Connect with us

Ethiopia

ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ኳስ ተጫዋች ተሽጦ ቢጫወት ዶክተር አብይ ለእንግሊዝ አሊያም ለአሜሪካ የሚጫወት መሪ ነበር፤

Published

on

ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ኳስ ተጫዋች ተሽጦ ቢጫወት ዶክተር አብይ ለእንግሊዝ አሊያም ለአሜሪካ የሚጫወት መሪ ነበር፤

ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ ኳስ ተጫዋች ተሽጦ ቢጫወት ዶክተር አብይ ለእንግሊዝ አሊያም ለአሜሪካ የሚጫወት መሪ ነበር፤ የታላቅ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑ ህዝቦች ቢወልዱንም አሁን ግን እንደህዝብ ዲቪዚዮናችን ወርዶ ከደረጃ በታች የምንጫወት ሆነናል፡፡ ***** ከስናፍቅሽ አዲስ፤

ሱስ አለብን፤ ኦቦ ለማ እንዳሉት ኢትዮጵያዊነት ሱስ ቢሆንም አዲሱ ትውልድ ደግሞ ያለመደማመጥ ሱስ አለበት፤ ነገን ያለማየት ሱስ አለበት፤ አሁን ባይ ራስ ወዳድ የመሆን አራራ አለበት፡፡ እኔም የዚህ ትውልድ አባል ነኝ፡፡

ሁላችንም፤ አባቶቻችን የታላላቅ ስልጣኔ ባለቤቶች ነበሩ፤ አክሱም አልፈው ህንድ ድረስ ገዝተዋል፤ የመን በአረማውያን እጅ በነበረችበት 5ኛው ክፍለ ዘመን የሰላም ማስከበር ስራ የሰሩ ባለውለታዎች ናቸው፡፡

በአይሁድ በክርስትናና በኢስላም ታሪኮች አኩሪ ገድል ያተሙ ልበ ብሩሆች ነበሩ፤ የእነሱ ልጆች ብንሆንም አሁን ካለው የዓለም ሜዳና የስልጣኔ ጨዋታ አኳያ ሊጋችን የወረደ የመጨረሻው ዲቪዚዮን እንኳን የማይገባን ኋላ ቀሮች ነን፡፡ በእርግጥ መሪዎች ሰርተውን ነው፡፡ ንጉሡ እንዳንደማመጥ አድርገውናል፤ ወታደራዊው መንግስት ጆሮም ሀሳብም ካለው ይልቅ ጉልበት ያለው ራሱን ያተረፈበት እንደሆነ አሳይቶናል፡፡

ያለፉት ሃያ አምስት የጨለማ ዓመታት ከሰው ልጆች ስልጣኔ ወደኋላ ቀርተን በዘር ቡድን እንደ እንስሳ የተፋጀንበት፣ ቂም የተቋጠርንበት ነበር፡፡ የዚህ ሁሉ ስሪት ውጤት መሆናችን አሁን ጥሩ ቀን መጥቶ እንኳን መጥፎውን ማዛጋትና መራብ ጀምረናል፡፡

ዶክተር አብይ የሚወደድ እና የሚመረጥ መሪ ነው፡፡ የሚናፈቅ ሰው ነበር፤ የምንናፍቀውን ነገር ሁሉ ሰጠን፤ የተሰጠን ነገር ሁሉ ሰለቸን፡፡ እንደ ዓለም ኳስ ተጫዋቾች ህግ የአንዱ ሀገር ምርጥ ሌላው ጋር ተሽጦ እንደሚጫወተው በመሪ ደረጃም እንዲህ ያለ ልማድ ቢኖር የጠቅላይ ሚኒስትራችን ሜዳ እንግሊዝና አሜሪካ ነበሩ፡፡ ለአሜሪካና እንግሊዝ ዓይነት ስልጡን ህዝብ ተሽጠው ቢጫወቱ ጥሩ ኳስ አግብተው ዋንጫ ያነሳሉ፡፡ ዋንጫ በማይነሳባት ሀገር ፍዳቸውን በሉ፡፡

መንገዳችን ጥሩ እንዳልሆነ እያወቅን ጓዝ ጭነን ጉዞ ጀምረናል፡፡ እስከአሁን ከመጣነው ብዙ ልንማር ይገባ ነበር፡፡ የእስከአሁኑ መንገድ ተጉዘን ተጉዘን የትም ያልደረስንበት ጎዳና ነው፡፡

ጥላቻና በቀል የዱር እንስሳት እንኳን ያለ መርህ የማይተገብሩት ባህሪ ነው፡፡ ወደማንም ጣታችንን አንቀስር፤ ሁላችንም ጥፋተኞች ነን፡፡ ሁላችንም መደማመጥ፣ ነገን ማሰብ፣ ሰክኖ መጓዝ አንሻም፡፡ ሀገር የተረከብነው ትንፋሻቸውን ውጠው፣ ህይወታቸውን ሰጥተው፣ እምነታቸውን አክብረው፣ ልዩነታቸውን ጠብቀው ታሪክ ከሰሩ አባቶቻችን ነው፡፡ ሀገራችንን ገዝተናት አይደለም፡፡ የሸሚዞቻችንን ያህል እንኳን ቦታ የማንሰጣት የተከፈለውን ዋጋ አቅልለን ከማየታችን የመጣ ሞኝነት ነው፡፡ ሰንፍ ሰው ሞኝ ነው፡፡ ግን ደም አለብን፡፡

ሀገር ለመስራት የተከፈለው ደም እንደ አቤል ደም ሲያቅበዘብዘን እንዳይኖር ሩቅ እናስብ፤ ከዚህ ቀደም ታሪካችን ነበር የማይመጥነን አሁን ደግሞ ታሪካችንና መሪያችን የማይመጥኑን ህዝቦች ልንባል ነው፡፡ አቤቱ የቀደመ በደላችንን አታስብብን፤

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close