Connect with us

Art and Culture

የፈረንጁ መምህር ጥያቄዎች

Published

on

የፈረንጁ መምህር ጥያቄዎች

የፈረንጁ መምህር ጥያቄዎች |  ታገል ሰይፉ በድሬቲዩብ)

አሁን ስድስት ኪሎ በሚገኘው የአዲሳባ ዩኒቨርሲ ውስጥ ነን፡፡ ዓመተምህረቱን ለጊዜው አልመዘገብነውም፡፡ ነገር ግን እነጀማነሽ ሰለሞን ተማሪ፤ እነ ደበበ ሰይፉ ደግሞ አስተማሪ በነበሩበት ወቅት ነው፡፡ ክፍለ ጊዜው ግን የአቶ ደበበ አልነበረም፡፡ የአንድ ፈረንጅ መምህር እንጂ…

በወቅቱ ክፍለጊዜውን የተካፈሉት ተማሪዎች መምህሩ ሰዓታቸውን አክብረው መድረሳቸውን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም እንደገቡ ማስተማር መጀመራቸውን ለማወቅ ግን በጣም ዘግይተዋል፡፡

ወደው አይደለም፡፡ ካሁን አሁን አስተማሩን በማለት አቆብቁበው ሲጠብቋቸው ዕቃ እንደጠፋበት ሰው ወለሉ ላይ አቀርቅረው ጥቂት ከተንጐራደዱ በኋላ ‹‹እስቲ ባማርኛ ቋንቋ ቀጭን ሴትን የሚያወድስ ወይም የሚያቆላምጥ አንድ ቃል ፈልጉልኝ››
በዚያን ሰዓት ሁለት ነገር ተፈጠረ ተጠራጣሪዎቹ ተማሪዎች ጥያቄውን ከሰሙ በኋላ በጥርጣሬ ኮስተር አሉ፡፡ በነሱ ቤት ይህ ፈረንጅ በአንዲት ሀበሻ ፍቅር የሚነደፍበት ምክንያት ካገኘ በኋላ ውበትዋን የሚገልፅበት አማርኛ አጥቶ ተቸግሯል፡፡

የዋሆቹ ተማሪዎች ደግሞ በየዋህነት ፈገግ አሉ፡፡ አንዳንድ መምህራን ማስተማር ከመጀመራቸው በፊት ክፍሉን ለማነቃቃት ለተማሪዎቻቸው ከሚያቀርቧቸው አዝናኝ ዓይነት ጥያቄዎች አንዱ እንደተወረወረላቸው አስበው ነው፡፡

እናም የጥያቄውን አዝናኝነት በሚመጥን ፈገግታ ፈታቸው እያበራ ቀጭን ሴትን አሳምሮ የሚገልጥ የተለየ ቃል ፍለጋ በተለያየ ተመስጦ ተበታተኑ፡፡

ጥቂት ደቂቃዎች በዚህ ሁኔታ አለፉ፡፡ አሁን ከተበተኑበት ተመስጦ ባዶ ሃሳባቸውን ተመልሰዋል፡፡ ከዚያም በ‹‹እንዴት ይጠፋናል›› ስሜት እርስ በርሳቸው ተያይተዋል፡፡

ያችን ቃል ወደተራቡት የመምህሩ ዓይኖች ግን ቀና ለማለት አልደፈሩም፡፡ ይልቁንስ ባዶው አየር ላይ አፍጥጠው ወጥመድ ውስጥ የገባች ድንቢጥ መሰሉ፡፡

እዚያ ወጥመድ ውስጥ ከገቡት ድንቢጦች መሃል አንድ እሳት የላሰ ድንቢጥ ብቻ ከእሳቱ ተሰማ አንደበት የሰማውን የፍቅር ዘፈን አስታውሶ እጁን አነሳ፡፡

‹‹አገኘህ?›› አሉት መምህሩ
‹‹አዎ!?››
‹‹ንገረኝ››
‹‹ችቦ አይሞላም ወገቧ››
‹‹ምናልክ!?›› አሉት ነጭ ግንባራቸውን ስብስብ አድርገው፡፡

ምን እንዳለ ደግሞ ነገራቸው፡፡ እንደዚህ ያለ ረጅም ቃል በአማርኛ ቋንቋ ውስጥ መኖሩን የተጠራጠሩት እኒህ ፈረንጅ ደግመው ጠየቁት ‹‹በርግጥ ይሄ አንድ ቃል ነው?›› በማለት፡፡

አሁን እሳቱ ጠፍቶ አመዱ ቡን አለ፡፡ ከሶስት ራሳቸውን የቻሉ ቃላት ተፈትሎ የተሰራ የአማርኛ ሀረግ መሆኑን እያመነታ ገለፀላቸው፡፡

ብዙዎቹ ተማሪዎች የመምህሩ ጥያቄ የቀጭን ሰው ክብደትን ያክል ቀላል እንዳይደለ ልብ ያሉት ይሄን ጊዜ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጥያቄው የትምህርቱን መጀመር እስካሁን አላመላከታቸውም፡፡

ቅድም ፈገግ ያሉት ተማሪዎችም የጥያቄው አዝናኝነት ቀዝቀዝ እያለባቸው መጣ፡፡ አንዳንዶቹ በጭንቀት ወደ ኮርኒሱ ቀና አሉ፡፡ ሌሎቹ በሃፍረት ወደ ጠረጴዛዎቻቸው አቀረቀሩ፡፡

የተቀሩት በክፍሉ መስኮቶች አሻግረው ወደውጭ ይመለከቱ ጀመር፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በወፍራም ሰዎች መካከል የሚርመሰመሱ ቀጫጭን ሰዎች ይታዩዋቸዋል፡፡ እነኚያን ቀጫጭን ፍጥረቶች ለማድነቅ የተፈጠረ አንድ አማርኛ እንኳ አብሯቸው እልፍ ሲል አለመመልከታቸው ከፋ እንጂ!…

በዚህ እየተገረሙ ሳሉም ‹‹በቃ ተውት›› የሚለው የመምህራቸው እንግሊዝኛ ከንቱ ፍለጋቸውን አስተዋቸው፡፡
እናም አሻቅበው ከተሰቀሉበት ኮርኒስ አወረዳቸው አቀርቅረው ከተደፉበት ጠረጴዛ አነሳቸው … ተወርውረው ከወጡበት መስኮት መለሳቸው…

ያም ሆኖ ታዲያ ፈረንጁ መምህር ገና በደንብ ያልወረደ በደንብ ያልተነሳ እና በደንብ ያልተመለሰ ነገር የቀራቸው ይመስል እንደገና አቀርቅረው ከተንጐረደዱ በኋላ ‹‹እስቲ ደሞ አሁን በአማርኛ ቋንቋ ቀጭን ሴትን የሚያንኳስስ እና የሚሰድብ ቃል አምጡልኝ››

የሚገርም ነው፡፡ ይሄን ቃል ለማምጣት የተማሪዎቹ ዓይኖች እንደ ቅድሙ ወደጣራው አልወጡም ወደጠረጴዛው አልወረዱም ወደደጅም አልበረሩም፡፡

ልክ የፊሽካ ድምፅ ሲሰማ ፈጥኖ እንደሚንቀሳቀስ የጅምናስቲክ ቡድን በአንድነት እና በቅፅበት እጆቻቸውን ሽቅብ ወረወሩ፡፡
መምህሩ እጃቸውን ያላወጡ ተማሪዎች አለመኖራቸውን ካረጋገጡ በኋላ ወደላይ ከተመዘዙት ጣቶች መካከል ለአንዳንዶቹ እነኚያን ቃላት ይጠቁሟቸው ዘንድ ዕድል ሰጧቸው፡፡

‹‹አንተ››
‹‹ስልባቦት››
‹‹አንቺስ››
‹‹ሲምቢሮ!››
‹‹እዛጋ!››
‹‹ኮሳሳ!››
‹‹እዚህስ!››
‹‹ቀጫጫ››
‹‹በቃ!››
‹‹ሌላምአለ››
‹‹ይበቃል! ይበቃል››

በርሳቸው ይበቃል የወረዱት የዋህ እጆች ማስታወሻ ደብተሮቻቸውን መግለጥ ጀመሩ፡፡ በነሱ ቤት አሁን መምህራቸው የክፍሉን መነቃቃት ካረጋገጡ በኋላ አዝናኝ ጥያቄያቸውን አብቅተው የዕለቱን ትምህርት ለመጀመር ተዘጋጅተዋል፡፡

መምህሩ ግን ገና አልበቃቸውም አሁንም በክፍላቸው ወለል ላይ ጥቂት ከተንጐራደዱ በኋላ ከተደፋ አንገታቸው ቀና በማለት ‹‹እስቲ ደሞ አሁን ወፍራም ሴትን የሚያሞግስ ወይም የሚያቆላምጥ አንድ አማርኛ ፈልጉልኝ››

አሁንም ጭንቅ ሆነ፡፡ ጣራው ታየ ጠረጴዛው ተዳሰሰ፡፡ ደጁ ተፈተሸ በዚያን ሰዓት በቅጥር ግቢው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ከሚሉት ቀጫጭን እግሮች መካከል ጐልተው የሚታዩዋቸው ብዙ ወፋፍራም ሰዎች ነበሩ፡፡

ወፍራምነታቸው አሳምሮ የሚገልጥ አንድ ቃል ማግኘት ከወፍራም ሰው ክብደት በላይ ከብዶ ተሰማቸው እንጂ…
በዚህ እየተገረሙ ሳለም‹‹እሱን ተውትና …›› የሚለው የመምህራቸው ድምፅ ካሻቀቡበት አወረዳቸው ከተደፉበት አነሳቸው ከወጡበት መለሳቸው…

‹‹እሱን ተውትና ወፍራም ሴትን የሚያንኳስስና የሚሰድብ አንድ ቃል አምጡልኝ፡፡ ››
ተማሪዎቹ እንደፈረደባቸው እጆቻቸውን ሽቅብ ወረወሩ መምህሩም እንደገና ከእነኛ የትየለሌ እጆች መካከል ለአንዳንዶቹ አንዳንድ እድል ሰጧቸው፡፡
‹‹አንቺ››
‹‹ወደል››
‹‹አንተስ››
‹‹ድብልብሌ››
‹‹እዚህ ጋ››
‹‹ዘረጦ››
‹‹እዛስ››
‹‹ግንድ እግር››
‹‹በቃ››
‹‹ሌላም አለ መምህር››
‹‹ይበቃል ይበቃል››

በፈረጁ ይበቃል የወረዱት የዋህ እጆች ማስታወሻ ደብተራቸውን ገለጡ፡፡ ትምህርቱ ግን አሁንም አልተጀመረም፡፡
‹‹አያችሁ…የማድነቅ ባህል ስለሌላችሁ ቋንቋችሁ እንኳን የበለፀገው በስድብ ቃላት ነው›› በሚለው የመምህሩ የመጨረሻ ቃል ተደመደመ እንጂ፡፡ ….

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close