Connect with us

Ethiopia

ኢሳትና የብሄር ፖለቲካው ጦርነት

Published

on

ኢሳትና የብሄር ፖለቲካው ጦርነት

ኢሳትና የብሄር ፖለቲካው ጦርነት | ፀጋው መላኩ

የአማራ ብሄርተኞችና ኢሳት

ኢሳትና የብሄር ፖለቲከኞች ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡ ይህ ውዝግብ እየጦዘ ሄዶ በስተመጨረሻ ከሰሞኑ በጣቢያውና በኦሮሞ ፖለቲኞች መካከል ሲፈነዳ ታይቷል፡፡ ሁኔታው ድንገት የተከሰተ ሳይሆን ከመሰረታዊ የአቋም ልዩነቶች ጭምር የመነጨ መሆኑን ከሌሎች ብሄር ተኮር አደረጃጀቶችም ጭምር ጋር በማያያዝ እንመለከታለን፡፡

የአማራ ብሄርተኞች በኢሳት ላይ ሰፊ ዘመቻን ከከፈቱ ሰነባብተዋል፡፡ አንዳንዶቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ጣቢያውን “ፀረ አማራ” በማለት በግልፅ የፍርጃ ዘመቻን ሲከፍቱ ታይተዋል፡፡ ሁኔታው በሚገባ ሲመረመር አክቲቭስቶቹ በሚዲያው ላይ የከፈቱት ዘመቻ ያዝ ለቀቅ የሚታይበት ሳይሆን እጅግ የተቀናጀና ተከታታይነት ያለው ነበር፡፡

በእነዚህ የሚዲያው ተቃዋሚዎች ከሚነሱት መሰረታዊ የተቃውሞ ቅሬታዎች መካከል፤ “ጣቢያው ስለአማራ ሰቆቃ አይዘግብም፣ ቢዘግብም አቀራረቡ አሉታዊ በሆነ መልኩ ነው፣ ፀረ አማራ ኃይሎችን መድረክ እየሰጠ የአማራ ብሄርተኝነትን ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ለመቸለስ ተግቶ ይሰራል” የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ሌላኛው ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው ጭብጥ፤ ጣቢያ የግንቦት ሰባት ልሳን የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ በአማራ ብሄርተኛ ኃይሎችና በአርበኞች ግንቦት ሰባት መካከል ከባድ የሆነ የሀሳብ ፍለሚያ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

የአማራ ብሄርተኞች “ አማራ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ሲታገል ላላፉት ሁለት አስርት ዓመታት ህዝቡ ላይ እስከ ዘር ማጥፋት የዘለቀ የተቀነባበረ ጥቃት የደረሰበት በኢትዮጵያዊነቱ ሳይሆን በአማራነቱ ነው” በማለት የአማራ ህዝብ ብሄርተኝነቱን አጠናክሮ ራሱን በአማራነት በማደራጀት ህልውናውን ማስጠበቅ ያለበት መሆኑን አጥብቀው ይከራከራሉ፡፡

አማራው ካለፈበት ሰፊ የሀገር ምስረታ (Nation building) ሥነ ልቦና እና ታሪካዊ ሂደት አኳያ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ብሄር ዘለል ፓርቲዎችን የማስተናገድ መደላድልም ያለው መሆኑ እሙን ነው፡፡ ከእዚህ ብሄር ዘለል ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች መካከል የሚጠቀሰው ደግሞ ግንቦት ሰባት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በተለይ “ከዚህ በኋላ አማራ በኢትዮጵያ አንድነት ስም መስዋዕትነት መክፈል የለበትም” የሚል የፀና አቋም ላላቸው የአማራ ብሄርተኛ አቀንቃኞች ፈፅሞ የማይዋጥ ሆኖ ታይቷል፡፡

ግንቦት ሰባትም ቢሆን ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ከአዲስ አበባው አቀባበል ቀጥሎ ተከታታይ ስብሰባዎችን እና ውይይቶችን ያካሄደው በአማራ ክልል ከተሞች ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በአማራ ብሄርተኞችና በግንቦት ሰባት የአንድነት ኃይሎች መካከል የነበረውን የከረረ ልዩነት የበለጠ አጡዞታል፡፡

ኢሳት “ለኢትዮጵያ የብሄር ፖለቲካ አይጠቅምም” በማለት በግልፅ ያወግዛል፡፡ አሁን ያለው የብሄር ፌደራሊዝም አወቃቀርም እንዲቀየር አጥብቆ የሚሰራ መሆኑንም በተደጋጋሚ ይናገራል፡፡

ይህ አቋሙ ከብሄርተኞች ጋር ሰፊ የሚዲያ ጦርነት ውስጥ ከቶታል፡፡ በተለይ ለግንቦት ሰባት ከሚሰጠው የሚዲያ ሽፋን ጋር በተያያዘ በአማራ ብሄርተኞች በኩል ዘመቻ እንዲከፈትበት አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ በአዲሱ የአማራ ብሄርተኛ አቀንቃኞችና እንደ ግንቦት ሰባት ባሉት የአንድነት ኃይሎች መካከል ያለው የትግል ፍትጊያ “የብሄር ፖለቲካ ለኢትዮጵያ አይጠቅምም የሚል የፀና አቋም ላለው ኢሳት በሚዲያው ጦርነት ውስጥ ፍልሚያ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል፡፡

በአማራ ብሄርተኞች በሰፊው እየተሰራበት ያለው የአማራ የተቀናጀ ሚዲያን እውን የማድረግ ተግባር ወደ መሬት ለማውረድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በእንቅስቃሴው ዙሪያ ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ መሰል እና ሌሎች ሚዲያዎች መበራከታቸው ለህብረተሰብ ግንባታ ሊኖራቸው የሚችለው ሚና ሰፊ ቢሆንም፤ የማህበራዊ ሚዲያው የፕሮፖጋንዳ ጦርነት ተመልሶ በዋናዎቹ ሚዲያዎች የሚደገም ከሆነ ግን የሀገሪቱን ፈተና በእጅጉ ያከብደዋል፡፡ ከሰሞኑ በኢሳትና በኦኤምኤን (OMN) መካከል የሚታየው ዲንጋይ መወራወርም የዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

የትግራይ አክቲቪስቶችና ኢሳት

ኢሳት በትግራይ አክትቪስቶች በኩል የሚታይበት የጥላቻ አይን ወደር የለውም፡፡ በተለይ የህወሓት አፍቃሪና ደጋፊ የሆኑ የትግራይ አክቲቪስቶች ብሄርተኞች ከጣቢያው ጋር ሲያደርጉት የነበረውና እና እያደረጉት ያለው የፕሮፖጋንዳ ፍለሚያ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

ቀደም ባለው ፀረ ህወሓት ትግል የሀገሪቱ የፖለቲካ የሙቀት መጠን ከፍ ባለ ቁጥር ይህ የፕሮፖጋንዳ ጦርነትም እንደዚሁ ሲጋጋል ቆይቷል፡፡ “ጣቢያው በአንድ ወቅት በትግራይ ህዝብ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ እዲካሄድ በግልፅ የክተት አዋጅ አውጇል” በሚል ጠበቅ ያለ ክስ ሲሰማበትም ቆይቷል፡፡

ጉዳዩን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያጤነው የህግ ተጠያቂነትም ጭምር በማንሳት ጣቢያው እንደዚጋና ኃላፊዎቹና ጋዜጠኞቹም ጭምር በህግ እንዲጠየቁ በውጭና በሀገር ውስጥ ባሉ የትግራይ ሰዎች አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረው ነበር፡፡ የቪዲዮና የድም ማስረጃ ማሰባሰብ ስራዎች ሳይቀሩ ሲሰሩ የነበረበት ሁኔታ ነበር፡፡

ሆኖም በመጨረሻ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ያም ሆኖ በህወሓት አፍቃሪያን፣ በሌሎች የትግራይ አክቲቭስቶችና ብሄርተኞች ኢሳት የሚታይበት አይን የጠላትነት ነው፡፡

የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ኢሳት

ኢሳትና የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች ያን ያህል የከረረ ፀብ የታየባቸው ሁኔታ አልነበረም፡፡ ግንኙነቱ ሳይሞቅም ሳይበርድም በደፈናው ሲቀጥል ቆይቷል፡፡ ጣቢያው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስትና ስርዓት ለማስወገድ በነበረው ሂደት ከምስረታው ጀምሮ የኦሮሞን የትግል እንቅስቃሴ በስፋት ሲዘግብ ቆይቷል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ከለውጡ በፊት ለርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞችንም ጭምር ሰፊ መድረክ በመስጠት ያላቸውን አቋምና ሀሳብ እንዲያስረዱም ጭምር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በጣቢያው ራሳቸውን የበለጠ ካስተዋወቁት የኦሮሞ አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች መካከልም ጃዋር መሀመድ ተጠቃሽ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ የቴሌቪዥን ጣቢያም(OMN) እንዲቋቋም ዋነኛ የተነሳሽነት ሞዴልም ሆኖም አገልግሏል፡፡

በሀገሪቱ የፖለቲካ የለውጥ አየር መንፈስ ሲጀምርና በውጭ ያሉ ሚዲያዎች በሀገር ውስጥ ገብተው የሚሰሩ መሆናቸው ከተገለፀ በኋላም ኢሳት አቶ በቀለ ገርባን፣ዶክተር መረራ ጉዲናን እና ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ሳይቀር ሰፊ የቃለ መጠይቅ ሽፋንን ሲሰጥ ታይቷል፡፡

ሆኖም በቅርቡ በቡራዩ ከተማ ከተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አምስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ባወጡት መግለጫ ኢሳትን በስም ጠርተው በፅኑ ማውገዛቸው የኢሳትን እና የብሄርተኛ ፖለቲከኞችን የአቋም ልዩነት ግልፅ አድርጎታል፡፡

አምስቱ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ማለትም የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣የተባበሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦሮሚያ ነፃነት አንድነት ግንባር፣የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር እና የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረንስ በጋራ ባወጡት መግለጫ ኢሳትን በስም በመጥቀስ “ፀረ ኦሮሞ ሚዲያ” ከማለት ባለፈ በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሀሰት ፕሮጋንዳ ዘመቻ ማሰራጨት ከጀመረ የሰነባበተ መሆኑንም በመግለፅ፤ በተለይ ቄሮን እንደ ጭራቅ በመሳል በስም ማጥፋት ዘመቻ ውስጥ የገባ መሆኑን የድርጅቶቹ መግለጫ ያመለክታል፡፡

በቡራዩ የተፈጠረውንም ችግር በተመለከተ የዘር ማጥፋት አስመስሎ በመዘገብ ጭምር በጣቢያው ላይ ክስ አሰምተዋል፡፡

ከመግለጫው በኋላ ጉዳዩን አስመልክቶ በኢሳት በኩል ተደጋጋሚ ውይይቶች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በድርጅቶቹ በኩል በዚህ ደረጃ የተሰጠው መግለጫም ያሳዘናቸው መሆኑን ተጋባዥ እንግዶችና የጣቢያው ጋዜጠኞች ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡ በትግሉ ሂደት ለኦሮሞ ፖለቲከኞች ሰፊ የሚዲያ ሽፋንን በመሰጠት ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን የገለፁት የውይይት መድረኩ ተሳታፊ ጋዜጠኞች፤ “ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” በሚል ስሜት ሰፊውን የውይይት ጊዜ ወስደውታል፡፡

በቀና ልቦና ቢሆን ኖሮ፤ ችግር ካለም በመግለጫ በሚዲያው ላይ ዘመቻ ከመክፈት በቀጥታ ለድርጅቱ ደብዳቤ በመፃፍ እርምት እንዲወሰድ መወያየት ይቻል ነበርም በማለት ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የኢሳት ቤተኞች እንደነበሩ ያመለከቱት ተወያዮቹ፤ ጣቢያው በርካታ ተቃውሞዎች እየቀረበበትም እንኳን ለጃዋር መሀመድ ሳይቀር ሰፊ የአየር ሰዓት ሲሰጥ የቆየበትን ሁኔታ አስታውሰዋል፡፡

ኢሳትና የብሄር ፖለቲካ

ኢሳት በተደጋጋሚ እንደሚገልፀው ጣቢያው የሚሰራው ለኢትዮጵያ አንድነት እንጂ ለብሄር ፖለቲካ አይደለም፡፡ ድርጅቱም አሁን ያለው ብሔርን ያማከለ ፌደራሊዝም እንዲከለስ ፀኑ ፍላጎት ያለው መሆኑን ሲገልፅ ቆይቷል፡፡

ከሰሞኑ በዚሁ ዙሪያ ውይይት ያደረጉት የጣቢያው ጋዜጠኞች፤ አሁን በሚዲያው ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄዱ ያሉት ብሄርተኞች፤ የኢትዮጵያ አንድነት ትንሳኤ ሲቃረብ በሰብአዊ ጋሻነት የሚጠቀሙበት የዘር አደረጃጀት ምሽግ የሚናድ መሆኑ ስለገባቸው ነው በማለት ወቀሳቸውን ይሰነዝራሉ፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close