Connect with us

Africa

ኢትዮጵያን የኤርትራ ወደቦችን እንድጠቀም የተሰራው የጀርባ ፖለቲካ

Published

on

ኢትዮጵያን የኤርትራ ወደቦችን እንድጠቀም የተሰራው የጀርባ ፖለቲካ

ኢትዮጵያን የኤርትራ ወደቦችን እንድጠቀም የተሰራው የጀርባ ፖለቲካ | ፀጋው መላኩ በድሬቲዩብ

ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም እንቅስቃሴን ጀምራለች፡፡ ሁለቱ ሀገራት ሰላም አውረደው የመግባቢያ ስምምነትን ከተፈራረሙ በኋላ የስምምነቱን አተገባበር በአካል ለመመልከት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የተመራው ልዑካን ቡድን በአሰብና ምፅዋ ወደቦች በመገኘት የሁለት ቀናት ጉብኝት አድርጓል፡፡

ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ ጥገኝነት በመላቀቅ አማራጭ ወደቦችን እንድተጠቀም በማድረጉ ረገድ በጀርባ የራሳቸውን ሚና የተጫወቱ ኃይሎች አሉ፡፡ በዚህ በኩል ባለው የጥቅም ፖለቲካ ትስስር ጁቡቲና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የገቡበት የወደብ አገልግሎት ውዝግብ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ጂቡቲ ለቻይና የጦር ሰፈር የመፍቀዷም ጉዳይ አሜሪካንንም ክፉኛ ያስቆጣበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

የጂቡቲን ወደብ ዘመናዊነትን በተላበሰ ሁኔታ በማስተዳደሩ ረገድ ሶስት ኩባንያዎች በሽርክና ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አንደኛው የተባበሩት አረብ ኤሜሬቱ ዲፒ ወርልድ ኩባንያ ሲሆን፤ ሌሎቹ ሁለቱ ኩባንያዎች ደግሞ ፖርት ዲ ጂቡቲ እና ቻይና ሜርቻንትስ ናቸው፡፡
ወደቡን በሽርክና በማስተዳደሩ በኩል በጅቡቲ መንግስትና በዲፒ ወርልድ መካከል ተከታታይ የሆኑ ውዝግቦች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ በማድረጉ ረገድ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት መንግስት የራሱን ጥረት ሲያደርግ ቢቆዩም ጥረቱ ስኬትን ሳያገኝ ቀርቶ ወደ ፍርድ ቤት አምርቷል፡፡

ዲፒ ወርልድ የምስራቅ አፍሪካን ወደቦችን በኮንትራት በማስተዳደር አካባቢውን በጂቡቲ ወደብ አንድ ብሎ ወደ ሶማሌላንድ በርበራ ወደብ ለመሸጋገር ያደረገው ጥረት ገና በጅቡቲው ጉዞው ስኬቱ ተደናቅፏል፡፡ የጂቡቲና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት የውዝግብ መነሻ በወደብ አገልግሎት ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡

እንደ አልጄዚራ ዘገባ ከሆነ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከዚህ ቀደም በጂቡቲ የጦር ቤዝ እንዲኖራት ጥያቄ አቅርባ ጉዳዩ በጂቡቲ መንግስት በኩል ተቀባይትን ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ ሀገሪቱ በጂቡቲ ያጣችውን የጦር ሰፈር በኤርትራው የአሰብ የጦር ሰፈር ማሳካት ችላለች፡፡

ይህም የጂቡቲ እምቢታ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተጨማሪ የቅሬታ መንስኤ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ተደማማሪ ሁኔታዎች የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን ልዑላን ክፉኛ ንዴትን ሳላጫረባቸው ጂቡቲን ከወደብ አገልግሎት ጨዋታ ውጪ የማድረግ ሴራ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡

ጂቡቲን በብዙ መልኩ መበቀል የፈለገችው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ፤ ሁለቱ ሀገራት ማለትም ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላሙ አቅጣጫ እንዲመጡ በማድረጉ ረገድ የራሷን ያላሰለሰ ሚና ስትጫወት የቆየች ሲሆን፤ በመጨረሻ ጥረቱ ፍሬ ማፍራቱን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት በታላቁ ቤተመንግስት የንጉሱን የክብር ሜዳሊያ ሽልማትን በአንገታቸው እንዲያጠልቁ ተደርጓል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለከቱት ከሆነ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንዲገቡ ቀደም ብሎ ከመጋረጃው በስተጀርባ አሜሪካና የተባበሩት አረብ ኤሜሬት እንደዚሁም ሳዑዲ አረቢያ ሰፈውን የማግባባት ሥራን ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

የሰላም ሀሳቡን በመቀበሉ ረገድ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ያስቀመጠችውን ቅድመ ሁኔታ አንስታ የአልጀርሱን ሥምምነት እንዳለ ለመተግበር ከመስማማቷ ጀርባ፤ እንደዚሁም ኤርትራ “የኢትዮጵያ ጦር ባድሜን ለቆ ካልወጣ ነገሮችን ወደ ነበሩበት መመለስ (Normalization) የሚባል ነገር የለም” የሚለውን አቋሟን ከመቀየሯ ጀርባ፤ ሌሎች ስውር የዲፕሎመሲ እጆች መኖራቸውን የሚጠቁሙ አዝማሚያዎች እንዳሉ አሁን አሁን ሁኔታዎቹ ገልፅ እየሆኑ መጥተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከጂቡቲ ጋር ከገባችበት የቀደመ ውዝግብና በሌሎች ውስብስብ አካባቢዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ጋር

በተያያዘ ኢትዮጵያን በሚገባ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗን በግልፅ እያሳየች ትገኛለች። ኢትዮጵያ የገጠማትን ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመታደግ የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ልዑል ሞሀመድ ቢን ዛይድ አልናያን በሙስሊሞች ልዩ የበዓል ቀን ኢትዮጵያ ድረስ በመምጣት በኢትዮጵያና ዓረቦች ዘመናዊ የታሪክ ግንኙነት ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የ 3 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍን ማድረጋቸው የዚህ ቁርጠኝነት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

የዚህ ሰውር የዲፕሎማሲ እጅ ጨዋታ በተባበሩት አረብ ኤሜሬት የሚገታ ብቻ ሳይሆን አሜሪንንም ጭምር የሚያካትት ነው፡፡ እንደሚታወቀው አሜሪካ በጂቡቲ ግዙፍ የጦር ሰፈርን ገንብታለች፡፡ ጂቡቲ በኤደን ባህረ ሰላጤ፣በስዊዝ ቦይ መተላለፊያና በእስያና አውሮፓ መገናኛ ጫፍ ላይ ምትገኝ ስትራቴጂክ ሀገር በመሆኗ የትኛውም ሀገር ለጦር ሰፈርነት ይፈልጋታል፡፡ ሆኖም ጂቡቲ አሜሪካን የጦር ሰፈር በሰጠችበት ለጋስነቷ የአሜሪካ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ባላንጣ ለሆነችው ቻይና የጦር ሰፈር መፍቀዷ አሜሪካንን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡

አሜሪካ የቻይና መንግስት በጂቡቲ ምድር የጦር ሰፈር እንዳያገኝ ያደረገችው ጥረት በጂቡቲ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ በእጅጉ ቅሬታዋን ስትገልፅ ቆይታለች፡፡ ጉዳዩ ከቅሬታነት ባለፈ ወደ በቀልም በማምራቱ አሜሪካ ልክ እንደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬት ሁሉ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በማግባባት ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች በመጠቀም ከጂቡቲ የወደብ ጥገኝነት እንድትላቀቅ ሰፊ የጀርባ ሥራን ስትሰራ ቆይታለች፡፡

አሜሪካ ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀውን የኢትዮ-ኤርትራ ውዝግብ እንዲያከትም በማድረጉ ረገድ ከመጋረጃ ጀርባ የራሷን ሚና ስትጫወት ቆይታ፤ በስተመጨረሻ አሜሪካዊው እውቅ ዲፕሎማት ዳናልድ ያማማቶ በሚያዚያ ወር 2010 ዓ.ም አስመራና አዲስ አበባ በመመላለስ ጉዳዩ የመቋጫ መልክን እንዲይዝ ማድረግ ችላለች፡፡ አሜሪካ ኤርትራን በአሸባሪነት ከፈረጀችበት ወቅት ጀምሮ ነገሮችን በማለዘብ አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት አስመራ ስትልክ ዶናልድ ያማማቶ የመጀመሪያው ሰው ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡

የተባበሩት አረብ ኤሜሬት አመራሮች የኤርትራ ወደቦችን ወደ ተፈለገው ዘመናዊነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደዚሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያሉትን የመሰረተ ልማቶች ተስስስር ለመጠገንና ለመገንባት የሚሆን እገዛም ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡

ይህ ብቻ ሳይሆን ከአሰብ ወደብ አዲስ አበባ የሚደርስ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦን ለመዘርጋትም የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ውሳኔ ላይ ደርሳለች፡፡ ይህም የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ እውን የሚሆን ከሆነ ኢትዮጵያ በጂቡቲ ወደቦች በኩል በተሽከርካሪ በማጓጓዝ የምትጠቀመው ነዳጅ ይቀራል ማለት ነው፡፡ ይህም የጂቡቲን የወደብ ገቢ በከፍተኛ ደረጃ የሚያወርደው ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ በነዳጅ ቦቴዎች ከወደብ ወደ መሀል አገር የሚደረገውን የቦቴ ተሽከርካሪ የነዳጅ ማጓጓዝ ስርዓት ወደ ዘመናዊው የነዳጅ ቱቦ አሰራር ለመለወጥ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ይህንን ፕሮጀክት እውን ለማድረግም ከፕሮጀክት ቀረፃ እስከ ፋይናስ ማፈላለግ ድረስ ተገብቶ ነበር፡፡ ብላክ ሬኖ ግሩፕ የተባለ ኩባንያም የቱቦ ዝርጋታ ሥራውን ይሰራል የሚሉ ጭምጭምታዎች ሲነገሩም ቆይቶ ነበር፡፡

ሆኖም አሁን የተባበሩት አረብ ኤሜሬት ከአሰብ አዲስ አበባ እዘረጋዋለሁ ያለችው የነዳጅ ቱቦ መስመር እውን የመሆን ከሆነ የኢትዮ-ጂቡቲን የቀደመ የነዳጅ ማስተላፊያ ቱቦ እቅድ ላይ ጥላውን በማጥላት የጂቡቲ ወደብን ከዚህ ጨዋታ ውጪ የሚያደርገው ይሆናል፡፡

በኢትዮ ኤርትራ አዲስ ግንኙነት ጂቡቲ ከኢትዮጵያ ታገኝ የነበረው የወደብ ገቢ እየቀነሰ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደቦች ባሻገር የኤርትራ ወደቦች መጠቀም መጀመሯ በጂቡቲ ወደቦች ላይ የነበራትን ጥገኝነት በከፍተኛ ደረጃ የሚቀንሰው ይሆናል፡፡

ሁኔታው በእጅጉ ያሳሰባት ጂቡቲ፤ ቀደም ሲል ከኤርትራ ጋር የገባችበትን የድንበር ውዝግብ በማለዘብ ጉዳዩን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት ዝግጁ መሆኗን ገልፃለች፡፡ ሁለቱን ሀገራት በማግባባቱ ረገድ የሰሞኑን የሰላም ሀሳብ ያቀረበችው ኢትዮጵያ መሆኗን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ እንደዚሁም ሶማሊያ በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ስብስብ ውሰጥ ግንኙነቶቻቸውን ማጠናከራቸው ጂቡቲን ክፉኛ ያሳሰባት ይመስላል፡፡ ይህም በመሆኑ ጂቡቲ ከኤርትራ ጋር እርቅ እንድታወርድ ስትጠየቅ ምላሿ ፈጣን ነበር፡፡

በዚሁ ሁሉ መሀል ግን ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ወደብ ሙሉ ጥገኝነት በተወሰነ ደረጃ ተላቃ አማራጭ የኤርትራ ወደቦችን እንድትጠቀም እድልን ፈጥሮላታል፡፡ ይህም በአካባቢው ለዓመታት ሲብላላ የነበረው የፖለቲካ ውዝግብ ውጤት ነው፡፡ እስከ አሁን ያለው ምክንያትና ውጤት ይህ ቢሆንም ቀጣይ አካሄዱ ምን አይነት አዝማሚያን እንደሚከተል አይታወቅም፡፡ ያም ሆኖ ግን አሁን ባለው የኃይል አሰላለፍ ኢትዮጵያና ኤርትራ አትራፊ ሆነው ይታያሉ፡፡

የዚህ ትንታኒያዊ ዘገባ ምንጭ አልጀዚራ፣ፋይናሲያል ታይምስ፣ ዘ ማሪ ታይም ኤግዚኪዩቲቭ (The MARITIME EXECUTIVE) እና ዘ ኢኮኖሚስት ናቸው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close