Connect with us

Business

የአዲስ አበባ ከንቲባ በመኾኔ ደስ ብሎኛል

Published

on

የአዲስ አበባ ከንቲባ በመኾኔ ደስ ብሎኛል

በሩን ለብቻው ከሚጠቀም አልጠግብ ባይ ከንቲባ እናንተም ከንቲባ ናችሁ ብሎ ለሚሊዮኖች ስልጣኑን ወደሚያጋራ ከንቲባ ያሸጋገርከን ፈጣሪ እናመሰግንሃለን፡፡ ኢንጅነር ታከለም እኔም እናንተም የአዲስ አበባ ከንቲባ ነን፡፡ |  ሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

ቃል ይፈውሳል፡፡ በአዲሱ ዓመት ተፈውሻለሁ፡፡ ደሳሳ ቤት ሳይኖረኝ ረዣዥም ህንጻዎች በበቀሉባት አዲስ አበባ ስኖር አንገቴን ደፍቼ ነበር፡፡ ባይተዋር ነበርሁኝ፤ አንድ ቀን አንዱ ሹም ጠርጎ ከከተማዋ ያበረኛል የሚል አሳብም ይመጣልኝ ነበር፡፡ አሁን ያ ስሜት የለኝም፡፡ አዲስ አመት አዲስ ሹመት አግኝቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከንቲባ ነኝ፡፡

ህንጻዎቹ ቢገዝፉም እኔ በምመራት ከተማ ስለሆነ ስጋት አይሰማኝም፡፡ የከተማዋ መንገዶች ጉዳይ እንደ እግረኛ ሳይሆን እንደ ከንቲባ ያሳስቡኝ ጀምረዋል፡፡

አዲስ አበባን የሚያህል ግዙፍ የአፍሪካ መናገሻ እንድመራ ከንቲባዬ የሹሙኝ ሹመኛ ነኝ፡፡ አሁን መንገድ ላይ አልሸናም፤ ከንቲባ መንገድ ላይ አይሸናም፡፡ አሁን በእግሬ ስሄድ ድህነት አይሰማኝም፤ በአውቶቡስ መሄድም ኩራት ነው፡፡ በአንበሳ ተሳፍሮ የሚሄድ ከንቲባ የሾመኝ መሆኔን አውቃለሁ፤ ከታክሲ ሹፌሮች እና ረዳቶች ጋር የምንግባባ ከንቲባዎች ነን፡ እኔና ኢንጅነር ታከለ፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ዛፎች ዛፎቼ ናቸው፤ ከተማዬን ያደምቁልኛል፡፡ አሁን የአዲስ አበባ ሕዝብ ሕዝቤ ነው፡፡

እኔ ከንቲባ ነኛ፤ ደግሞ ሌላውም ሰው ከንቲባ በመሆኑ ስልጣኔን ለመንጠቅ የሚፈልግ ጠላት እንደሌለኝ ስለማውቅ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ሁሉም ሰው ከንቲባ የሆነባት ከተማ መሪ በመሆኔ እኮራለሁ፡፡

አዲስ አበባን እንደ ክፍ እናት ጠልቻት ነበር፡፡ የሰጠቺኝ አንድም ነገር የለም፡፡ አየሩን እንደሆነ ባንግላዴሽም ዳርፉርም ሶርያም የመንም ቢሆን እስበዋለሁ፡፡ አዲስ አበባ በመሪዎቿ በኩል የበደለቺኝ ሰው ነኝ፡፡ አመል በሌላቸው፣ ፍቅር በሌላቸው፣ አቅም በሌላቸው፣ መልካም አሳብ በሌላቸው መሪዎቿ ተበድያለሁ፡፡ ሠፈሬን አፍርሰውታል፤ አድሬን በትነውታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ማዛጋጃ ቤት ስንገባ እንኳን በራችን ለየቅል ነው፡፡ ፎቅ ስንወጣ ሊፍታችን ለየብቻ ነው፡፡ ከንቲባዎቼ በሙሉ ከንቱ ባል ነበሩ፡፡ አሁን ከዚያ ዘመን መሻገሬን አምኛለሁ፡፡

ኢንጅነር ታከለ ኡማ የሚባል መልከ መልካም፣ ፍቅር የሚያውቅ፣ አቅም ያለው፣ ህዝብ አክባሪ ከንቲባ እኔን ጭምር ከንቲባ አድርጎኝ የአዲስ አበባ አበባነት ተገልጦልኛል፡፡

መልከ ጥፉ ከተማ ስኖር ነበርኩ ብዬ የማስበውን ሰው ለካስ ስሟም መልኳም ያምር ነበርና እንድል እያደረገኝ ነው፡፡ ከንቲባ ነኝ፡፡

የህዝቡ ንብረት ያስጨንቀኛል፡፡ ምናገባኝ አልልም፤ ያገባኛል፡፡ እንደ ከንቲባ ወጥቼ መግባት ጀምሬአለሁ፡፡ አዲስ አበባ ላይ ከመሾም የሚበልጥ የአዲስ አመት ስጦታ አይኖርም፡፡ አዲስ አበባ እጄ ላይ ገብታለች፡፡ አትወድቅብኝም ምክንያቱም ከንቲባዬ ብልጥ ናቸው ብቻዬን ደክሞኝ እንዳልጥላት ነዋሪው እጅ ላይ በሙሉ አስቀምጠዋታል፡፡

ሁላችንም ከንቲባ ሆነን አዲሱን አመት መኖር ጀምረናል፡፡ ከተማዬ ችግር ቢኖርባትም አላሽሟጥጥም እኔ ከንቲባዋ ስለሆንሁ ችግሩን ልፈታ እጥራለሁ፡፡ ከንቲባነት እንዴት ደስ ይላል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close