Connect with us

Ethiopia

የጠብመንጃ ሳምንት | በያየሰው ሽመልስ

Published

on

የጠብመንጃ ሳምንት | በያየሰው ሽመልስ

የጠብመንጃ ሳምንት | ያየሰው ሽመልስ

ሰሞኑን የኦነግ ትጥቅ አልፈታም ብሎ ማሽሟጠጥ (የአቶ ዳውድ ኢብሳን ገዳይ ፈገግታ መቼም አንዘነጋትም) መነጋገሪያ ከሆኑ ዓቢይ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በርግጥ ሰውዬው ለዋልታ ቴሌቭዥን ከሰጡት መግለጫ በተጨማሪ በቪኦኤም ‹‹እኛን ትጥቁ ፍቱ ማለት ጦርነት ማወጅ ነው›› ብለው ተናግረዋል፡፡ ይህንን የኦቦ ዳውድን ንግግር ለየት የሚያደርገው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹የኦነጉ ሊቀመንበር ያደረጉት ንግግር የአፍ ወለምታ ነው፤ ታጣቂ የሠላም ፖለቲከኛ የለም›› ብለው ከተናገሩ በኋላ የተደመጠ በመሆኑ ነው፡፡

ለነገሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ምክትል ሚኒስትሩ ‹‹ኦነግ እራሱ ትጥቁን ካልፈታ መንግሥት የፌደራል የጸጥታ ኃይሉን ተጠቅሞ በግድ ያስፈታዋል›› የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ኦቦ ዳውድ ግን ይህንንም ከቁምነገር አልቆጠሩትም፡፡ ‹‹መንግሥት ጦርነት አወጀብን›› የሚል ውንጀላም ማሰማት ጀምረዋል፡፡

የሆነው ሆኖ ይህ ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በኦነጉ አለቃ አስተያየትም ብዙዎች ተበሳጭተዋል፡፡ በርግጥ የኦነግ ሥህተት ምንድን ነው፣ ሊቀመንበሩ የተናገሩት ነገር ከኦነግ ባሕርይና ተፈጥሮ አንፃር አዲስ ነገር ነው ወይ ወዘተ የሚሉት ነገሮች በዚህ ብስጭት ውስጥ ተነስተው ውይይት እየተደረገባቸው አይደለም፡፡ ግን ብዙዎች መናደዳቸውን በመገናኛ ብዙሃንና በማኅበራዊ ገፆች በሚሰጡት አስተያየት መገንዘብ ይቻላል፡፡

ቀድሞ ነገር የመንግሥትና የአማፅያን ድርድር ይዘት ለሕዝብ ግልጽ ይደረግ፣ እያሉ ይጠይቁ የነበሩ ሰዎች አንድ ጊዜ ለውጥ አደናቃፊ፣ ሌላ ጊዜ የቀን ጅብ እየተባሉ ይሸማቀቁ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ሁሉ ነገር የነ ቶሎቶሎ ቤት ሆኗል፤ አስመራ የሄዱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህና የኦሮሚው ርዕሰ መስተዳድር ለማ ምን ተነጋግረው እንደመጡ አይታወቅም፡፡ ለሕዝብም የተነገረ ነገር የለም፡፡

ይህ በሌለበት ነው እንግዲህ ኦነግ ላይ ወቀሳ የበዛው፡፡ መንግሥት ከኦነግ ጋር ምን እንደተደራደረ፣ ምን እንደተስማማና ምን በይደር እንዳቆየ የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ለዚያም ነው አገር ቤት ከገቡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤትና ራሱ ኦነግ እርስበርሱ የሚባላ መረጃ መስጠት የጀመሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳመኑት የትጥቅ ጉዳይ በድርድሩ ላይ አልተነሳም፤ ኦቦ ዳውድ እንዳሉት ደግሞ ትጥቅን በተመለከተ አንዱ ፈቺ ሌላው አስፈቺ አይሆንም፤ የኮሙዩኒኬሽን ጽ/ቤት ደግሞ እንዴት እንደምናስፈታህ እናሳያሃለን እያለ ነው፡፡

ከዚሁ ሁሉ ጣጣ የሚሻል የነበረው የሥምምነቱን ዝርዝር ይዘት ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ከኤርትራም ሆነ ከአረቦቹ ጋር እየተደረገ ያለው ሥምምነት ይዘቱ ግልጽ እስካልሆነ ድረስ መዘዝ ይዞ መምጣቱ አይቀርም፡፡

የወታደሮቹ እጣፈንታ
——————-
ሁለተኛው ጠብመንጃ ነክ ነገር ሰሞኑን ያመጹትን ወታደሮች የሚመለከት ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ጠብመንጃ ስላላቸው ነው በቀጥታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን አግኝተው ማነጋገር የቻሉት፡፡ አርሶ አደሮች፣ መምህራን አለያም የአንድ የመንግሥት ኮርፖሬሽን ሠራተኞች ቢሆኑ ኖሮ ገና ሲያስቡት ይከሽፋል፡፡ ምክንያቱም እነዚህኞቹ ጠብመንጃ የላቸውማ!! ዜናውም ያነሱት የደመወዝና የተርበናል ጥያቄ ሳይሆን በአመጽ መግባታቸው የሆነው ለዚህ ነው፡፡

ለማንኛውም ወታደሮቹ የጦሩን ጠቅላይ አዛዥ አስገድደው ለውይይት ማቅረባቸው እሙን ነው። ኢቴቪ ” ከጠቅላይሚኒስትሩ ጋር ተወያዩ” ብሎ በማቅለል በዕቅድ የተያዘ ፕሮግራም እንዳስመሰለው አይደለም። በግዳጅ፣ በጠብመንጃ ለድርድር የተቀመጡበት ነው።።

ጥያቄያቸውም ኢኮኖሚያዊ መሆኑ ተገልጿል። በመግባባትም ወደየካምፓቸው መመለሳቸው ተነግሮናል።

የነዚህ ወታደሮች እጣፈንታና ቀጣይ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ሁለት መላምቶችን ያመጣል። እነዚህን መላምቶችን ከራሳችን ታሪክና ከጎረቤታችን ልምድ አንፃር እንየው፡፡

1ኛ-የ1966ቱ አብዮት በሲቪሉ ማህበረሰብ ሲካሄድ ወታደሩ ጥያቄው ኢኮኖሚያዊ እንደሆነ በመግለፅ እርሱም አመፀ። በመጨረሻ ንጉሱ ደመወዝ ጨመሩለት። ከዚያም ”ወቴ ደመወዟን አስጨምራ ካምፕ ገባች” ብሎ ሲቪሉ ወታደሩን ተነኮሰ። እናም ጦሩ በድጋሚ ጥያቄውን አሻሽሎ የፖለቲካ ስልጣን ጠየቀ። በመጨረሻም 108 ሻለቆች ደርግን መሥርተው መንግሥት ሆኑ።

2ኛ-በ1983 ሻዕቢያ አስመራን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ገንዘብ ቸገረው። እንደ ዱሮው በሽፍታነት ሳይሆን በመንግሥትነት ለወታደሮቹ ደመወዝ መክፈል ነበረበት። ግን አልሆነም። እናም ወታደሮቹ አመጹ። ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ ውጭም ማንንም እንደማያናግሩ በመግለጽ ከነትጥቃቸው ወደ ቤተመንግሥት አቀኑ። አቶ ኢሳያስም (ፈርዶበት ብልጥ ነው) የአስመራ ጎዳናዎችን ያጥለቀለቀውን ሰራዊት ”ስታድየም ሄዳችሁ ጠብቁኝ እዚያ መጥቼ አነጋግራችሁዋለሁ” አላቸው። ሠራዊቱም ወደዚያ ሄደ። ፕሬዚዳንቱም መጣ። ”ደመወዛችሁ መቶ ፐርሰንት ይጨመራል፣ ጥያቄያችሁ ተገቢ ነው” ብሎ ሲናገር የሳባ ስታድየም በጭብጨባ ደነቆረ። ችግሩም በስምምነት ተጠናቀቀ ተባለ። ወደካምፓቸው እንዲመለሱም ታዘዙ። ይሁን እንጂ ይህንን ጥያቄ ያነሱት አመጸኛ ወታደሮች እየተለቀሙ የታሰሩት ወዲያውኑ ነበር። በዚያን አመፅ ላይ ተሳትፋለች የተባለች ወፍ ሳትቀር ከርቸሌ ገባች። እነሆ የኢሳያስ መንበርም እስካሁን እንደጸናች አለች።

ከላይ የተጠቀሱት ማሳያዎች በትናንቶቹ ወታደሮች ላይ ላለመሆኑ ዋስትና የለም፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪል አቋም አያንጸባርቅም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close