Connect with us

Ethiopia

የህዳሴውን ግድብ ሜቴክ በላው! የህዳሴውን ዋንጫ’ስ???

Published

on

የህዳሴውን ግድብ ሜቴክ በላው! የህዳሴውን ዋንጫ'ስ???

የህዳሴውን ግድብ ሜቴክ በላው! የህዳሴውን ዋንጫ’ስ??? | አሳዬ ደርቤ 

-በአቶ መለስ ዜናዊ ‹‹መሃንድሶቹም እኛው፣ የገንዘብ ምንጮቹም እኛው›› ተብሎ የመሰረት ድንጋዩ የተጣለለት….

-በአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ‹‹ለአባይ ግድብ በማህጸን ካሉ ህጻናት፣ በመቃብር ካሉ ሙታን በስተቀር ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተባበር አለበት፡፡ ‹አልተባበርም› የሚል ካለ ግን እሱ በገዛ ራሱ ኢትዮጵያዊነቱን ሰርዞታል፡፡›› በማለት የተገዘትንበት…

-በታዋቂው አርቲስት ጌትነት እንዬውና በእልፍ አእላፍ የጥበብ ሰዎች ‹‹አባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ›› የሚል አስገራሚ ግጥም የተገጠመለት…

-በእነሸዋፈራሁና ሰራዊት ፍቅሬ በርካታ ማስታወቂያ የተሰራለት…

-እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከራሱ አልፎ በማህጸን ባሉ ሽሎችና በመቃብር ባሉ ሙታኖች ስም ቦንድ በመግዛት ድጋፉን ያሳየበት…

-የአባይን ግድብ ቀርቶ የራሱን የስልጣን ዘመን መገደብ ያልቻለው ኢህአዴግ የበዝባዥነት እድሜውን ያራዘመበት….

-በእርዳታ የሚኖሩ ዜጎች ከዛሬ ርሃባቸው ይልቅ የነገ ጥጋባቸውን በማስቀደም የእርዳታ እጃቸውን የዘረጉለት….

-በየጊዜው በሚደረጉ ጉብኝቶች የአገራችን ዜጎች ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን የሰውለት…

-መንግስት ያለምንም በጀት እቅዱን ይፋ ሲያደርግ፣ ሜቴክ ያለምንም እውቀት ግንባታውን ለመስራት ተቋራጭ ሆኖ የቀረበበት…

-የእለት ጉርስ የሌላቸው ዜጎች ቁጠባን የተማሩበት፣ በልዩነት ውስጥ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች አገራዊ አንድነታቸውን ያሳዩበት……….

ይሄ ሁሉ ሸብ-ረብ የተደረገለት ግድባችን ያለበት ሁኔታ ሲረጋገጥ ሜቴክ ስራውን ትቶ በጄቱን ሲጨርስ መክረሙን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ሰማን፡፡

የጣሊያኑ ሳሊኒ ስራ-አስኪያጆች ‹‹በተሰጣቸው በጄት የሚጠበቅባቸውን ያህል ስራ መስራታቸውንና በሜቴክ ምክንያት ቀሪውን ስራ ሙሉ በሙሉ ለመጨረስ አለመቻላቸውን…›› የሰሩትን ግድቡን በማሳየት ደረታቸውን ነፍተው ሲናገሩ የእኛዎቹ አጋሰሶች በበጀቱ የሰሩትን ስራ በማናገር ፈንታ ተርገብጋቢ ዐይናቸውን የሚያሳርፉበት ስፍራ አጥተው ሲደነባበሩ ዐየን፡፡

በእውነቱ ይሄ በባለሙያዎች ሳይሆን የብየዳ ሙያ ባላቸው ሌቦች የተመሰረተ ድርጅት በተሰማራባቸው ፕሮጀክቶች ሁሉ በጀቱን ከመስረቅ አልፎ ፕሮጀክቱን ሲያስመርቅ ባይታይም… አገራችንን ወደ ጎጆ-እንዲስትሪ ካልሆነ በቀር ወደ ዘመናዊ ኢንዱስትሪ የማሸጋገር አቅም ባይኖረውም…. የህዳሴውን ዋንጫ እንጂ የህዳሴውን ግድብ የመስራት ብቃት እንደሌለው ቢታመንም…

እያንዳንዱ ዜጋ ገንዘቡንና ዐይኑን ከጣለበት ፕሮጀክት ላይ ግን ይሄን ያህል ቢሊዮን ብር ይዘርፋል ብሎ መገመት ይከብዳል፡፡
የሆነው ግን እንደዚህ ነበር፡፡

በታሪክ እንደተነገረን ወራሪው የጣሊያን ጦር አገራችንን በወረረበት ሰዓት ከፋሽስቶቹ ይልቅ ባንዳዎቹ ለጀግኖች አባቶቻችንን ፈተና ሆነውባቸው ነበር፡፡ ዛሬም ከጦርነት ወጥተን ልማትን በምናስብበት ሰዓት ‹‹ታሪክ እራሱን ይደግማል›› እንደሚባለው የጣሊያኑን ተቋራጭ ያህል አገራዊ ስሜትና ታማኝነት የጎደላቸው ‹የባንዳ ልጆች› ከግብጾች ጎን ተሰልፈው… ‹‹ማደሪያ በሌለው ወንዝ›› ስም ከህዝብ ጉሮሮ ተመንግጎ በመጣ ገንዘብ ‹‹ማደሪያቸውን ሲሰሩበት›› መክረማቸውን ሰማን፡፡

በአፍሪካ ቀዳሚ የሚያደርገን ግድብ ከዛሬ ነገ ያልቃል እያልን ስንጠብቅ… ሜቴክ በእግርኳሱ ዘርፍ ያጣነውን የአፍሪካ ዋንጫ ‹‹በህዳሴው ግድብ›› ስም በማዘጋጀት ‹‹እኛ በጀቱን፣ ህዝቡ ዋንጫውን ይብላ›› ብሎ ሲጫዎትብን እንደኖረ ተረዳን፡፡
እናም ለዶክተር አቢይ መንግስት እንዲህ ማለትን ወደድን፡፡

‹‹የዚህን ምስኪን ህዝብ ተስፋና ገንዘብ ያጠፉ አጋሰሶች አንድ በአንድ ተለይተው የዘረፉትን ገንዘብ ከእነወለዱ እንዲከፍሉና በካቴና ተጠፍንገው ወደ ወህኒ እንድወርዱ ካልተደረገ በቀር ‹‹እንዳጋመስን እንጨርሰዋለን›› የሚለው መፎክር አይሰራም፡፡

ኮንትራቱ ተቋርጦ ለሌላ ተቋራጭ ከመሰጠቱ በፊት… ባልሰሩት ስራ በቢሊዮን የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ ዘርፈው የተደበቁና በሰላም እየኖሩ ያሉ አመራሮች እንኳንስ ከኢትዮጵያ መሬት ይቅርና ከሌላ ፕላኔት ላይም ቢሆን አንገታቸውን ተጠምዝዞው ለፍርድ እንዲቀርቡ እንፈልጋለን፡፡ ሌቦቹን ላለመስጠት የሚንገታገት የክልል ባለስልጣንም ጠቡ ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡

ከዚህ ባለፈ ደግሞ ከአረቦች ጋር ባላቸው ቀረቤታና ከሜቴክ ሰዎች ጋር ባላቸው ቀየሜታ ስማቸው እየተነሳ የሚገኙት ጠቅላያችንም… ያላለቀውን ግድብም ሆነ ያለቀውን ገንዘብ ከዳር በማድረስ ጥቂቶች እንደሚያሟቸው ሳይሆን ብዙሃኑ እንደሚያምናቸው ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል›› እላለሁ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close