Connect with us

Ethiopia

የአቶ ልደቱን ቃለ-መጠይቅ… ከሃዲነቱን ወይስ መከዳቱን የገለጠ…..?!

Published

on

የአቶ ልደቱን ቃለ-መጠይቅ… ከሃዲነቱን ወይስ መከዳቱን የገለጠ…..?!

የአቶ ልደቱን ቃለ-መጠይቅ… ከሃዲነቱን ወይስ መከዳቱን የገለጠ…..?! | አሳዬ ደርቤ 

በእኛ አገር ላይ መንግስት ህዝብን ይጨቁናል፡፡ ህዝብ ደግሞ ግለሰቦችን ያፍናል፡፡ ልደቱ አያሌው ላይ እንደሆነው ማለት ነው!

ለባለፉት 13 ዓመታት ልደቱ አያሌውን ከሚጨቁኑ ሰዎች መሃከል አንዱ እኔ ነበርኩ፡፡ በዚህም የተነሳ የሚጽፈውንም ሆነ የሚናገረውን ነገር አልቀበለውም ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ አንዱን ቅዱስ ሳደርግ አቶ ልደቱን እርኩስ አድርጌው ነበር፡፡

ይሄን ሆኖ ግን የልደቱን የፖለቲካ ብቃትና የአንደበቱን ትባት መካድ አይቻለኝም፡፡ በዘመኔ ካያኋቸው ፖለቲከኞች ሁሉ የልደቱን ያህል ቀልቤን የሚስበኝ ሰው አላጋጠመኝም፡፡

ቸግሩ ግን አፍ አስከፋች ድስኩሩን እስከ መጨረሻም ድረስ ስከታተል ከቆየሁ በኋላ ቻናሌን የምቀይረው ‹‹በተባ አንደበት ላይ ታማኝ ማንነት ካልተጨመረበት ምን ዋጋ አለው?›› በማለት ነው፡፡

ልደቱ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ ብዙ ዓይነት ማንነቶች ተጭነውበታል፡፡ ለማስረጃም ያህል ‹እንደ ወያኔ እና እንደ ከሃዲ› ሲቆጠር መኖሩን ማስታወስ ይቻላል፡፡ እናም በወቅቱ እኒህን ፍርጃዎች ለማስተባበል ቢጣጣርም… የሚጠሉትን ሰዎች ሃሳብ ማስቀየር አልቻለም፡፡ ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያውያኖች አንድን ሰው ስንወድም ሆነ ስንጠላ በሙሉ ልባችን ነው፡፡

የምንወደውን ሰው እስክንጠላው ድረስ ስህተት ቢሰራ እንኳን እያድበሰበስን እናልፈዋለን እንጂ አሳልፈን ለጠላት አንሰጠውም፡፡ የጠላነው ሰው ደግሞ የቱንም ያህል በጎ ነገር ቢሰራ ዳግም ወደ ልባችን ለማስገባት እንቸገራለን፡፡ በተለይ ደግሞ በፖለቲካው ዘርፍ ያሉ ሰዎችን አንዴ ከጠላን እንዲያንሰራሩ ቀርቶ ጥፋታቸውንም የማስተባባያም ሆነ ይቅርታ የመጠየቂያ መድረክ እንዲያገኙ አንፈልግም፡፡

ልደቱንም ያጋጠመው ይሄው ነበር፡፡ መድረክ ላይ ተሰይሞ ኢህአዴጎችን ሲያብጠለጥላቸው ብናይ እንኳን ድርጅቱ እንዳይፈርስበት ፈልጎ እንጂ ለአገር አስቦ አይመስለንም፡፡ እንደ ሚሚ ስብሐቱ የምንቆጥረው በርካቶች ነበርን፡፡

ይሄም ሆኖ ግን አቶ ልደቱ አያሌው የጎደፈ ስሙን ይዞ ከፊታችን ገለል በማለት ፈንታ ጥንካሬን እና ‹አልሸነፍ-ባይነትን› ደርቦ የሃገራችን ፖለቲካ ላይ የሙጥኝ በማለት ለባለፉት 13 ዓመታት በተፈቀደለት ልክ ሲንቀሳቀስ ነበር፡፡

ከወራት በፊት ግን ‹‹አሁን ያለው የፖለቲካ አየር ከእኔ ጋር አብሮ የሚሄድ ስላልሆነ ላልተወሰነ ጊዜ ከየትኛውም አይነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ ራሱን አግልያለሁ›› በማለት ገልጾ ነበረ፡፡ ከአብዛኛው ህዝብ ያገኘው ምላሽ ‹‹ካገለልንህ እኮ ቆየን!›› የሚል ቢሆንም!)

በቅርቡ ደግሞ የግንቦት ሰባት አመራሮችን ለመቀበል በተደረገው ዝግጅት ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑን በማሞገስ ፈንታ ልደቱን የሚወቅስ መንጋ ከታዬ በኋላ… አቶ ልደቱ በሚዲያዎች በኩል ብቅ በማለት ‹‹ለቅንጅት መፍረስም ሆነ በወቅቱ ለተከሰተው ደም መፋሰስ ተጠያቂ መሆን ያለበት ማን ነው? በሚል ጉዳይ ላይ ከፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመሟገት ፋይሉ እንዲዘጋ እፈልጋለሁ›› በማለት አሳሰቡ፡፡ ይሄንንም እድል እንዲሰጧቸው ለቴሌቪዥንና ለሬድዮ ጣቢያዎች ጥያቄውን አቀረበ፡፡

የአማራ ቴሌቪዥንም የአቶ ልደቱን አቤቱታ በመቀበል ሁለቱንም በግንባር ለማወያየት ማሰቡን ገለጸ፡፡ ሆኖም ግን ይሄን ባለ ማግስት ‘ፕሮፌሰሩ ባለፈ ጉዳይ ላይ የምነታረክበት ትርፍ ጊዜ የለኝም’ ስላሉኝ አንድኛውን ወገን ብቻ ማናገር አልችልም›› በማለት ኢንተርቪው የማድረግ እቅዱን ሰረዘ፡፡

ይሄም ጉዳይ በግሌ ለልደቱ ያለኝን አተያይ እንዲከልስ አደረገኝ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ አንደኛ ነገር አቶ ልደቱን እንዲጠላቸው ካደረጉኝ ተጨባጭ መረጃዎች ይልቅ ተራ አሉባልታዎች መብዛታቸው… በሌላ መልኩ ደግሞ ‹ከሃዲ› እየተባለ የሚወቀሰው ግለሰብ በራስ-መተማመን ውስጥ ሆኖ ‹‹ስከሰስበት የኖርኩት ወንጀል ትክክል ስላልሆነ ከሳሼ ጋር በመሟገት ስሜን ማንጻት ካልሆነም ደግሞ ይቅርታ ማለት እፈልጋለሁ›› ሲል ይሄኛው አካል ማፈግፈጉ ጥርጣሬ እንዲጭርብኝ ስላደረገኝ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ቅዳሜ ምሽት ላይ የቴሌቪዥኔን ቻናል ስቀያይር አቶ ልደቱን ዋልታ ቴሌቪዥን ላይ አገኘኋቸው፡፡ ኢንተርቪው የሚያደርጋቸው ጋዜጠኛም ፕሮፌሰሩን ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ከገለጸ በኋላ ይጠይቃቸውና ይሟገታቸው ያዘ፡፡

እውነት ለመናገር ጋዜጠኛ ‹ስሜነህ ባይፈርስ› የሚያቀርብላቸው ጥያቄዎች የሚያፋጥጡና የሚያስደነግጡ ቢሆንም አቶ ልደቱ ግን አንድም ቦታ ላይ ሲደናገራቸውም ሆነ መልስ ሲያጥራቸው አልታዩም፡፡ ኩልል ባለ አንደበት ‹‹ስለቅንጅት አፈራረስ፣ ስለ ማህተሙ ክስ፣ ወያኔ እንዴት እንደተባሉ፣ ከቅንጅት እንዴትና ለምን እንደተባረሩ፣ በወቅቱ ሲያነሱት የነበረው ሃሳብ ትክክል ሆኖ ሳለ እንደት እንደተወነጀሉበት፣ የስም ማጥፋት ዘመቻው በምን አይነት መልኩ እንደተካሄዴ፣ የእሳቸውን ስም የሚያጠፋ በርካታ ሚዲያ ባለበት ሁኔታ የማስተባብሉበት አንድም ሚዲያ ማግኘት ስላለመቻላቸው፣ የተካዱት እሳቸው ሆነው ሳለ ‹ከሃዲ› የሚል ስም እንዴት እንደወጣላቸው….›› በማብራራት የጋዜጠኛውንም ሆነ የእኔን ጥያቄዎች ያብራሩ ያዙ፡፡

የምሽቱ ቃለ-መጠይቅ ለ50 ደቂቃ ያህል አየር ላይ ከዋለ በኋላ በማግስቱ ደግሞ ቀሪው ክፍል ቀረበ፡፡ በቀጣዩ ምሽትም ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች ከሃዲነታቸውን ሳይሆን ንጹህነታቸውን ይፋ ያወጡ ነበሩ፡፡ በበቂ ዝግጅት ሊሟገታቸው የቀረበው ጋዜጠኛም ወደ መጨረሻው አካባቢ እጅ ለመስጠት ተገደደ፡፡ እኔም እንደዚያው!

አቶ ልደቱም…. ለባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ለሃገራችን ፖለቲካ መሻሻል ሙሉ ጊዚያቸውንና ጉልበታቸውን በመሰዋት ያደረጓቸውን መልካም ነገሮች በማውሳት… በፈጸምኳቸው አበርክቶቶች የሚገባኝን ያህል ክሬድትና አድናቆት ባለገኝ እንኳን እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሬ ለስደት ልዳረግባቸው አይገባም!›› በማለት አሳስበው ንግግራቸው አጠናቀቁ፡፡

የኔም ሃሳብ ሲጠቃለል የአቶ ልደቱ ማብራሪያ ከማሳመንም አልፎ አሳምሞኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ እራሴን ስገመግም ለአቶ ልደቱ ያለኝ አሉታዊ አተያይ በራሴ ጭንቅላት ሳይሆን በሌሎች ጭንቅላት የታሰበና መንጋነቴን የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ለባለፉት ዓመታትም በተራ ሃሜትና የሚጠሏቸው ሰዎች በጻፉት ድርሰት በመመራት በጭንቅላቴ ውስጥ መልካም ስብዕናቸው እንዳያንሰራራ ከመጠን በላይ ስጨቁናቸው መኖሬን ተረድቻለሁ፡፡

አሁን ላይ ግን የአቶ ልደቱ ጥፋት ከሃዲነታቸው ሳይሆን ብቃታቸው መሆኑ ግልጽ ሁኗል፡፡ ስለሆነም በግሌ አቶ ልደቱን ይቅርታ ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ፡፡ እናንተ ደግሞ ቃለ-መጠይቁን አይታችሁ የራሳችሁን ፍርድ እንዲትሰጡ እጋብዛለሁ፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪል አቋም አያንጸባርቅም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close