Connect with us

Ethiopia

አገራዊ ለውጡ ያልጎበኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት!

Published

on

አገራዊ ለውጡ ያልጎበኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት!

አገራዊ ለውጡ ያልጎበኘው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት! | ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአንጋፋነቱ የታወቀ የህትመት ሚዲያ ሲሆን ላለፉት ሰባ ዓመታት ለህዝብ መረጃ በመስጠት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ተቋሙ በመንግስት ይዞታ ስር እንደመሆኑ እጅግ ከፍተኛ ከግብር ከፋዩ የሚሰበሰብ ገንዘብ ከመንግስት ይመደብለታል፡፡

ይህ ተቋም ባሳለፍናቸው ሶስት መንግስታት ማለትም በንጉሱ፤ በደርግና በኢህአዴግ ዘመናት የአገዛዝ መሳሪያ በመሆን ቢያገለግልም ስመ ጥር ደራስያናና ጸሐፍትን በመፍጠር የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ እነ ፓውሎስ ኞኞ፣ በዓሉ ግርማ፤ብርሃኑ ዘርይሁንና የመሳሰሉ አንጋፋ ጋዜጠኞች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በስሩ የሚታተሙት አዲስ ዘመን፤ኢትዮጵያን ሄራልድ ፤አል አለም (የአረብኛ)፣ በሪሳ (የኦሮምኛ) ጋዜጦች እንደተቋቋሙበት ዓላማ መንግስትንና ህዝብን አገልግለዋል፡፡ የፕሬስ ውጤቶቹ በንጉሱና በደርግ የዲሞክራሲ ስላልነበር መንግስታቱን ፍላጎት ከላይ ወደ ታች በማውረድ እንደ ዘመኑ ፖለቲካ ለአገዛዞቹ ብርቱ ክንድ ሆነው ቆይተዋል፡፡

ከ1983 የመንግስት ለውጥ በኋላ በሽግግሩ ዘመን በወጣው የሽግግር ወቅት ቻርተር ሀሳብን የመግለጽ ነጻነት በተረጋገጠበት ወቅት ዘመኑ የሚጠይቀውን የሚዲያ ነጻነት ለማረጋገጥ ጅምር ስራዎች ታይተው የነበሩ ቢሆንም ብዙም አልዘለቀም፡፡ ነገር ግን እንደገና በ1997 አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫውን ተከተሎ የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ በነበረበት ወቅት የተለያዩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪና አባላትን በማነጋገር በወቅቱ ለተከሰተው አዲስ የፖለቲካ ብሩህ ተስፋ የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ነገር ግን የምርጫው መጨረሻ በደም አፋሳሽ ግጭት ከተጠናቀቀ በኋላ የኢትዮጵያ ፕሬስም ወደነበረበት ዋሻ ተመልሶ በአገዛዝ መሳሪያነቱ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡

ተቋሙ ስለ ጋዜጦቹ አንድም ጊዜ የአንባቢና የስርጭት መጠን ጥናት አድርጎ ስለማያውቅ ምን ያህል ተደራሽ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በየመንግስት መስሪያቤቱ በዱቤ የሚላኩት ሁሉም ጋዜጦች ሳይነበቡ በዓመት መጨረሻ በኪሎ እንደሚሸጡ ለማወቅ ብዙም ምርምር ማድረግ አያስፈልግም፡፡ አንድ ጋዜጣ ገበያ ላይ በአራት ብር ሲሸጥ፤ ለብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ግን ለአንድ ጋዜጣ ማሳተሚያ 13 ብር ይከፈላል፡፡ ለአንድ ጋዜጣ ዘጠኝ ብር ገደማ ከመንግሥት ካዝና እየደጎመ ከታተመም በኋላ ሽያጩ ያን ያህል ያደገ አለመሆኑ የበርካታ ቅን ሠራተኞች ቁጭት ነው፡፡ ችግሩ የተከሰተው ደግሞ ባለሙያው አቅም በማጣቱ ሳይሆን የበላይ አመራሩ ያለአቅምና ችሎታው በኤዲቶሪያል ሥራ ውስጥ በቀጥታ ገብቶ የሚፈተፍትበት ሁኔታ በመኖሩና ይህም ድርጊት ጋዜጠኛውን ተስፋ በማስቆረጡ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ተቋሙ የሚያገኘው ገቢ የማስታወቂያ ገበያውን በሞኖፖል መያዝ የሚችልበት ዕድል በማግኘቱ እንጂ በውድድር ስላልሆነ እንደ ታላቅ ክንዋኔ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ በልዩ ትዕዛዝ የሚስተናገዱ መንግሥታዊ ማስታወቂዎች በውድድር ይሰጡ ቢባል ተቋሙ አሁን ባለው ቁመና ለአንድ ዓመት ያህል ጊዜ እንኳን ራሱን ችሎ መቀጠል እንደማይችል ማንም ሊገምተው የሚችለው ጉዳይ ነው፡፡

በአገራችን ባለፉት ሁለት አስርታት ዓመታት ባልተቋረጠ መስዋእትነት እንዲሁም በ2008 እና 2009 በኦሮምያ፤ በአማራና በኮንሶና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች በተደረገ ትግል ኢህአዴግ ተገዶ ስልጣኑን ለለውጥ አራማጅ ሀይሎች ለቋል፡፡ ዶ/ር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ሀገራችን በትውልድ አይታው የማታውቀው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ለውጥ አምጥታለች፡፡ የመንግስትና የፓርቲ ሜዲያዎች ኢቲቪ ፤ዋልታና ፋና ብዝሃነት ሃሳቦች እያስተጋቡ የተጀመረውን ለውጥ እያሳለጡ ይገኛሉ፡፡ ከክልል ሚዲዎች ደቡብ፤አማራና ኦሮሚያ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲም እንዲሁ ከፍተኛ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ ለዚህም የሚዲያው አመራር ሊመሰገን ይገባዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ግን ገና በእንቅልፍ ላይ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ከፍተኛ አመራር ደካማና ከጋዜጠኛው ጋር ተቀራርቦ ለመስራት አቅም ያጠረው በመሆኑ ነው፡፡የተቋሙ ከፍተኛ አመራር የራሱን ደሴት ሰርቶ በሠራተኞች መካከል ወሬና አሉባልታ በማስፋፋት፣ በልከክህ እከክልኝ አግባብ ምደባና ሹመት በመስጠት የኢንዱስትሪ ሠላም እንዲጠፋ በማድረግ እድሜውን ለማራዘም ከመታተር ባለፈ ለተቋሙ እና ለሠራተኞች ዕድገት አንዳች አስተዋጽኦ ማበርከት አልቻለም፡፡ በተለይም እንደአዲስ ዘመን ያለ አንጋፋ ጋዜጣን መሠረታዊ ሥርነቀል ለውጥ በማድረግ አገራዊ ለውጡን በሚመጥን ቁመና ላይ እንዲገኝ የማድረግ ሕልም አሁን ባለው ደካማ አመራር የሚሳካ አልሆነም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሚዲያ የሀሳብ ቦታ ነው ብለው በብሮድካስት ባለስልጣን በኢቲቪና በሌሎች ተቋማት ሀሳብ አፍላቂ ተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በቦርድ አባልነት ሾመዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ፕሬስም አዲስ የቦርድ አባላት የሾሙት ሚዲያውን ብቃቱን ለማሳደግ ነው፡፡

ነገር ግን እስካሁን የቦርዱ አባላት የድርጅቱን ሠራተኞች ስለ ሚዲያው ሪፎርም ዙሪያ አለማወያየታቸው ቅሬታን እያሳደረ በመሆኑ በአስቸኳይ ሠራተኛውን ሰብስበው ማወያየት አለባቸው፡፡ ሚዲያ የሃሳብ ብዝሃነትን በነጻነት ሊያስተናግድ የሚችለው በካድሬ ሳይሆን በባለሙያ መመራት ሲችል ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲሱ ቦርድ ሠራተኛውን አነጋግሮ ፈጣን የሪፎርም ሥራ በማከናወን እንደአዲስ ዘመን ያሉ አንጋፋ ጋዜጦችን መረጃ በመስጠት ረገድ ተአማኒና ተመራጭ የሚሆኑበትን አሠራር እንዲዘረጋ፣ ተቋሙ አገራዊ ለውጡን በማገዝ ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close