Connect with us

Art and Culture

ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬኑስ፤ እናቷ ዳኛ ልጇን እንዳንከስ…

Published

on

ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬኑስ፤ እናቷ ዳኛ ልጇን እንዳንከስ… | አሳዬ ደርቤ

ወንዶች ከማርስ ሴቶች ከቬኑስ፤ እናቷ ዳኛ ልጇን እንዳንከስ… | አሳዬ ደርቤ

ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከቤቴ ወጥቼ መንገድ ላይ እየተንገላወድኩ ሰፈሬን እቃኛለሁ፡፡
በአውራ ጎዳናው ላይ ደም-ግባታም ሴቶችና ግርጣታም ወንዶች ውር ውር ይላሉ፡፡

ፈገግ በሚሉበት ወቅት… ወንዶቹ ድድ ላይ ‹አነቃቂ ጫት› ሴቶቹ ጥርስ ላይ ደግሞ ‹‹አብረቅራቂ ብረት›› ተለጥፎ ይታያል፡፡
‹‹አልማዝ›› የምትባል ሚስቱ ጥላው ወደ ውጭ አገር ከሄደች ጊዜ አንስቶ ለእብደት የተዳረገው ‹‹በለጠ›› የሚስቱን ፎቶ አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ ‹‹ይህች ሴት ያለችበትን ቦታ ለሚጠቁመኝ ወረታውን እከፍላለሁ›› እያለ ቁልቁል ወረደ….

ከፊታቸው ላይ ውበታቸውን እንጂ እድሜያቸውን የማያሳዩ ኮረዳዎች ወደ ‹ሳራ ኮስሞቲክስ-ቤት› እየገቡ… ጸጉር፣ ቅባት፣ ሽቶ፣ ጡት ማስያዣ፣ ዶድራንት፣ ፒኪኒ፣ መነጽርና መሰል ነገሮችን እየገዙ ይበታተናሉ፡፡ ወንዶቹ ደግሞ ወደ ሸምሱ ጫት ቤት በመሄድ ወንዶ፣ በለጬ፣ ገለምሶ፣ ሂርና፣ ማጣቀሻ፣ ልዩ፣ ጉራጌና አወዳይ.. እየገዙ ይሰወራሉ፡፡

ከጫት ቤቶቹ አጠገብ የሚገኘው ‹‹አትለፉኝ ቡና ቤት›› ተሟሙቋል፡፡ ሴቶቹ ይቀዳሉ፣ ወንዶቹ ያንቃርራሉ፡፡

ይሄን እያየሁ እንዳለ አንዲት ሴት ስትንደረደር መጥታ ወደግሮሰሪው ከገባች በኋላ… በግዙፍ እጇ የሆነ ምስኪን ሰካራም የሸሚዝ ኮሌታ ጨምድዳ ወጣች፡፡ ሰካራሙ እየተወላገደ ‹‹እዚሁ ግደይኝ›› ሲላት ‹‹ሕይወት ሲኖርህ አይደል!›› እያለች ትመልስለታለች፡፡

በአሮጌ ቤቶች ለተሞላው ሰፈራችን ‹ድምቀትን› የፈጠረ ባለኮከብ ሆቴል ከፊት ለፊቴ ደረቱን ገልብጦ ይታያል፡፡ ሆቴሉ አቶ አስፋው በተባለ ባለሃብት የተሰራ ሲሆን ባለሃብቱ የሞተው ሆቴሉ ሳይመረቅ በፊት ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ባልታወቀ ምክንያት ሽጉጡን በመጠጣቱ ሲሆን ሚስቱ ግን ሻምፓኟን እየጠጣች ሆቴሉን ማስተዳደሩ ያን ያህል አልከበዳትም፡፡ የሆቴሉ ትርፋማነት የተመሰረተው በሚበዘበዙ ወንዶችና በሚጋበዙ ሴቶች ህልውና ላይ ነው፡፡

ከሆቴሉ ጀርባ ወንዶች የሚታሰሩበት ወህኒ-ቤት አለ፡፡ እዚህ እስር ቤት ውስጥ ሴቶችን ማግኘት ከቻልክ ያየኻቸው ሴቶች እስረኞች ሳይሆን ፖሊሶች መሆን አለባቸው፡፡

እነዚህ ታራሚዎች በድብደባ፣ በግድያ፣ በስርቆትና በመሳሰሉት ወንጀሎች የሚታሰሩ ቢሆኑም ‹‹ለምን ይሄን አደረጋችሁ?›› ተብለው ሲጠየቁ የሚሰጡት መልስ አንድ አይነት ነው፡፡

‹‹ለምን ገደልከው?›› ሲባሉ ሚስቴን ሲያመግጥብኝ ይዠው… ‹‹ለምን ወደ ዘረፋ ገባህ?›› ሲባል.. ‹‹እጮኛዬ ወርቅ ግዛልኝ ብላኝ››… በማለት በስሜት ሳይሆን በሴት ተመርተው ወደ ወንጀል መግባታቸውን የሚናዘዙ ናቸው፡፡

ከዚህ የምንረዳው ነገር ከእፀ-በለስ ባለፈ አሳራችንን የሚያበሉን የሄዋን ዘሮች ከስኬታችን ብቻ ሳይሆን ከወንጄላችን ጀርባም መኖራቸውን ነው፡፡

ባየሁትና ባሰብኩት ነገር ራስ-ምታቴ መነሳት ሲጀምር ፓራስታሞል ልገዛ ወደ ፋርማሲ አመራሁ፡፡ ውስጥ ላይ አንዲት ቆንጅዬና የሆነ ዱርዬ ተስተናጋጆች ቆመዋል፡፡ ቆንጅዬዋ ጀርመን አገር የተሰራ ቫዝሊን ገዝታ ስትወጣ.. ዱርዬው ‹‹ቪያግራ ስጡኝ›› በማለት ጠየቀ፡፡ ፋርማሲስቱ ‹‹በወተት አድርገህ ውሰደው›› ሲለው ‹‹ማዘዣ ካልጻፍክልኝ በቀር ወተቷን ለመጥባት ቀርቶ ጡቷን ለመንካትም አትፈቅድልኝም›› ብሎት ወጣ፡፡

የገዛሁትን ፓራስታሞል ይዤ ወደ አብዲ ካፌ በመግባት ግማሽ ሊትር ውሃ አዘዝኩኝ፡፡ ከአጠገቤ ባልና ሚስት የሚመስሉ ጥንዶች ተቀምጠዋል፡፡ ሴቷ እስፕሪስ ጁስ በስትሮው ትመጣለች፡፡ ባልዬው ደግሞ የሚዝረበረብ አፍንጫውን በሶፍት ወትፎ በቀሽር ሻይ ይገሸራል፡፡ በእጆቹ መዓት መጽሐፍቶችን የተሸከመ አንድ ወጣት በመጣ ጊዜም… እሷ የማካቬሌን መጽሐፍ ስትገዛ እሱ ደግሞ የጆርዳናን መጽሐፍ ሸመተ፡፡

መድሃኒቴን ከዋጥኩ በኋላ ከካፌው ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ቴሌቪዥን የሚያቀርበውን ፕሮግራም መከታተል ጀመርኩ፡፡

ፕሮግራሙ ‹‹ዶክተር አቢይ አስር ወንዶችን አባርረው አስር ሴቶችን በሚኒስቴርነት በሾሙ ማግስት ዶክተር ሙላቱን አሰናብተው ወይዘሮ ሳህለ ወርቅን የሃገራችን ፕሬዝዳንት ማድረጋቸው አልበቃ ብሎ… በዛሬው እለት ደግሞ የጠቅላይ ፍርድ-ቤት ኃላፊነቱንም ለአንዲት ሴት ማስረከባቸውን›› የሚያብራራ ነው፡፡ ማለትም ‹‹አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ›› የሚለው ብሔል ‹‹እናቷ ዳኛ ልጇ ቀማኛ›› በሚል አባባል መቀየሩን የሚያረዳ ነው፡፡ ይሄ ፕሮግራም እንዳለቀ ደግሞ የሆነች ታዋቂ አርቲስት ‹‹ሚስት ከማግባትዎ በፊት ሪል-ስቴት ገዝተውላታል?›› የሚል ማስታወቂያ ታቀርብ ጀመረ፡፡

ዐይኔን ከስክሪኑ አንስቼ ሞባይሌን በማውጣት ፌስቡኬን ስከፍተው እንደተለመደው ሁላ ወንዶቹ መንግስታቸውንና አገራቸውን የሚያማርር ፖለቲካ አዘል አርቲክል ይጽፋሉ፡፡ ሴቶቹ የሚያማምር ፎቶዎቻቸውን እየለጠፉ አድናቆት ይሰበስባሉ፡፡

የውሃውን ሂሳብ ከፍዬ ከካፌው በመውጣት ወደ ቤቴ ሳዘግም ከሚስቴ ጋር መንገድ ላይ ተገጣጠምን፡፡ በቅርቡ ቦሌ ክፍለ-ከተማ ላይ የሆነ ሹመት ከተሰጣት ጊዜ አንስቶ ሚስትነቱን ትታ ባሌ ሆናለች፡፡ ቦርሳዋን የማየት እድሉን ባላገኝም ከሁኔታዋ ተነስቼ ስጠረጥር ከሹመት በተጨማሪ ሽጉጥም የተሰጣት ይመስለኛል፡፡

እናም ‹‹የት አባክ አምሽተህ ነው?›› ስትለኝ ከእኔ አልፋ የአባቴን ስም ማንሳቷ የፈጠረብኝን ብስጭት ዋጥ በማድረግ ‹‹መድሃኒት ልገዛ ወጥቼ ነው›› በማለት መለስኩላት፡፡

እሷ ግን ምን ልታደርገኝ እንዳሰበች እንጃ ‹‹መርዝ ብትገዛ ይሻልህ ነበር›› እያለች ታስፈራራኝ ጀመር፡፡
ሃሳቤ ሲጠቃለል….

‹‹ያለንባት ፕላኔት ለወንዶች ምቹ አይደለችም!!›› ስለዚህም ‹‹ወንዶችን ከማርስ፣ ሴቶችን ከቬኑስ›› አምጥቶ ምድር ላይ ያገናኘን አምላክ… ተቃጥለን ከመሞታችን በፊት ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ወደ ቀድሞ ፕላኔታችን እንዲመልሰን ጾለታችንን ማጠናከር ያለብን ይመስለኛል፡፡

እናንተስ?

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close