Connect with us

Ethiopia

መገንጠል የሚያውደው ፖለቲካ!

Published

on

መገንጠል የሚያውደው ፖለቲካ!

መገንጠል የሚያውደው ፖለቲካ! | ሬመንድ ኃይሉ

የኢትዮጵያን ፖለቲካ መገንጠል እያወደው ነው፡፡ የኦነጉ ቃላ አቀባይ ቶሌራ አዴዳ ከራዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ጋር በነበራቸው ቆይታ ድርጅታቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው እስከ መገንጠል የሚል መርሁን ይዞ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮ ሶማሌ ክልል የኮሚኒኬሽን ሀላፊ ኢድሪስ ኢብራሂም ከቢቢሲ ሶማሌኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ ክልሉን መገንጠል ምን ነውር አለው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ጥቂት የአማራ ፖለቲካ ልሂቃንም ኢትዮጵያዊነት አልበጀንም የራሳችንን ዕድል በራሳችን ዕድል መወሰን አለብን የሚል ስብከት ከጀመሩ ውለው አድረዋል፡፡ የኢትጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመገንጠል ሃሳብ ብርቅ አይደለም ፡፡ኦብነግ ኦጋዴንን ለመገንጠል አዕላፍ ዘመናትን ታግሏል፡፡ ህወሓት ለወራትም ቢሆን ትግራይን እገንጥላለሁ የሚል ሃሳብ ይዞ ደፋ ቀና ብሏል፡፡ ኦነግ አራት አስርታትን ስለመገንጠል ሲያዜም ኑሯል፡፡

ህዝቡ ጋር ያለው ዕውነታ ግን እሱ አይደለም፡፡ የኦጋዴን ህዘብ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ወቅት ከማንም በፊት ለሀገሩ መስዋዕት ሁኗል፡፡ የትግራይ ህዘብ የኢትጵያን ክፉ ላለማየት እራሱን ሰውቷል፡፡ ኦሮሞ ከአድዋ እሰከ ባድመ ከሀገሬ በፊት ልሙት ብሎ ላይመለስ አሸልቧል፡፡ እንዲህ ያለው የትናት ታሪክ ግን ዛሬ ካልተሰራበት ያሸዋ ላይ ቤት እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡

የዛሬ ዘመን ፖለቲካ እንደ ትናንቱ አይደለም፡፡ ትናንት ሶማሌ ከኦሮሞ ሲጣላ የኢሳ ጎሳ ከቦረና የሚያደርጉት ግጭት ተደርጎ ይወሰድ ነበር፡፡ መተከል ላይ ግጭት ሲፈጠር ጉምዝ ከጎጃም ጋር ስለመጣላቱ ካልሆነ አማራ በጉምዝ ተደፈር የሚል ወሬ አልነበረም፡፡ አሁን ጨዋታው ተቀይሯል፡፡ የኢሳና ሀዌ ጎሳ በቦረና መጠቃት የሁለት ጎሳዎች ግጭት ሳይሆን የድፍን ኦሮሚያና ሶማሌያ ፖለቲከኞች ጸብ ሁኗል፡፡

ሶማሌ ተደፈረ፡፡ ኦሮሞ ተዋረደ በሚል ተረክ ጥላቻና ቂም በቀል በፌስቡክ ይረጫል፡፡ የጉምዝና ጎጃሜ ጸብ አማራን ለመቀስቀስ መሳሪያ ሁኖ የክልሉ ወጣት በጉምዝ ላይ ጥርስ እንዲነክስ ያስገድዳል ፡፡በዚህ ጎዳና ዕርቁ መጓዝ አንችልም፡፡ ትናንት ይችን ሀገር ፖለቲከኛው ሳይሆን ህዝቡ እንዳትፈርስ አድርጓታል ፡፡ ዛሬም ይህ ህዘብ በአንድነቱ አይከራከርም ብለን ካሰብን ግን የምንሳሳት ይመስልኘል፡፡

ትናንት የዘራናቸው ልዩነቶች አሁን አሽተው ሀገር የመገዳደር አቅም አዳብረዋል፡፡ የኦጋዴን ህዝብ ትናንት ለኢትዮጵያዊነቱ መሥዕዋትነት ስለከፈለ አሁንም ይከፍልልናል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ይመስለኛል ፡፡ ኦሮሞ፣ አመራ፣ ትግራይ፣ አፋርም ለዚች ሀገር ዘብ የሚቆሙት የእነሱ ቦታ በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የት እንደሆነ ካረጋጋጡ በኋላ መሆኑ አያከራክርም፡፡

ይህ ደግሞ የሀገራችን አንድነት በትናንት ታሪክ ወደፊት የሚይጓዝ ሳይሆን በዛሬ የሚመራ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ አማራው በትግራይ ህዝብ ውስጥ ያለው ቦታ ኦሮሞው በሱማሌው ውስጥ ያለው ቦታ በጥላቻ የተሞላ ከሆነ ነጋችን ያስፈራል፡፡ የራስን ዕድል በራስ መወሰን እሰከ መገንጠል መብትም ህገ-መንግስታዊ ሆነም አልሆነም ወደ መለያየቱ እናማራለን፡፡ ከላይ ሩቅ የመሰለን የፖለቲከኞቹ ሟርትም ወደ እውነት ይቀየራል፡፡

እዚያ እንዳንደርስ ግን ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ እኔ አንድን ብሄር የሚያጥላላ ተግባርና ወሬ እየፈጸምኩ የፈለገውን ያህል ስለአንድነት ባወራ ሀገር ከማፍረስ ታሪካ ውርደት እራሴን ላርቅ አልችልም ፡፡እናም ኢትዮጵያዊነት እኔና አንተ ነን፡፡ ከዛም ከፍ ሲል እኛ እና እነሱ ነን ፡፡ እኛ ከተግባብን ሀገር የማዳን አቅም አለን፡፡ ከዚያ ውጭ ግን ሁሉም ነገር ጨለማ ነው፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪል አቋም አያንጸባርቅም)

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

 

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close