Connect with us

Art and Culture

የአርቲስት ፍቃዱን ለማሳከም ገንዘብ ሲሰበስብ የቆየው ኮምቴ አባላት አልተግባቡም

Published

on

የአርቲስት ፍቃዱን ለማሳከም ገንዘብ ሲሰበስብ የቆየው ኮምቴ አባላት አልተግባቡም

የአርቲስት ፍቃዱን ለማሳከም ገንዘብ ሲሰበስብ የቆየው ኮምቴ አባላት አልተግባቡም

*አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ የሰበሰበውን ገንዘብ ወደኮምቴው የሒሳብ ቋት አላስገባም ማለቱ የግጭቱ መነሻ ነው፣

በቅርቡ በሞት የተለየው የአርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም የህክምና ገቢ አሰባሳቢ ኮምቴ አባላት መካከል ለድጋፍ የተሰበሰበ ገንዘብን አወጣጥና አስተዳደር በተመለከተ አለመግባባት ተከሰተ፡፡

የኮምቴው አባላት ማለትም አቶ ኃይሉ ከበደ- ሰብሳቢ፣ ወ/ሮ መቅደስ ጸጋዬ፣ አቶ ሳምሶን ብርሃኑ፣ አቶ ቴዎድሮስ ተስፋዬ፣ ወ/ሮ መሰረት መብራቴ፣ አቶ ውድነህ ክፍሌ በአንድ በኩል፤ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ጋር በዋንኛነት በገንዘብ አወጣጥና አስተዳደር ጋር ተያይዞ ስለተከሰተው አለመግባባት በዛሬው ዕለት ካዛንቺስ በሚገኘው አፍሮዳይት ሆቴል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የነገሩ አመጣጥ፡-

ሟች አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በኩላሊት ሕመም እየተሰቃየ መሆኑ ከተሰማ በኃላ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን በማስተባበር ገቢ አሰባስቦ አርቲስቱን በማሳከም ሐይወቱን ለመታደግ ይህ ኮምቴ ሥራ ጀመረ፡፡ የገንዘብ ማሰባሰቡ ሒደት በሁለት መልኩ መጀመሩን የኮምቴው አባላት ይገልጻሉ፡፡ አንዱ በአገር ቤት የገንዘብ ማሰባሰብ ሒደት ሲሆን ሁለተኛው በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች በ ጎ ፈንድ ሚ ( Go fund me) አማካይነት በአቶ ቴዎድሮስ ተሾመ የውጭ አገር አካውንት ተሰብስቦ ገቢ እንዲሆን የተደረገበት አካሄድ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአሁን ሰዓት በአገር ቤት በሶስት ሰዎች በሚንቀሳቀስ ሒሳብ ውስጥ ብር 1 ሚሊየን 200 ሺ 895 ብር ከ65 ሳንቲም የሚገኝ መሆኑን፤ በአቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በኩል በ ጎ ፈንድ የተሰበሰበው ገንዘብ 73 ሺ 900 የአሜሪካን ዶላር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ልዩነቱ የተፈጠረው በአቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በኩል የተሰበሰበው ገንዘብ በአንድ የሒሳብ ቋት ገብቶ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ጥቅም ላይ እንዲውል አቶ ቴዎድሮስ ሲጠየቅ ገንዘቡን ለማስገባት ፈቃደኛ ካለመሆኑ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ለዚህ የሰጠው መልስ ኮምቴውን አላምነውም የሚል እንደሆነ የኮምቴው ሰብሳቢ አቶ ኃይሉ ከበደ አስረድተዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በበኩሉ 73 ሺ 900 ዶላር መሰብሰቡን አረጋግጦ ነገርግን የኮምቴውን የቀውስ (የክራይሲስ) ማኔጅመንት ስለማላምንበት ገንዘቡን ማስገባት አልቻልኩም ብሏል፡፡ በእሱ በኩል የተሰበሰበውን ገንዘብ ኮምቴው በሚያውቀው መልኩ አርቲስት ፍቃዱ በሕይወት እያለ ለሕክምና ወደሕንድ ሄዶ እንዲታይ መደረጉን፣ የፍቃዱ የቀብር ስነስርዓት በስዓቱ እንዲፈጸም መደረጉን፣ ሐውልት ለማሰራት ዲዛይን እየተሰራ መሆኑን፣ ከቤተሰቦቹ ጋር በመነጋገር የኩላሊት ሕክምና መስጫ የዲያሌሲስ ማሽን ገዝቶ ለሚመለከተው አካል ለመስጠት መስማማቱን ይፋ አድርጎአል፡፡ ከዚህ የሚተርፈው ገንዘብ አግባብ ባለው ሕግ መሠረት ለሚቀርቡ ወራሾች እንደሚሰጥ አቶ ቴዎድሮስ አስረድቷል፡፡

 

በርካታ ጋዜጠኞች በተፈጠረው የኮምቴ አባላት ልዩነት ማዘናቸውንና አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያምን በዚህ መልኩ ስሙን ማስነሳት ተገቢ አለመሆኑን በመጥቀስ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

አንዳንድ ጋዜጠኞች ገንዘቡ ሕዝብ የሰጣችሁ አደራ እንጂ እንደፈለጋችሁ የምትወስኑበት አይደለም፡፡ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ገንዘቡን ወስነህ ለመመንዘር ማን ፈቀደልህ? የተረከብከው ገንዘብ በትክክል የተባለው ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ታቀርባለህ? ገንዘቡ በትክክል ወጥቶ ሥራ ላይ ስለመዋሉ የሚያረጋግጠው ማንነው? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ቀርበው መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በሰጠው ምላሽ ገንዘቡ በጎ ፈንድ ሚ ድረገጽ በግልጽ በሚታይ መልኩ መሰብሰቡንና አሁንም ማየት እንደሚቻል ጠቁሞ ደረሰኞቹን በራሴ ድረገጽ አቀርባቸዋለሁ ብሏል፡፡ ገንዘቡን በኮምቴው ሒሳብ ቋት ያላስገባው በኃላ በማላዝበት ገንዘብ ተጠያቂነት ቢመጣ ስሙ ሊጠፋ እንደሚችል የሕግ አማካሪው የሰጠውን ምክር በመስማት መሆኑን፣ ሕሊናውን የሚወቅሰው ሥራ አለመስራቱን ጠቅሶ ለሚኖር ጥፋት ሁሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጿል፡፡

በመጨረሻም አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ አሁንም ከሕግ አማካሪው ጋር በመመካከር ከኮምቴው ጋር ለመስራትና ገንዘቡም ሕዝብ ስላወቀው ከዚህ በኃላ ወደኮምቴው አካውንት ቢገባም ችግር እንደማይኖረው አስረድቷል፡፡

በኮምቴው በኩልም መተማመንን ለመፍጠር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተው ሒሳብ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ ገንዘቡን ካስገባ አራተኛ ፈራሚ (ሒሳብ አንቀሳቃሽ) ሆኖ እንዲሰራ ማመቻቸት እንደሚችል ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close