Connect with us

Ethiopia

እንኳን ደስ አላችሁ!…

Published

on

እንኳን ደስ አላችሁ!...

እንኳን ደስ አላችሁ!… | (ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ)

እንኳን ደስ አልዎት ዶ/ር ዐብይ አሕመድ ዓሊ፤
እንኳን ደስ አልዎት አቶ ደመቀ መኮንን ሐሰን።

የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ሊቀመናብርት ሆናችሁ በድጋሚ በመመረጣችሁ እንደአንድ ዜጋ መደሰቴን ስገልጽላችሁ ከፍ ያለ ኩራት ይሰማኛል።

ለምን ተደሰትክ በሉኝ?…
ለምን ተደሰትኩ?..

በአጭሩ ጀምራችሁ ያልጨረሳችሁት ቀሪ ሥራ አለ ብዬ ስለማምን ነው። ባለፉት ስድስት ወራት፤ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተሰሩ ሥራዎችን የሚያስንቁ አስገራሚ ተግባራት በማከናወናችሁ ቀና ብለን አጨብጨብንላቹሀል። በዚህ ሥራችሁ ደጋፊውንም ተቀናቃኙም ረክቷል። ከትንሽ እስከ ትልቅ በፍቅር መግዛት ችላቹሀል። ይህ ትልቅ መታደል፣ ትልቅ ፀጋ ነው።
በአንጻሩ የጎደሉ፣ አንዳንዶቹም ችላ የተባሉ ነገሮች ነበሩ፣ አሁንም አሉ።

ለምሳሌ
የሰኔ 16 የተቀነባበረ የቦምብ ጥቃት ማስተር ማይንዱን አላገኘንም በሚል ዙሪያ ጥምጥም የመሄዳችሁ፣ ላኪዎቹን አስቀምጣችሁ፣ ተላላኪዎችን ብቻ ለፍርድ ስለማቅረባችሁ የሚነገረው ትርክት፤ በእውነቱ አልጣመንም። ስለነገሩም ይፋዊ ማብራሪያ ሳይሰጥ በዝምታ ወራት መፈርጠጣቸውም ደስ የሚል ስሜትን አይሰጥም።

እስቲ አስቡት!..አንድ ዕለት የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና ሌሎች ሠራተኞች መንግሥት ባለበት አገር፤ በጠራራ ጸሐይ ተገደሉ። ወሬው የሚድያ የአንድ ሰሞን ቀለብ ሆኖ ቀረ። መንግሥትም እንደተለመደው “ሁኔታው ተጣርቶ ለሕዝብ ይገለጻል” አለና በዝምታ ተቆለፈ። ቀስ በቀስ ነገሩ የተረሳ መሰለ። ግን እንዴት ሰውን ያህል ክቡር ህይወት የተገበረበት ወንጀል በዝምታ ሊዳፈን ይችላል?…ለምን?..ለማንስ ጥቅም ይህ ይሆናል?

እንቀጥል። ነፍሰ በላ፤ አስቀያሚ ዘር ተኮር ግጭቶች ጋር ተያይዞ ሚልየኖች ዋጋ የሚከፍሉበት አገርም ገንብተናል። ሰዎች በቤተእምነታቸው ሳይቀር የሚገደሉበት አሳፋሪ፣በድንጋጤ አፍን የሚያሲዝ ታሪክ በእኛ ዕድሜ እያየን ነው። በሶማሌ ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በድሬደዋ፣… ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ዘር ተኮር ጥቃቶች ተራ ገጠመኞች አለመሆናቸውን መንግሥታችንም ጠንቅቆ ያውቃል። ግጭቶች በተነሱ ቁጥር “ይህ ድርጊት የሶማሌን ሕዝብ፣… ይህ ድርጊት የኦሮሞን ሕዝብ…አይወክልም” እየተባለ ውጫዊ ምክንያት ለመፈለግ የሚደረገው ሩጫና ትርምስ እንደዜጋ ሲያሳዝነን የቆየ ጉዳይ ነው። እነዚህን ግጭቶች በፍጥነት ለመቆጣጠር መንግሥት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን በዚያው ልክ በተዋረድ ተጠያቂነትን ለማስፈን አለመቻሉ አሳዛኝ ነበር። እነዚህ ግጭቶች በሺ ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞትና እንዲሁም በሚሊየን የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ከሞቀ ቤት ንብረታቸው ተገድደው ለመፈናቀል ምክንያት መሆናቸውን የምናስታውሰው በታላቅ የሐዘንና የቁጭት መንፈስ ውስጥ ሆነን ነው።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ራሳቸውን ስለማጥፋታቸው የፓሊስ ምርመራ አሳይቷል ስለመባሉ ሰምተናል። ግን ጥያቄ አለን!…ፋይሉ በዚሁ ይዘጋል ወይንስ ይቀጥላል? ሰውየው ለዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ያደረሳቸው መነሻ ምክንያት ምንድነው የሚለው በተጨባጭ ተተንትኖ ሊመለስልን ይገባል።

ሌላው የእነአጅሬ ዝም መባልን የሚመለከት ነው። አዎ!..የሕዝብን የልማት መዋጮ ሳይቀር ቀርጥፈው የበሉ ሌባ ሹማምንትን አይቶ እንዳላየ የማለፍ አዝማሚያ አሁንም አለ። ሰሞኑን በኢህአዴግ ስብሰባ ላይ እንደተሰማው ዓይነት “ከአሁን በኃላ ሌቦችን አንታገስም” አይነት መፈክር ጉንጭን ከማልፋት የዘለለ ትርፍ የለውም። በቃ!..ሕግናሥርዓት ባለበት አገር ምንም መማማል አያስፈልግም። ወንጀለኛውን ለቅሞ ፍርድ ቤት መገተር ነው። ሥራው ያውጣው ብሎ ጣጣውን ለሕግ ሥርዓቱ መተው ነው።

እናም መንግሥታችን በቅድሚያ ጉያው ሥር የበቀሉ ሌባ ሹማምንቶችን አራግፎ ለፍርድ በማቅረብ ከገባበት የዝምታ ባህር ዋኝቶ ሊወጣ ይገባል። የተከበሩ ሊቃነመናብርቶች በዚህም ረገድ አርኪ ድል ሊጎናፀፉ ይገባል እላለሁ።

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close