Connect with us

Ethiopia

ግልጽ ደብዳቤ! – ይድረስ ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ፡-

Published

on

ግልጽ ደብዳቤ! - ይድረስ ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ፡-

ግልጽ ደብዳቤ!
ይድረስ ለጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ፡-
የሐረር ሕዝብ የመጠጥ ውሃ እገታ በዝምታ ማለፍዎ ለምን ይሆን?

እሱባለው ካሳ (ከሐረር)

ለጤናዎ እንደምን ከረሙልኝ? እኔ የውሃ ማማ በምትባል አገር ውስጥ፤ በውሃ ጥም ስቃይ ውስጥ ከእነቤተሰቤ እንደማቀቅን አለን፡፡ በቅድሚያ ለገጽታ ግንባታ ወደአውሮፓ ለመጓዝ እየተዘጋጁ ባሉበት በዚህ ወቅት ገጽታን የሚያጠለሽ መርዶ ነጋሪ አቤቱታ ይዤ በመቅረቤ ይቅርታዎን እጠይቃለሁ፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ወደመንበረ ሥልጣኑ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በማራኪ ንግግርዎ ስደመም ከቆዩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች አንዱ ነኝ፡፡ መደመሜ ምናልባትም ርኩሱን ዘመን በይቅርታና በፍቅር ሊያሻግሩን ይችላሉ ብዬ ተስፋ በማድረጌ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋዬን የሚሸረሽሩ ሁኔታዎችን ማስተዋል ስጀምር መደንገጤን ልሸሽግዎ አልችልም፡፡

ሌላ ሌላውን ትቼ፤ በሐሮማያ አካባቢ ባሉ የመንደር ጎረምሶች ባነሱት ሚሊየን ብሮች ይከፈለን ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሐረር ውሃ ተሰብሮ ሕዝብ በውሃ ጥም እንዲሰቃይ የመደረጉን ዜና እንደሚያውቁት አልጠራጠርም፡፡ ለወትሮም ቢሆን የሐረሪ ክልል የውሃ አቅርቦት የተዘረጋው በየረር-ሐረማያ-ድሬዳዋ መስመር ሲሆን 1/3ኛውን የክልሉን የውሃ ፍላጎት እንደሚሸፍን ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሐረሪ ክልል መንግስት ከፍተኛ አመራሮች በሙስናና ብልሹ አሠራር እስከአናታቸው የተዘፈቁ በመሆኑ ለዚህ ከባድ ችግር ቀርቶ ለጥቃቅኑዋም ቢሆን ተስፋ የሚጣልባቸው አይደሉም፡፡ እናም ይህን ችግር መፍታት ቢያቅታቸው ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡

ነገርግን ሐረሪን በጣምራ ከሚያስተዳደሩት ክልሎች አንዱ የሆነውና እርስዎ በሊቀመንበርነት የሚመሩት አዴፓ/ኦህዴድ ይህን ነገር ሰምቶ እንዳልሰማ ዝምታን መምረጡ አስገራሚና አሳዛኝ ነገር ሆኖብናል፡፡ አሁንም እርስዎ የሚመሩትና ሌት ተቀን ስለህግ የበላይነት ላንቃው እስኪበጠስ የሚሰብከው ፣ የሰላም ጉዳይ አሳስቦት በሚኒስትር ደረጃ ለማቋቋም የተጋው የፌዴራል መንግሥትዎ ዝምታን መምረጡ በእውነቱ መንግስት አለ ወይ ብለን እንድንጠይቅ እያስገደደን ነው፡፡

ክቡርነትዎ፤ በአሁን ሰዓት የሐረር ሕዝብ የመንግሥት ያለህ፤ የፍትህ ያለህ እያለ ነው፡፡ ሕዝብ ሥራውን ትቶ፣ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ተስተጓጉለው ውሃ ፍለጋ ሲባዝኑ የሚውሉበት አሳዛኝ ሁኔታ ተከስቷል፡፡ በከተማዋ ንጽህናው ያልተጠበቀ አንድ ጀሪካን ውሃ ከ15 እስከ 20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ራሳቸውን “ቄሮ“ብለው የሚጠሩ የወረበሎች ቡድን ውሃውን በማገታቸው ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በየደረጃው የሚገኝ የመንግሥት አካል እነዚህን ወረበሎች ቆንጥጦ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር አቅም በማጣቱ ነው፡፡

ክቡርነትዎ እንደሚያስታውሱት ባለፈው ሰሞን በአዲስ አበባ ተቃውሞ ተቀሰቀሰ በሚል ሰበብ ወጣቶችን አፍሶ ለመቅጣትና በ48 ሰዓታት ፍርድ ቤት የማቅረብ ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ ጭምር እስከመጣስ የሄደው የፖሊስና የደህንነት መዋቅር ይህን ችግር እንደምን መፍታት ተሳነው?

ክብርነትዎ፤ እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት አልበኝነት በእንጭጩ ለመቀልበስ ማንገራገርዎ በቀጣይ ሊያስከፍልዎ የሚችለውን ከባድ ዋጋ እንደምን ዘነጉት?

ክቡርነትዎ!.. አሁንም ቁጥሩ ወደ 300 ሺህ የሚጠጋው የሐረር ሕዝብ በከፍተኛ ትግዕስት በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ሕግና ሥርዓትን እንዲያስከብሩ እየወተወተ ነው፡፡ ይህን ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን፣ በመሸሽ፣ ጉዳዩን ትኩረት በመንፈግ የሚፈታ ችግር የለም፡፡ እናም አቤቱታዬ የእርምት እርምጃ ይወሰድ ዘንድ ፈጣን አመራርዎን እንዲሰጡና ጉዳዩንም እንዲከታተሉት በታላቅ ትህትና ለማስታወስ ብቻ የተጻፈ መሆኑን ይረዱልኝ፡፡

መልካሙን ሁሉ እመኝልዎታለሁ!

 

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close