Connect with us

Entertainment

የፓስተር እዩንና የአክተር ጀትሊን የካራቴ መንፈስ ያጎናጸፈ ክስተት… | በአሳዬ ደርቤ

Published

on

የፓስተር እዩንና የአክተር ጀትሊን የካራቴ መንፈስ ያጎናጸፈ ክስተት… | በአሳዬ ደርቤ

የፓስተር እዩንና የአክተር ጀትሊን የካራቴ መንፈስ ያጎናጸፈ ክስተት… | በአሳዬ ደርቤ

አዲስ መኪና ገዝቻለሁ፡፡ ‹‹መኪና›› የሚለውን ቃል በራሴ መንገድ ስተነትነው ‹‹ከሆነ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሳይሆን ከአንዱ ደስታ ወደሌላ ደስታ የሚያሸጋግር መንኮራኩር›› በማለት ነው፡፡

መሪ ስጨብጥ ከመኪና ባለፈ የአንዲት አገር ስልጣን የጨበጥኩ ያህል ደስታ ስለሚሰማኝ የውስጤን ፈንጠዚያ ክላክስ በመንፋትና በፍጥነት በመንዳት እገልጻለሁ፡፡ (አሁን ራሱ ይሄን የምጽፈው መኪናዬ ውስጥ ተቀምጬ በመሆኑ በእያንዳንዱ አንቀጽ መሃከል የጡርንባ ድምጽ መኖሩን ልብ ይሏል፡፡)

መኪና የመግዛት ሂደቱ አድካሚ ነበር፡፡ ዓመት ከመንፈቅ ፈጅቶብኛል፡፡ የመጀመሪያ እቅዴ ቁጠባን ባህል በማድረግ ባጠራቀምኩት 300 ሺህ ብር ‹ራቫ-ፎር› መግዛት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሄንን ሃሳቤን ያሳኩ ዘንድ የደወልኩላቸው ደላላዎች ‹‹በዚህ ብር ራቫ-ፎር መግዛት ከተቻለ ለእኛም ፈልግልን›› በማለት ሳቁብኝ፡፡

ስለዚህም መኪናውን በራሴ ጥረት ለመግዛት በማሰብ… የምፈልገውን አይነት ተሸከርካሪ የሚነዱ ሰዎች ባየሁ ቁጥር መንገድ ላይ እያስቆምኩ ‹‹በ300 ሺህ ብር ልግዛችሁ›› ስላቸው ከረምኩ፡፡ በመጨረሻ ግን አንድ እብድ አሽከርካሪ ‹‹ሶስት መቶ ቦታ ይቆራርጥህና…›› ብሎ ከመኪናው በመውጣት ስላሯሯጠኝ ይሄን እቅዴን ሰረዝኩት፡፡

አሁን ራቫ-ፎር ባይሆንም ቪትዝ ገዝቻለሁ፡፡ ግዥውን የፈጸምኩት ከአንዲት ሴት ላይ ስለሆነ መኪናው ከአሮጌነት ይልቅ ለአዲስነት ይቀርባል፡፡ ምክንያቱም የሃገራችን ሴቶች ባሎቻቸውን እንጂ መኪናቸውን አያጎሳቁሉም፡፡ ከባል አያያዝ በላይ የቤትና የመኪና አያያዝ ያውቃሉ፡፡

እናም በእኔ ጥረት ብቻ ሳይሆን በመለኮታዊ ጣልቃ-ገብነት ጭምር የገዛኋትን መኪና ይዤ መንሳፈፍ ከጀመርኩ አንድ ወር አለፈኝ፡፡

በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ… ለሚስቴ የምሰጠውን የወር ደሞዜን ለትራፊክ ፖሊሶች አስረክቤያለሁ፡፡ ዶክተር አቢይ ለጥቂት ሴቶች ሹመት ሲሰጥ እኔ ደግሞ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች ሊፍት ሰጥቻለሁ፡፡ (ልዩነቱ ጠቅላይ-ሚኒስቴሩ ስልጣኑን ያደለው ለእናቶቻቸው ሲሆን እኔ ሳገለግል የከረምኩት ልጆቻቸውን መሆኑ ነው፡፡)

ይሄ ተዓምራዊ ክስተት ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ቤቴ ተቀምጬ ቴሌቪዥን መመልከት ትቻለሁ፡፡ ሶሻል ሚዲያ ላይ መጦመሩንም እረስቸዋለሁ፡፡ ሞባይል ጨብጬ ‹‹ይች አገር ወደት እየሄደች ነው?›› በማለት ፈንታ…. መሪ ጨምድጄ ‹‹ወደ የት እየሄድኩ ነው?›› ወደማለት ተሸጋግሬያለሁ፡፡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን የሚሰጠውን መግለጫ እርግፍ አድርጌ በመተው የሳጂን አሰፋ መዝገቡን ሪፖርት መከታተል ጀምሬያለሁ፡፡ (ቤልት ታጥቄ ስለምውል… ኦነግ ትጥቁን ይፍታ አይፍታ የማውቀው ነገር የለም፡፡)

የስነ-ልቦና ሙህራን የደስተኝነት ስፍራው በልብ ውስጥ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እኔ ግን ‹‹የደስታ ምንጬ ልቦና ውስጥ ሳይሆን ጋቤና ውስጥ ነው›› እላለሁ፡፡ ካላመንከኝ ገዝተህ ሞክረው፡፡

ባለፈው ታዲያ ሲያቀብጠኝ ይህችን መኪናዬን በመያዝ ከአዲስ አበባ ወጥቼ ነበር፡፡ እናም የሆነ አካባቢ ስደርስ ረብሻ ተነስቶ ጠበቀኝ፡፡ በርካታ ወጣቶች መንገዱን ዘግተው ‹‹መሬታችንን የወረሩ መጤዎች ይውጡልን›› የሚል መፎክር ያሰማሉ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የመፎክራቸው ይዘት ‹‹የአገሬን እንጂ የመኪናዬን ህልውና አደጋ ውስጥ ይከታል›› የሚል አመለካከቱም ሆነ ግምቱ አልነበረኝም፡፡

የሆነው ግን እንደዚያ ነበር፡፡

ከወጣቶቹ መሃከል የተወሰኑት ተቀንሰው በመምጣት መኪናዬንና ደስታዬን ከበቡት፡፡

አስራ ምናምን ዓመት በፈጀ ‹‹ቁጠባ›› የገዛኋትን መኪና የእነሱ ቁጣ መብረጃ ሊያደርጓት መጠቃቀስ ጀመሩ፡፡

የእኔን ጥረትና የፈጣሪን ታላቅነት የምትመሰክር ተሸከርካሪዬን እንደ ልደት ቀን ሻማ ሊለኩሷት ‹‹ክብሪት፣ ክብሪት›› ይባባሉ ያዙ፡፡

አንዱ ወጣት መለኮሻ ሊያመጣ ሲሄድ ሌሎቹ የመኪናዬን መስታወት እያንኳኩ ‹‹ፈጠን ብለህ ውጣ›› የሚል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ቀጠሉ፡፡

ወጣቶቹ ገና ‹ጥሬዎች› ስለነበሩ የአሽከርካሪውን ፊት የማንበብ አቅሙ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም መኪናዋን ከማቃጠል በፊት ሹፌሩን መግደል አስፈላጊ መሆኑን አልተረዱም፡፡ እኔ በህይወት እስካለሁ ድረስ ይህችን መኪናዬን ሊያነዷት ቀርቶ ሊነዷት እንደማይችሉ አልገባቸውም፡፡ ሊገልጹት ያሰቡትን ቁጣ ሙልጭ አድርጌ በመቀማት ከሰውነት ወደ አቦ-ሸማኔነት እንደተቀየርኩ አልተገነዘቡም፡፡

እነሱ መኪናዬን ለመገልበጥ የሸሚዛቸውን እጅጌ መሰቅሰቅ ሲጀምሩ እኔ በውስጤ ያለውን ተስፋ ቁ.ር.ጥ.ር.ጥ አድርጌ ጨርሼ ነበር፡፡ (ለካስ ‹‹ጀግንነት›› ማለት ተስፋ ከመቁረጥ የሚመጣ ስሜት እንጂ ከፈጣሪ የሚሰጥ መክሊት አልነበረም፡፡)

ሌባ ጎማ ጨብጬ በድምጽ ፍጥነት በዓየር ላይ ከመንከረባበቴ በፊት… መኪናዬን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አየኋት፡፡ በአራቱም ማዕዘን የአማልክት ምስልና የምስጋና ቃል ተለጥፎባታል፡፡

ከዚያ በኋላ ስለሆነው ነገር ባወራችሁ አይገባችሁም፡፡ ብቻ ግን… የፓስተር እዩ እና የአክተር ጀትሊ የካራቴ መንፈስ በላዬ ላይ ወርዶ ነበረ፡፡

ከፊሎቹ ከእግሬ ስር ሲረፈረፉ… እኩሎቹ ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ብለው ተፈተለኩ፡፡

መኪናዬን አዙሬ ስመለስ ከለጠፍኳቸው ጥቅሶች መሃከል አንዱ ‹‹የሰማዩ ጌታ እንኳን ከኩታራ መንጋ ከአንበሳ መንጋጋ ፈልቅቆ የሚያወጣ ነው!›› ይላል፡፡

የገባው ካለ ‹‹አሜን›› ይበል፡፡

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close