሚል ርዕስ ሊሰጠው የሚችል ንግግር ሲናገሩ ነበር፤ ማርቲንሉተር ኪንግ ‹ሕልም አለኝ›› እንዲል!!

ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ትኩረት ያልሰጡት አንድ ግዙፍ ነገር ተናግረዋል፡፡ ‹‹የጎረቤት ክልልን ለመውጋት ጦር መሣሪያ የሚያስገባ ክልል አለ፤ ጠብመንጃ ከሚገዛ ትራክተር ቢገዛ ይሻለው ነበር›› የሚል ይዘት ያለው የጠቅላዩ ንግግር ብዙ ጥያቄዎችን የሚጭር ነው፡፡ ይህ ጠብመንጃ የሚያስገባ ክልል ማነው፣ ለምንስ ዝም ተባለ፣ በፍራንክፈርት በኩልስ ጉዳዩ ለምን እንዲነገር ተፈለገ፣ ይህ ዓይነት ሕገወጥ ተግባር ‹‹ትራክተር ቢገዛበት ይሻል ነበር›› ተብሎ መታለፍ ያለበት ነው ወይ ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡

ባሳለፍነው መሥከረም በዚህ በድሬቱዩብ ላይ ‹‹የሰሜን ዕዝ የማስጠንቀቂያ መልዕክት›› በሚል ርዕስ በተፃፈ ዘገባ ላይ ይህ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ የዕዙ ምክትል አዛዥ፣ ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ‹‹ ‹‹የክልል የጸጥታ ተቋማት አሁን አሁን ለጋራ ደህንነትና ሰላም ከመትጋት ይልቅ፣ ለሌላ ተግባርና ዓላማ የመዘጋጀት ምልክቶች ይታያሉ፡፡ ሁሉም ባላድርሻ አካላት እነዚህ ተቋማት ለተቋቋሙበት ዓላማና ግብ እንዲዘጋጁ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት በአጎራባች ክልሎች ወሰን አካባቢ የታጠቀ ኃይል የማሰባሰብ ዝግጅት የማድረግ እንቅስቃሴዎች ይታያሉ፡፡ ይህ በሕዝቦች ደህንነት ላይ የተደቀነ አደጋ በመሆኑ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ልዩ ትኩረት በመስጠት፣ በሰው ሕይወትና ነብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ የቅድመ መከለከል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡›› ማለታቸውን አንብበን ነበር፡፡

ይህንን የጄኔራሉን ንግግር ነው እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍራንክፈርት የነገሩን፡፡ አስተዛዛቢው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሩን ነግረውን መፍትሔው ላይ ምን እየሠሩ እንደሆነ አለመናገራቸው ነው፡፡ እንደ አንድ የሐገር መሪ በሕዝብ መሀል የእርስበርስ ጦርነት እየመጣ እንደሆነና ሐገሪቱ ወደ ግጭት ልታመራ እንደሆነ መናገርህ ካልቀረ ይህንን ችግር የምትፈታበት መንገድም ይጠበቃል፡፡ እናም ከችግሩ ጎን ለጎን የምትናገረው ቁርጠኛ የመፍትሔ ሐሳብ ሕዝብን ያሰባስባል፤ ያረጋጋልም፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ በፍጥነት የሚቀያየርና ተለዋዋጭ ነው፡፡ ትናንት አብሮ የነበረ ዛሬ ተለያይቶ ይገኛል፡፡ መርህ የለም፡፡ እሩጫና ስሜት ሐገሪቱን ወርረዋታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ ግርግር ሁሉ አለቃና የበላይ ጠባቂ ናቸው፡፡ በዚህ መደናበር መሀል ጦር መሣሪያ እየገዛ ያለውን የክልል መንግሥት በአግባቡ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለባቸው፡፡ መቆጣጠር ከተሳናቸውም ሕዝብ እንዲያግዛቸው ጥሪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ባንኩም ታንኩም ያለው እርሳቸው እጅ ነውና!!

ለእርስበርስ ጦርነት ሲባል ጦርመሣሪያ የሚያሥገባ ክልላዊ መንግሥት ካለ በቅድሚያ መጠየቅ ያለበት በድሃዎች ግብር የቆመው የፌደራል መንግሥትና ሠራዊቱ ናቸው፡፡ ይህንን ጉዳይ መቆጣጠርም ሆነ መቅጣት፣ ማጋለጥም ሆነ ማውገዝ ያለባቸው የአገሪቱ ርዕሰመንግሥት ናቸው፡፡

ደግሞስ ይህንን የሚያህል ጉዳይ ለምን ከፍራንክፈርት እንድንሰማ ተፈለገ፤ ከአሁን በፊትስ ለምን በሰሜን እዝ አዛዥ በኩል እንዲነገር ተፈለገ፣ ጦር መሣሪያን የሚያህል ጸረ-ሰው ነገር ወደ ሐገር ቤት በገፍ እየገባና ትንሹም ትልቁም እየታጠቀ ባለበት በዚህ ወቅት የመንግሥት የመቆጣጠርና የመቅጣት ፖሊሲ የትጋር ነው ያለው፡፡

አስገራሚው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍራንክፈርት ላይ ይህንን እየተናገሩ እዚህ እንጦጦ ተራራ ላይና መተማ ላይ (በአደጋ በወደቀ ቦቲ ውስጥ) ጦር መሣሪያ እየተያዘ ነበር፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close