Connect with us

Ethiopia

ስንት ኢህአዴግ ነው ያለው?

Published

on

ስንት ኢህአዴግ ነው ያለው?

ስንት ኢህአዴግ ነው ያለው? | ሬመንድ ኃይሉ በድሬቲዩብ

የኢህአዴግ ሰዎች ሙግት ይወዳሉ፡፡ ተቃራኒ ማሰብ የመሪነት ጥበብ ይመስላቸዋል፡፡  የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የጎርቫቾቭ ዕጣ ፋንታ ይደርሰዎታል ሲባሉ ሟርት ነው እያሉ ሲያወግዙ ኑረዋል፡፡ እንደውም አፋር ላይ በተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል የፌደራላዊ ስርዓታችን የአሸዋ ላይ ቤት አይደለም ዝም ብሎ የሚፈርሰው ሲሉ ተሳልቀውም ነበር፡፡ ይህን በተናገሩ በሁለተኛው ወር የፈሩት ነገር ከደጃፋቸው ደረሰ፡፡ የሀገሪቱን ህልውና ማስቀጠል እንደተሳናቸው በግልጽ አምነው፤ ልውጡን ለመደገፍ በሚል የዳቦ ስም የምኒልክን ቤተ-መንግሰትን ተሰናበቱ፡፡

ጠቅላይ ሚንሰትሩ የኢህአዴግ አራቱ ድርጅቶች ለየፊናቸው ጉዞ መጀመራቸውን ሲነግሯቸው አልሰማም ብለው መጨረሻቸው ኃላፊነት መሸሸት ሆነ፡፡ የዚህ ውጤቱ ሀገር ወደ ማፍረስም ተንደረደረ፡፡ እሳቸውንም ከፖለቲካ ሜዳ አርቆ ወረወራቸው፡፡ ኢህአዴግ ከዚህ በኋልም ህመሙ እንደጸነበት ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ ምኒልክ ቤተ-መንግስት የሚገቡ ሰዎች ግን ከስልጣን በትራቸው ጋር ሀቅን መካድ ይቀቡ ይመስል ይኽን እውነት አይቀበሉትም፡፡

ችግሩን እናንተ ብቻ ፈጠራችሁት የተባለ ይመስል ከዚህ ዓይነቱ ዕዳ ለማምለጥ ይጥራሉ፡፡ ጠቅላይ ሚንሰተር ዐብይ አህመድም የዚህ በሽታ ሰለባ ናቸው፡፡ አሜሪካ ላይ በነበራቸው ቆይታ ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሯል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንሰትር ኃይለማሪም ስልጣን በመለቀቂያቸው ዋዜማ ላይ የተናገሩትን ኢህአዴግ እንደ አሁኑ እራሱን ገምግሞ አያውቅም የሚል ቃል ተውሰው ያንኑ አነብንበዋል፡፡

በዚህ በኩል ህወሓት ታህድሶው ክሽፏል ይለናል፡፡ በሌላ በኩል ጠቅላያችን ባህር ማዶ አምረተው 90 በመቶው ኢህአዴግ የለውጡ አካል ነው ይሉናል፡፡ የሌላውን ፓርቲ ጥለን የህወሃትን በይፋ ታህድሶ ክሽፏል አስተያየት ብቻ ብንመለከት እንኳን በድርጅቱ ውስጥ 25 በመቶ ድርሻ ስላለው የጠቅላዩ ንግግር መጋነኑ ይገባናል፡፡

ኢህአዴግ አሁን ከትናንቱም በላይ መሰረታዊ ችግር ያለበት መሆኑን በተግባር እያሳየን ነው፡፡ የፓርቲው እህት ድርጅቶች እንቅስቃሴም ከዚህ በሽታ ለመላቀቅ የሚካሄድ ሩጫ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ብአዴን በዚህ ወር በማስተናግደው ጉባዔ ለውጡን የማይደግፉትን ጠራርጌ አስወጣለሁ የሚል ዛቻ አብዘቷል፡፡ ህወሓትም የመተዳደሪያ ደንቡን እስከማሻሻል የደረሰ ለውጥ እንደሚካሂድ ተናግሯል፡፡ ኦህዴድ መዋቅራዊ ለውጥ ለማድረግ አኮብኩቧል፡፡

የዚህ ሁሉ ርብርብ አላማው የኢህአዴግን ዕድሜ ማራዘም ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ እውነት ቢሆንም ዛሬም አንድን ባለስልጣን ጠርተን ብንጠይቀው ኢህአዴግ በፍጹም ድሎት ላይ ነው የሚል ምላሽ እንደሚሰጠን እሙን ነው፡፡ እንዲህ ያለውን መካካድ ሳይ ሁለት ነገሮች ወደ አዕምሮየ ይመጣሉ፡፡ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ሰዎች ዛሬም ህዝቡን የፖለቲካ ሀሁ የማያውቅ አድረገው የናቁት ይመስለኛል፡፡ ሁለተኛው መታመሙን ማመን ያልቻለ በሽተኛ እንዴት ከህመሙ የሚፈውሰውን መድሃኒት በአግባቡ ተጠቅሞ ሊድን ይችላል እላለሁ፡፡

አንድ የፖለቲካ ድርጅት አደጋ ውስጥ መግባቱ በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ችግሩ ከዚህ ለመውጣት ያለው ያለው ዝግጁነትና የሚወጣበት መንገድ እንዴት ነው የሚለው ነው፡፡ የታላቁ ሀገር መሪ ዶናልድ ትራምፕ ፓርቲ ሪፐብሊካንም ሀገር እየመራ በተደጋጋሚ ችግር ውስጥ ሲገባ ታይቷል፡፡ ግን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ችግሩን እየፈታ ነው፡፡ የዝሙባቤው ዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲም ከአደጋ ዞን ለመውጣት እየጣረ ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካም መሪ ፓርቲዋ እየተተራመሰ እሷ ግን ተረጋግታ ጉዟዋን ቀጥላለች፡፡

ኢህአዴግ ግን ማህበረሰቡን ፈርቶ ታማሚን ልጁን ቤት እንደሚያውል ቤተሰብ ችግሮቹን ፓርቲው ውስጥ ቆልፎባቸዋል፡፡ ማህበረሰቡ ፓርቲው ችግር ገጥሞታል የሚል ጥያቄ ሲያነሳም ነገሩን ከማብራራት ይልቅ አይኔን ግንባር ያድረገው ማለት ይቀናዋል፡፡

ቤተ-መንግሰት ሲገቡ ውሽትን ይቀቡ ይመስል የዛ መንደር ሰዎች የሚታይ የሚሰማውንም ይክዳሉ፡፡ ሌላ ኢህአዴግ ያለ ይመስል የእነሱ ኢህአዴግ በአስገራሚ ሁኔታ መቀየሩን ይለፍፋሉ፡፡ እንዳፋችሁ ያርገው ከማልት ውጭ ሌላ ተስፋ ከምንስ ይገኛል? ከምንም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close