Connect with us

Ethiopia

አቶ ልደቱ ፕ/ ር ብርሃኑን ለምን ያሳድደዋል?

Published

on

አቶ ልደቱ ፕ/ ር ብርሃኑን ለምን ያሳድደዋል?

አቶ ልደቱ ፕ/ ር ብርሃኑን ለምን ያሳድደዋል? | ሬሞንድ ኃይሉ በድሬቲዩብ

አቶ ልደቱ አያሌው ለሁለተኛ ጊዜ የፕሮፌሰር ብራሃኑን ደጃፍ እያንኳኳ ነው፡፡ ከዓመታት በፊት አሜሪካን ሀገር ላይ ሁለቱን ፖለቲከኞች ለማገናኘት የተደረገው ጥረት በፕሮፌሰር ብርሃኑ እምቢተኝነት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ፕሮፌሰር ብረሃኑ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት ለአንባቢያን ጀባ ባለው መጽሐፉ አቶ ልደቱን በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅንጅትን ያፈረሰ ሰው መሆኑን ሊነግረን ሞክሯል፡፡ ባሳለፍነው ዕሁድ በአዲስ አባባ ስታድዮም ለደጋፊዎቹ በሾርኔ ለመናገር እንደሞከረው ሁሉ ልደቱን የድህንነት መስሪያ ቤቱ ቅጥረኛና ቅንጅት ውስጥ ሰርጎ የገባ የኢህአዴግ ሰው ያድርገዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ “የነጻነት ጎህ ሲቀድ” በተባለው መጽሐፉ ላይ ልደቱን ሲተች እጅግ ስልታዊ መንገድን እየተከተለ ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ላይም እራሱን ከዳር አድርጎ ልደቱን ሰላይ ነው ይሉታል፤ ውሸታም ነው ይሉታል፤ እያለ ትረካውን በሶስተኛ ወገን አንጻር የሚያስኬደውም ከዚህ በመነሳት ይመስላል፡፡

አቶ ልደቱ ግን በመጽሐፉ ፕሮፌሰሩን በተዘዋዋሪ ከመዝለፍ ይልቅ ስሙን እያነሳ ያበጠረጥረዋል፡፡ “ከአርም ዕርሻ “እሰከ “ትያትር ወ ቦለቲካ” ባቀርባቸው ሶስት ድረሳናት ውስጥ የፕሮፌሰር ብርሃኑን ስም ሲነሳ ያለርህራሄ መተቸት ይቀናዋል፡፡ የብልጣ ብልጥ ፖለቲከኛ መሆኑ ሳያንስ የስልጣን አምሮት ያሳበደው ሰው ነው ሲልም ይወቅሰዋል፡፡ በድሃ ልጅ ደም ተረማምደን ስልጣን እንያዝ ሲለኝ እምቢ ማለቴም ክህደት አልነበረም ሲልም ይደመጣል፡፡ ሁለቱ ጉምቱ ፖለቲከኞች በመጻሐፋቸው የየራሳቸውን ትክክለኝነት ለማሳየት ጥረዋል ፡፡ አንዱ አንዱን የድሀን ልጅ ደም ዋጋ ያሳጣ ሲል ይተቻል፡፡

ፕሮፌሰር ብረሀኑ ነገና አቶ ልደቱ አያሌው በመጽሐፋቸው በርካታ ቦታዎች ላይ ቢዘላለፉም በሁለት ነገር ግን ይሰማማሉ፡፡ የመጀመሪው ቅንጅትን እንደ ፓርቲ ያቆመው የልደቱ አያሌው ኢዴፓ መሆኑን ነው፡፡ ህልም የሚመስለው የቅንጅት ለአንደነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ማኒፌስቶ ከኢዴፓ ፓርቲ ማኒፌስቶ ላይ ቃል በቃል የተገለበጠ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የልደቱ አሰተዋጾ የጎላ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሀሳብ ደግሞ ቅንጅትን እንደ ፓርቲ ያቆመው ልደቱና የእሱ ፓርቲ ኢዴፓ መሆኑን ያሰገነዝበናል፡፡ ነገርየውን ገልብጠን ከተረዳነው ቅንጅት ካለልደቱና ኢዴፓ ከውኃ የወጣ ዓሳ ነበር ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ፕሮፌሰሩም ቢሆን ያልካዱት ጉዳይ ደግሞ የልደቱ አያሌውን ግሩም ፖለቲከኝነት ነው፡፡ ፕሮፌሰር ብረሃኑ በ”ነጻነት ጎህ ሲቀድ መጽሐፋቸው የልደቱ ትልቁ ብቃቱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በብቃት ተረድቶ መተንተኑ ነው የሚሉንም ለዚህ ነው፡፡ አራት አስርታትን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያለፉት ሰው ልደቱን እየጠሉትም ቢሆን ይህን አስተያየት መስጠታቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለምን ከልደቱ ጋር መገናኘት እንደሚፈሩ የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡

ፖለቲካ ዕምነት እንጅ ዕውነት አይደለም፡፡ ሀቅን መያዝ ብቻውን በፖለቲካ ሰገነት ላይ አያስቀምጥም፡፡ ፕሮፌሰሩ ዕውነት ከዕሳቸው ጋር ብትሆን እንኳን ልደቱ ላይ ጎል ማስቆጠር እንደሚከብዳቸው በውሉ ተረድተዋል፡፡ የልደቱን ልበሙሉነት ላየ ሰው ግን ጉደዩን ከመከራከር ብቃት ጋር ብቻ አስተሳስሮ መመልከቱን ኢ አምክኖያዎ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁለት ዕውነት ቢኖር እንኳን ሀቅ ያለቸው ካአንድ ጎራ ነውና ለአንዱ ሽንፈትን ማሰጎንጨቷ አይቀርም፡፡

አቶ ልደቱ እራሱ እንደሚለው የሀሜት ፈንጣጣ የያዘው ሰው ነው፡፡ ይህ አይነቱ ህመም ደግሞ በሕይወት ውስጥ አንዴ ብቻ የሚያጠቃ በመሆኑ ነገ ድጋሚ እጠቃበታለሁ ብሎ አይፈራም፡፡ በዚህ የተነሳም አቶ ልደቱ እሱ በተሰቃየበት በሽታ ፕሮፌሰሩ ሲሰቃይ ማይት ይፈልጋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደግሞ በዚህ ስዓት ከዚህ ህመም ጋር መጋፈጥ አይፈልጉም፡፡ በሕይወት መንገድ ላይ ከስድስት አስርታት በላይ ለተጓዙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሀሜት ፈንጣጣው የዘመናት የፖለቲካ ልፋታቸውን እንደ ጠዋት ጤዛ ማረገፉ አይቀርም፡፡ እናም ከልደቱ ጋር መገናኛት ለበሽታው ያጋልጠኛል ብለው ይርቁታል፡፡ ለፖለቲካ የተሰጠ ስብዕና አለው ብለው በአንድ ወቅት የመሰከሩለት ሰው አሁን ያሳድዳቸው ይዟል፡፡ ፕሮፌሰሩ ልደቱን የሚሸሹት ዕራሳቸውን ለማዳን ነው፡፡ ከፖለቲካዊ ራስን ማጥፋት የሚደረግ ሽሽት ተደርጎም ሊቆጠር ይችላል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ የሚፈሩት ልደቱን ይሁን ዕውነትን እርገጠኛ መሆን ባይቻልም የመገናኘት የሞራል ሀላፊነት ግን ያለባቸው ይመስለል፡፡ ይህ ደግሞ ልደቱን በማክበር አልያም ከዕሱ አላንስም በሚል ጀብደኝነት ሳይሆን ህዝብ እውነቱን እንዲረዳ ከማድረግ የሚመንጭ መሆን አለበት፡፡

ምርጫ 97ን ተከትሎ ለጠፋው የሰው ህይወት ከመንግስት ባልተናነሰ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ሀላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ ይህ ኃላፊነት የመውሰድ ጉዳይ ግን እስካሁን አንዳቸው በአንዳቸው ላይ ከማሳበብ ባለፈ የጸጸት ምልክት እንኳን ሊያሳዩን አልፈለጉም፡፡ በመሆኑም የፕሮፌሰር ብርሃኑና የአቶ ልደቱ ውይይት ህዝቡ ከታሪክ እንዲማር በር ስለሚከፍት የሞራል ግዴታ ያለበት ተግባር ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close