Connect with us

Business

የሼህ ሙሐመድ እስር ያደኽያቸው ሹማምንቶች!

Published

on

የሼህ ሙሐመድ እስር ያደኽያቸው ሹማምንቶች!

የሼህ ሙሐመድ እስር ያደኽያቸው ሹማምንቶች! | ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ 

እዚህ አገር የሙስና መገለጫ ዓይነቱ አንድ ሺ አንድ ነው፡፡ ድንበር የለውም፣ ይሉኝታና ምን ይሉኝን አያውቅም፡፡ ባለፉት ዓመታት እንደምንም ኢህአዴግን ተጠግተውና ተንጠላጥለው ሥልጣን የተቆናጠጡ ብዙ ብልጣብልጦች የድርሻቸውን ዘግነዋል፡፡ ከደሀው ሕዝብ ኪስና ጉሮሮ ዘርፈው የወደቀ ኑሮአቸውን አቃንተዋል፡፡ ብዙዎችም ከልደታ እስከ ባዕታ የማታደርስ ወርሀዊ ደመወዝ ይዘው “ባለሀብት” እና “ልማታዊ ባለሀብት” ተብለው በአደባባይ ተሞግሰዋል፡፡ ገሚሶቹም ለገዛ ልጆቻቸው እንዴት ሐብት እንዳፈሩ ሊተርኩላቸው በማይችሉበት ሁኔታ “ሚሊየነር” የመባል ክብር (ክብር ከተባለ) ተቀዳጅተዋል፡፡

አሁንም እነዚሁ ጉዶች በለውጥ ባቡር ውስጥ ተሸለክልከው ተሳፍረውም ጭምር “የሥርዓታችን አደጋ ኪራይ ሰብሳቢነት ነው” የሚለውን ነጠላ ዜማ እያዜሙ የሰረቁትን ማጣጣም ቀጥለዋል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ እነዚሁ የመንግሥትን ሥልጣን ለግል ክብርና ዝና ያውላሉ ተብለው በሌሎች ባለስልጣናት የሚብጠለጠሉ ሌቦች ባለሀብቶችን ላልተገባ ጥቅማቸው እንዴት እንደሚጠቀሙባቸው ማየት የምለውን ለማስረዳት ይቀላል፡፡

የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ያው እንደምናውቀው ዓለምአቀፍ ቱጃር ናቸው፡፡ ይህቺ አገር ገና ሠላምና መረጋጋት የላትም፣ ለኢንቨስትመንት አታመችም ተብላ በተፈረጀችበት የ1983ቱ ለውጥ ወቅት የውጭ ምንዛሪያቸውን ሸክፈው ወደአገር ውስጥ ለመግባትና ለመስራት ማንም የቀደማቸው አልነበረም፡፡ እናም የእሳቸው መምጣትና በሠላም ሥራቸውን ማከናወን በቀጣይ ለመጡት ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች ጥሩ አርአያና መሠረት መሆን ችሏል፡፡

ሼህ ሙሐመድ የተቸገረን የመርዳት፣ የመደገፍ ልማድ ያላቸው ርህሩህ ሰው ናቸው፡፡ ባለስልጣናት ከገቢያቸው ማነስ ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች እንደሚገጡሟቸው በመረዳታቸው አቅማቸው በፈቀደ ለመርዳት ወደኃላ ብለው አያውቁም፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ደጋግመው ደጃቸውን ጠንተው ቤት፤ ሕንጻና ውድ መኪና የተገዛላቸው፣ ለቢዝነስ መነሻ ገንዘብ የተለቀቀላቸው ሹማምንት ለጊዜው ትተን ሌላውን አንቃኝ፡፡

አንዳንድ በሚኒስትር ደረጃ ያሉ ከፍተኛ ሹማምንት ከራሳቸው አልፎ ዘመዶቻቸው ሁሉ ሲታመሙ ደጅ የሚጠኑት ሼህ ሙሐመድ ጋር ነው፡፡ “አባቴን፣ እናቴን፣ አጎቴን፣አክስቴን… አሳክምልኝ” ከሚለው የልመና ደጅ ጥናት ጀምሮ “ልጆቼን ያሳደገች ታማኝ ሠራተኛዬ ናት፣ አሳክምልኝ” እስከሚል ባለስልጣን የልመናና የተማፅኖ አቤቱታ በየዕለቱ ያስተናግዳሉ፡፡

ከዚህም አልፎ ተርፎ አንዳንድ ባለሥልጣናት ሸራተን አዲስ ሆቴል ተቆላፊ ባለሳጥን የመጠጥ ደንበኞች ናቸው፡፡ በስማቸው በተከፈተ ሳጥን መጠጥ ተቆልፎ (እገሌ ሸራተን ሎከር አለው ይባላል) ይቀመጥላቸዋል፡፡ በስማቸው እየፈረሙ ውድ መጠጦችን በየቀኑ ሲያንቆረቁሩ ሐፍረት የሚባል ነገር አልፈጠረባቸውም፡፡ አንዳንዶቹ አልፈው ተርፈው ድግስ በተጠሩበት ሁሉ በሸራተን የቅሌት መዝገብ ላይ ግጥም አድርገው ፈርመው መጠጥ አስጠቅልልለው እብስ ማለታቸው የተለመደ የየዕለት ትዕይንት ነበር፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በትዝብት እንደሚናገሩት አንዳንዶቹ ዓመታዊ የመጠጥ ፍጆታቸው ሚሊየን ብሮች የደረሰ ነው፡፡ ሚሊየኖች የዕለት ጉርስ ባጡባት ኢትዮጵያችን፤ ውድ መጠጦችን በዱቤ ፈርመው የሚጠጡ ሹማምንት መኖራቸው ሰሚውን ሁሉ የሚያስደንቅ፤ በሌላ በኩል በሥልጣን አለአግባብ የመገልገል የሙስና ድርጊት የቱን ያህል ሥር ሰዶ እንደቆየ አመልካች ነው፡፡

እርግጥ ነው፤ የመንግሥትን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት በማዋል ሕዝብና መንግሥትን በፍጹም ታማኝነትና ቅንነት የሚያገለግሉ በርካታ የተከበሩ ሹማምንትን መኖራቸውን ጨርሶ የምንክደው አይደለም፡፡ ይህ ትችትም እነዚህን ወገኖች ጨርሶ የሚመለከት አይደለም፡፡

እናም በድንገት አምና በጥቅምት ወር ገደማ ሼህ ሙሐመድ ከሳዑዲ ንጉሳዊያን ቤተሰቦች የሥልጣን ሽኩቻ ጋር ተያይዞ ለእስር መዳረጋቸው ተሰማ፡፡ በዜናው በርካታ ኢትዮጵያውያን አዘኑ፡፡ ቀን ቀን እየወለደ ሲመጣ ታላቁ የአገር ባለውለታ፣ በኢትዮጵያ ከ70 በላይ ኩባንያዎች ባለቤት፣ ከ40 ሺ በላይ ሠራተኞች አስተዳዳሪና አባት የሆኑት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ እየተረሱ መጡ፡፡

እውነት ለመናገር፤ በአሁኑ ሰዓት ከሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች በስተቀር ስማቸውን በአደባባይ የሚጠራ፣ ለእሳቸው በአደባባይ የሚቆረቆር፣ እንዲፈቱ የሚወተውት ዜጋ ማግኘት አዳጋች ሆኗል፡፡

ሼሁን ከረሷቸው ሰዎች ቀዳሚዎቹ ከእጃቸው የበሉ፣ የጠጡ፣ ታክመው ከሞት የዳኑ ግለሰቦች ቀዳሚዎቹ ነበሩ፡፡

አንድም ተጧሪ አርቲስት በአደባባይ ወጥቶ “ሼህ ሙሐመድ ይፈቱ” ሲል አልተሰማም፡፡ ለእሳቸው ደረቱን ነፍቶ አጠገባቸው ሲቆረቆር አልታየም፡፡

አንድም ባለሥልጣን (በቅርቡ ከጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በስተቀር) ስለሳቸው መልካምነት አንስቶ ድምጹን ያሰማ የለም፡፡

የሼህ ሙሐመድን ድርጅቶች በቅርበት የሚመሩት ወንድሞቻቸው ይህንን በመገንዘብ ይመስላል፤ በቅድሚያ የወሰዱት እርምጃ አንዳንድ አይን አውጣ ባለስልጣናትን ከሕገወጥ ጥቅም ማገድ ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት የፊርማ ብዕሩን ቀስሮ ወደሸራተን የሚሄድ ባለሥልጣን የለም፤ ከእነቅሌቱ ተባሯልና፡፡ በመባረሩ ብቻም ሳይሆን ከልደታ- ባዕታ በማታደርስ ደመወዙ ከፍሎ መስከር ስለማይችል (በዚህ ላይ ኩርፊያ ተጨምሮበት) ሸራተን ድርስ አይልም፡፡

ይህ ብቻም አይደለም፤ አንዳንዶቹ ያን ሕገወጥ ጥቅም እንደሕጋዊ አሠራር ማየት በመጀመራቸው ዛሬ ባውለታቸው የነበሩት ሼህ ሙሐመድ በታሰሩበት ጊዜ እንኳን ከጎናቸው ለመቆም ዳተኛ ሆነዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከጠላቶቻቸው ጋር አብረው የቆሙበት ሁኔታ መኖሩ እያስተዋልን ነው፡፡

ይህም ሁሉ ሆኖ ሼህ ሙሐመድ አንድ ቀን ከእስር ሲወጡ እነዚህ ሆድአደሮች አሁንም ተንጋግተው ከፊት ለመሰለፍ ሲሯሯጡ እናያቸው ይሆናል፡፡ አዎ! በእርግጥም ማየታችን ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ለአሁኑ ግን ሼህ ሙሐመድ በሠላም ተለቅቀው ከሚወዷት አገራቸውና ሕዝባቸው ጋር የሚቀላቀሉበት ቀን እንዲመጣ ሁላችንም በጸሎት አንርሳቸው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close