Connect with us

Art and Culture

ለትዳሩና ለራሱ ያልታመነ አርቲስት የበዓል ዕለት ሲመክር…

Published

on

ለትዳሩና ለራሱ ያልታመነ አርቲስት የበዓል ዕለት ሲመክር…

ለትዳሩና ለራሱ ያልታመነ አርቲስት የበዓል ዕለት ሲመክር… | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሀጽዮን በድሬቲዩብ

ይህ ጽሁፍ ሆምጠጥ ያለ ነው፡፡ ሆኖም ሁሉንም አርቲስቶች አይመለከትም፡፡ በጸባያቸውና በሥራቸው፣ በሥኬታቸውና በሥማቻው የተከበሩ አርቲስቶችን አያካትትም-ጽሁፉ፡፡ ሆኖም ጎምዘዝ የሚል መሆኑን አስቀድሜ መናገር እፈልጋለሁ፡፡ አዲሱን ዓመትም ነጭ ነጩን በመነጋገር እንጀምረው እስኪ፡፡ እናም ነጭ ነጩን በመፃፌ የሚመለከታችሁ አርቲስቶችዬ ብትከፉብኝ አልገረምም፡፡

በነገራችን ላይ አርቲስት ምንድን ነው…? በዕውነቱ ይህንን ቃል ያለ ልክና ያለ ቦታው በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል ደረገው ደርግ ነፍሱን አይማረው፡፡ በ196ዎቹ መጨረሻ (በደርግ የአፍላ ሰሞናት) ድራማ ሰሪዎችም፣ ዘፋኞችም፣ ሰዓሊዎችም…’’ተሰደብን ማኅበረሰቡ አዝማሪ፣ እብድ ወዘተ እያለን ነው’’ ብለው በማማረር ወደ ደርግ ሄዱ፡፡ ከመንግሥት ሹመኞች መካከልም ሻምበል ፍቅረስላሴ የእነዚህን ሙያተኞች አቤቱታ ከሰሙ በኋላ ‹‹በቃ እናንተ ከዛሬ ጀምሮ አርቲስት ናችሁ›› ብለው ሁሉንም የኪነጥበብ ሰዎች ሰየሟቸው፡፡ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮም አንድ ነጠላ ዘፈን የለቀቀውም፣ አንድ ቀን መድረክ ላይ የታየም፣…ፊልም ሰሪም ሙዚቃ አቀናባሪም፣ ዘፋኝም አዘፋኝም አርቲስት ይባሉ ጀመር፡፡

በእውነቱ ይህ ትክልል አይመስለኝም፡፡ ሌሎች ሀገራትም ይህንን የሚጠቀሙበት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ አርቲስት ማሪያ ኬሪ፣ አርቲስት ማይክል ጃክሰን፣ አርቲስት ሺዋዚንገር… ሲባል ሰምቼ አላውቅም፡፡ እንግሊዘኛው በደንብ ለያይቶ ነው የሚያቀርባቸው፡፡

ዘፋኙን ‹‹singer›› ፊልም ሰሪውን performer ሰዓሊውን artist ነው የሚላቸው፡፡ እኛ ግን ሁሉንም አርቲስት እንላለን-ምስጋና ለሻምበል ፍቅረስላሴ ይሁንና!!

የሆነው ሆኖ እነዚህ አርቲስቶች (ቃሉን እኔም ለገዜው እየተጠቀምኩበት ጽሁፌን ልቀጥል) በተለይ ፊልም ሰሪዎቹና ዘፋኞቹ በየዓመት በዓሉ፣ በየቴሌቭዥኑ እየመጡብን መሆኑን ሁላችንም አስተውለናል፡፡ እንደሚታወቀው ዓመት በዓል በጉጉት የሚጠበቅ፣ ሕፃናትም አዋቂዎችም በደስታ ስሜት የሚያከብሩት የጋራ በዓል ነው፡፡ በዚህ በዓል ላይ ነው እንግዲህ እነዚህ አርቲስቶች እየመጡ በቴሌቭዥኖቻችን የምናያቸው፡፡

ለዚያም ነው በርግጥ እነዚህ አርቲስቶች ለኛ ለኢትዮጵያዊያን አርዐያ መሆን ይችላሉ ወይ? የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ያደረገኝ፡፡ ከላይ እንደገለጽሁት ይህ ሐሳብ አንዳንድ ሥማቸውንና ሥራቸውን አስከብረው በዲስፕሊን የሚኖሩ ባለሙያዎችን ባይመለከትም፣ ከላይ ላነሳሁት ጥያቄዬ መልስ የሚሆነው ሐሳብ ግን ‹‹እንኳን ለኢትዮጵያዊያን ለልጆቻቸውም አርዐያ አይሆኑም/አይደሉም›› የሚል ነው፡፡

እንደምናውቀው አብዛኞቹ አርቲስቶች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንኳ መጨረስ ያልቻሉ ሰነፎች ናቸው፡፡ በትምህርታቸው ደካማ ሆነው የኖሩ መሆናቸው ሳያንስ ‹‹ከሙዚቃ ትምህርት ውጭ ያለውን ትምህርት እፎርፍ ነበር›› እያሉ በኩራት የሚያወሩ እፍረተቢሶች ናቸው፡፡ ይህ በዓመት በዓል ዕለት ሲነገር ደግሞ ምን ስሜት ሊሰጥ እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡ በተለይ ለሕፃናት!!

የእነዚህ አርቲስቶች ሌላው ችግር ሴሰኛና ሱሰኛ መሆናቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ አርቲስቶች ባል ወይም ሚስታቸውን የፈቱ፣ ደጋግመው የፈቱ፣ ለትዳራቸው መታመን አቅቷቸው ልጆቻቸውንና እናቶቻቸውን በትነው የወጡ፣ የአንዳንዶቹንም ሚስቶች ‹‹ባሌ በሽተኛ ልጅ ጥሎብኝ ሌላ አገባ፣ እኔም ከነ ልጆቼ ጎዳና ልወጣ ነው›› ሲሉ የሠማናቸውና ያየናቸው ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ሴት አርቲስቶች ደግሞ ልጅን ያለ አባት ማሳደግን በኩራት የሚናገሩ፣‹‹ሲንግል ማም ነኝ›› ብለው በሳቅ የሚያስካኩ፣ ትልልቅ ስም ያላቸው አርቲስቶች (በተለይ ሴቶቹ) የልጆቻቸውን የአባት ሥም ለመናገር የሚሸማቀቁ…ናቸው፡፡

ሱሰኝነታቸውም አይጣል ነው፡፡ በየሺሻና ጫት ቤቱ፣ በየአረቄና ውስኪ ቤቱ ሲዞሩ ውለው ሲዞሩ ያድሩና የበዓል ዕለት መጥተው ‹‹ሌሊት ስለምሰራ ቀንቀን እተኛለሁ›› ብለው ጸሐይ ማየት የናፈቃቸው ያህል ሆነው ያላግጡብናል፡፡ አሁን አሁን ግን ጫት ሳይበላ የሚሰራ አርቲስት ማግኘት በውርርድ ሆኗል፡፡ ሺሻ የማያጨስ አርቲስትም ከጣት ቁጥር አይበልጥም፡፡ ግን የበዓል ዕለት መጥተው ይመክራሉ!! ሃላስ!!

አንድ አርቲስት ሲታመም መታከሚያ ግን የሚጠየቀው ያው የፈረደበት ሕዝብ ነው፡፡ ያ ሌት ከ ቀን እንሰራበታለን የሚሉት ነገር የሚገለጠውም ያኔ ነው፡፡ ከሰሩ ገንዘብ መገኘት አለበት፣ ገንዘብ ከተገኘ ደግሞ መያዝ አለበት…! ሌሊትም ቀንም እሰራለሁ ሲሉ ከርመው ክፉ ቀን ሲመጣ ሰው ላይ ይወድቃሉ!!

በትምህረታቸው ሰነፍ፣ በትዳራቸው ሴሰኛና በአጋራቸው ላይ የሚማግጡ፣ በኑሯቸው ሴሰኛና አጉራ ዘለል፣ በኢኮኖሚያዉ አቅማቸው ድሃና ተመጽዋች የሆኑ አርቲስቶች ታዲያ በምን ሞራላቸው ነው የበዓል ዕለት መጥተው በየቴሌቭዥኑ የሚመክሩን…ይህንን ቃለ-መጠይቅ ለመሥራት በየቤቱ የሚሄዱ ጋዜጠኞችስ በዕውነቱ ይህንን ሁሉ አጥተውት ነውን?

የዚህ ዘርፍ ጋዜጠኞች ‹‹በዓል አርቲስቶች ናቸው፤ በዓልም እነርሱ ናቸው›› የሚል ትዕዛዝ ያስተላለፈባቸው መንግሥት የት እንዳለ አይታወቅም፤ ግን ከዓመት ዓመት በየበዓሉ ማይክራፎንና ካሜራ ይዘው አርቲስት ቤት ይገኛሉ፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ፊልም ሰሪና፣ ዘፋኝ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ገበሬና አርብቶ አደር ነው፡፡ የድግስ ቀን ጋዜጠኞች ግን ይህንን መሥራት አይፈልጉም፡፡ ‹‹የገበሬ በዓል አከባበር እንዴት ነው፣ ድግስ በአርብቶ አደር ቤት አለ ወይ፣ ጋራ ተራራ ሲቧጥጥ የከረመ አርሶ አደር በዓልን የሚያከብረው እንዴት ባለ ሁኔታ ነው፣ ከብቶቹን ይዞ ሲንከራተት የከረመ አርብቶ አደር አዲስ ዓመትን ለመቀበል የሚያስችል ጊዜ አለው ወይ፣ የገጠር ልጆች አበባዮሆሽ ሲጨፍሩ እንዴት ነው፣ የአርብቶ አደርስ ልጅ በዓልን ያውቀዋል ወይ…ወዘተ›› የሚሉት ጥያቄዎች የቀረቡበት የበዓል ዝግጅት እኔ አላስታውስም፡፡

ይህ ሁሉ ሐሣብ ተዘንግቶ ነው እንግዲህ በአንድ ስፖንሰር አድራጊ ሆቴል ዘመናዊ ሶፋ ላይ ከጫት ቤት የወጣ አርቲስት ቃለመጠይቅ እየተደረገለት ሕዝብ ሲመክር የሚውለው፡፡ ለራሱም ለጎረቤቱም፣ ለአገሩም አርዐያ መሆን የማይችል ጸባይ እያለው ግን ‹‹ብጹዕ ወቅዱስ›› ሆኖ ይመጣል፡፡

በድጋሚ ማሳሰቢያዬን ጽፌ ላብቃ!! ይህ ጽሁፍ ከዚህ ገለፃ በተቃራኒ ያሉትን በሙሉ አይመለከትም፡፡ በስም ብጠቅሳቸው ደስ የሚለኝ፣ ለትዳራቸው ታማኝ፣ በሥራቸው ታታሪ፣ በሥነምግባራቸው ምስጉን፣ በትምህርታቸው መልካም አርቲስቶች አሉ፡፡ እናም ይህ ወቀሳ እነርሱን አይመለከትም፡፡ እነዚያን ግን እላለሁ ‹‹እናንተ ሰዎች ሆይ እባካችሁ በዓላችንን ለቀቅ አድርጉልን››!!

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close