Connect with us

Business

ግልጽ ደብዳቤ – ይድረስ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

Published

on

ግልጽ ደብዳቤ - ይድረስ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

ግልጽ ደብዳቤ – ይድረስ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ

ለጤናዎ እንደምን ሰነበቱልኝ?!

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራ ከጀመሩ እጅግ አጭር ጊዜ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የምሰጠው አስተያየት የቸኮለ
ከሆነ አስቀድሜ ይቅርታዎን እጠይቃለሁ።

በእርስዎ አመራር በከተማዋ እየተካሄዱ ካሉ ተግባራት መካከል የድህነትን ችግር ለመቀነስ፤ የጎስቋሎች ኑሮ ለማሻሻል የጀመራችሁት ጥረት ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን ስገልፅልዎ በታላቅ አክብሮት ነው።

ባለኝ ውስን መረጃ አረጋውያንን የመደገፍና የወደቀ ቤታቸውን መልሶ የመገንባት፣ የአዲስ ዓመት ስጦታ በሚል ከሕዝቡ ቁሳቁስና ገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎች መጀመራቸው ትልቅ ጅምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለአዲስ ተስፋ ቀመር የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስፈጸሚያ እና አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ አስተዳደሩ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ ሆቴል ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ በድምሩ ከ32 ሚሊየን ብር በላይ ቃል መገባቱ በአዎንታ የምመለከተው ትልቅ ክንውን ነው፡፡

አዎ! አዲስ አበባ ከአፍሪካ ከተሞች በድህነቷ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናት። በቀን አንድ ጊዜ በልተው ማደር የማይችሉ የድሀ ደሀ ዜጎችን ጨምሮ ሐሩርና ቁር እየተፈራረቀባቸው ለጎዳና እና ልመና ሕይወት የተዳረጉ ወገኖች ቁጥራቸው የትየለሌ ነው።

ከነዋሪዎቿ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በቂ የመፀዳጃ አገልግሎት በሌላቸው ጎስቋላ ቤቶች ወስጥ የሚኖር ነው። የአፍሪካ መዲና እያልን የምናቆለጳጵሳት አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የተመቸች እንድትሆን ብዙ ሥራ ይጠይቃል።

በተጨማሪም እንደሴተኛ አዳሪነት ያሉ ማህበራዊ ችግሮች የከተማዋ የዘመናት ራስ ምታት ናቸው፡፡ ከምንም በላይ የሥራ አጥነት፣ የመጠለያ (መኖሪያ) ቤት ችግሮች ህዝቡን ቀፍድደው አላላውስ ማለታቸው እውነት ነው፡፡

እነዚህና መሰል ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ ከዕለት ድጋፍ ባለፈ ከመሠረቱ ማህበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ቁርጥ አቋም
መውሰድ ይገባል፡፡ ባለሃብቶች መዋዕለንዋቸውን እንዲያፈሱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ጎን ለጎን ድህነት የመቅረፍ ዕድሉ እየሰፋ ይመጣል፡፡

ማህበረሰቡ ያለውን እንዲያካፍል፣ አቅመ ደካሞችን እንዲረዳ የሚስችል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰፋና መሠረት እየያዘ ሲመጣ ድሆች ተገቢውን ትኩረት ያገኛሉ፡፡ ማህበረሰቡ ስለመብትና ግዴታው በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚሰሩ ምግባረ ሠናይ ድርጅቶች እንዲስፋፉ ዕድል ሲሰጥ የሌብነት ችግሮች እየተቀረፉ የመንግሥት ሐብት ለታለመለት ዓላማ በቁጠባ መጠቀም ያስችላል፡፡

እናም ክቡር ከንቲባ ድህነትን ለመቅረፍ ስለጀመሩት ጥረት ተገቢውን ክብር ሰጥቼ የሚከተሉት የከተማዋ ማህበራዊ ችግሮች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጧቸው ወይንም በአሁን ሰዓት እየተሰባሰበ ባለው ድጋፍ መርሃግብር ውስጥ ልዩ ትኩረት እንዲሰጧቸው በማሰብ አነሳቸዋለሁ፡፡

የአዲስ አበባ ቁልል ማህባረዊ ችግሮች አንዱ በከተማዋ የተለያዩ ጠርዞች ሐሩርና ቁር እየተፈራረቀባቸው የጎዳና ሕይወት የተዳረጉ ወጣቶችና አረጋዊያንን ይመለከታል፡፡ እነዚህም ወገኖች ብዙዎቹ በልመና አልፎ አልፎም በወንጀል ድርጊቶች ይሳተፋሉ፡፡ ይህ መሆኑ የአፍሪካ መዲና የምናት አዲስ አበባ ገጽታ ግንባታ ጉልህ ችግር ተደርጎ ሲነሳ የኖረ ነው፡፡

አንድ ቱሪስት በነጻነት መንቀሳቀስ የማይችላባቸው ወይንም በጎዳና ተዳዳሪዎችና ለማኞች ውክቢያና እንግልት የተሞሉ ጎዳናዎች መመልከት የዕለት ተዕለት ትዕንት ሆኗል፡፡ እነዚህን የጎዳና ወገኖች አፍሶ ወደአንድ ቦታ በመውሰድ ለመርዳት መሞከር ባለፉት ዓመታት ብዙ ተሰርቶበት እምብዛም ውጤት ያላስገኘ፤ በእኔ እምነት የከሸፈ ስትራቴጂ ነው፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎች ዛሬ ሲነሱ ወዲያውኑ ይተካሉ፣ አዲዲስ ወጣቶችና አረጋውያን ወደጎዳና ይወጣሉ፡፡ ለምን ቢባል ማህበራዊ ችግሩ ሥራዬ ብሎ የሚፈታ አካል ባለመኖሩ ነው፡፡

እናም የጎዳና ወገኖቻችንን ችግሮች በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ ፕሮጀክት ያላቸውን ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች በመደገፍ፣ አስተዳደሩም የራሱን ስትራቴጂ በመንደፍ ወደሥራ የመግባቱ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝቡን በማስተባበር ጭምር በየክፍለ ከተማው ዓመታዊ በጀት ያላቸው ቋሚ የማደሪያ እና የምገባ ጣቢያዎችን በማቋቋም ቢያንስ ወገኖቻችንን ጎዳና ላይ እንዳያድሩ፣ በምግብ እጦት እንዳጎዱ፣ እንዳሞቱ ክቡርነትዎ በእርስዎ አመራር ሊከናወን የሚችል ሥራ ነው፡፡

የእነዚህ ጣቢያዎች መቋቋም የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለማስተማር፣ ከጎዳና እንዲላቀቁ ለመደገፍ የሚደረገውን አገር አቀፍ ጥረት በዘላቂነት በማገዝ ረገድም ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል፡፡ በተጨማሪም የጎዳና ወገኖች የጤና አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ፣ የስነተዋልዶ ትምህርቶችን በማስፋፋት ትልቅ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል፡፡

ክቡር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ የጎዳና ወገኖች የምገባ እና የማደሪያ እንዲሁም የጤና አግልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በአዲስ አበባ በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንዲኖር ጉዳዩ ተጠንቶ ወደተግባር እንዲገባ አመራር ይሰጡ ዘንድ እንደ አንድ ዜጋ እጠይቅዎታለሁ፡፡

አክባሪዎ
ፍሬው አበበ

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close