Connect with us

Ethiopia

ፌርማታ አልባው የኢትዮ ሱማሌ ፖለቲካ!

Published

on

ፌርማታ አልባው የኢትዮ ሱማሌ ፖለቲካ!

ፌርማታ አልባው የኢትዮ ሱማሌ ፖለቲካ! | ይነገር ጌታቸው በድሬቲዩብ

የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሰትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በፖለቲካ ሕይወታቸው ሁሌም የሚገርማቸው ጉዳይ የሱማሌ ፖለቲከኞች በነሀሴው ጉባዔ ላይ መሳተፍ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ይህ የጠቅላይ ሚንስትሩ አግራሞት ከሁለት ነገሮች የተቀዳ ይመስለኛል፡፡ የመጀመሪያው የሱማሌ ፖለቲከኞች ከኢትዮጵያ በመንፈስ ከራቁ በርካታ አመታት ያስቆጠሩ በመሆናቸው ነው፡፡

የምዕራብ ሱማሊያ ነጻነት ግንባርን መስርተው ለኦጋዴን ነጻነት ሲፋለሙ የኖሩት ኃይሎች በርግጥም ህገ-መንግስት በማጽደቅ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን ተዋከይ መላካቸው ሊያስገርም ይችላል ፡፡ ሁለተኛው የቀድሞው ጠቅላይ ሚንሰትሩ አግራሞት ምንጭ በሱዳን አደራዳሪነት የሱማሌ ፖለቲካ ኃይሎች በሽግግር መንግስቱ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ሲደረግ የነበረው ሂደት ተስፋ አስቆራጭ ከመሆኑ የሚመነጭ ይመስላል፡፡

በርግጥም የወቅቱ የኦብነግ ሊቀመንበር ሸክ ኢብራሂም አብዱላሂ ማኽ የሽግግር ቻርተሩ እንዲቀበል ለቀረበለት ጥያቄ ቻርተሩ ለኢትዮጵያውያን እንጅ ለኦጋዴን ህዝብ ምኑ ነው ማለቱ ለእንዲህ ያለው አግራሞት ጉልበት እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

ሳዓውዲ አርበያ መቀመጫውን ያደረገው አብዱላሂ ማህ በሱዳን በኩል ቢለመንም አሻፈረኝ ብሎ ወደመጣበት ተመልሷል፡፡
ሀገር ከመረከቡ የኢትዮጵያን አንድ ሶስተኛ የቆዳ ስፋት እንደሚያጣ የገባው ኢህአዴግ በጊዜው ወደ ሁለተኛው አማራጭ ፊቱን ማዞሩ የማይቀር ነበር፡፡ በዚህም በሱማሌ ህዝብ አነስተኛ ቅቡልነት ያለውን የምዕራብ ሱማሊያ ነጻነት ግንባርን ወደ ማግባባት አዘነበለ፡፡ የወቅቱ ፕሬዘዳንት አቶ መለስ ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረትም የፖለቲካ ድርጅቱ ከነጻ አውጭነት ስያሜው ወጥቶ የምዕራብ ሱማሊያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚል መጠራት ጀመረ፡፡

ምሱዴፓ በነሀሴው ኮንፈረስ ላይ ሁለት ወነበር ያገኘ ሲሆን የኢሳና የጉረጉኸ ፖለቲካ ድርጅቶችም ሱማሌን በመወከል ተጨማሪ መቀመጫን አግኝተዋል፡፡ ይህ ተሳትፎ ግን አስራ ሦሰት ያህል ጎሳዎች ላሉት የሱማሌ ክልል በቂ የሚባል አልነበረም፡፡ ይሁን እንጅ የሱማሌ ህዘብ የክልልነት ጥያቄው ዕውን ሁኖ በ1985 ዓ.ም የወሰን ማካለል ሰራ ሲጀመር ኦብነግ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አሳወቀ፡፡

በወቅቱ የድርጅቱ ቃል አቀባይ የነበረው አብዱላሂ ሞሐመድ ሰዒድ ወደ አዲስ አበባ መምጣትም በኢህአዴግና በሱማሌ ፖለቲካ ልሂቃን መካከል ያለውን ልዩነት ለማርገብ ትልቅ አስተዋጾ ነበረው፡፡ ኦብነግ በፌደራሊዝሙ ሐሳብ ላይ እንደሚሰማማና በተግባር አይቶት ከመዘነ በኋላ ከኢህአዴግ ጋር ለመስራት እንደሚወሰንም አስተወቀ፡፡ በኢህአዴግ ሰፊ ድጋፍም በጥር ወር 1985 ዓ.ም ጋርቦ ላይ ብሄራዊ ኮንፈርስ አካሂዶ በይፋ ስራ ጀመረ፡፡

ኦብነግ ኮነፈርንስ አካሂዶ ሀገራዊ ፓርቲ ሁኖ ለመንቀሳቀስ ዝግጁ መሆኑን ቢገልጽም የድርጅቱ መሪ የነበረው ሸክ ኢብራሂም ግን ከኢህአዴግ ሰዎች ጋር መገናኘት አልፈለግም የሚል አቋም ያዘ፡፡ እነዲህ ያለ ተቃርኖ ያሳሰበው የሽግግር መንግስቱም ኦብነግን በአይነ ቁራኛ አየተከታተለ ጉዞውን ቀጠለ ፡፡ መንግስት አልባ በሆነችው ሱማሊያ በኩል መውጫ መግቢያውን ያደረገው የሪያድ ዩንቨርስቲ መምህሩ ሸክ ኢብራሂም በጊዜ ሂደት አለማው ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡

የሽግግር መንግሰቱን አለሁ እያለ ለነገ ትግሉ የሚረዳውን ወታደራዊ ኃይል ማደራጀት ጀመረ፡፡ እንዲህ ያለው የኦብነግ ሀሳብ በመሀል ሀገሩ ፖለቲከኛ መደናገርን ቢፈጥርም የምራጫ ወቅት በመቃረቡ ለውሳኔ አዳጋች ነበረ፡፡ በሁለት ቢለዋ የሚበላው የኦብነግ አመራር ግን በ1987 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ተሳትፎ በማድረግ ከፍተኛ ድምጽን አገኘ ፡፡ ኦጋዴን በሚል የሚጠራውን አከባቢም ሱማሌ ክልል ብሎ ለመጥራት መወሰኑን አስታወቀ፡፡

የወቅቱ ጠቅላይ ሚስትር ታምራት ላይኔ በድሉ ማግስት ወደ ድሬ ደዋ አቅነተውም ከዚህ በኋላ ሱማሌ ኢትዮጵያዊ ዜገነት አግኝቷል ሲሉ ተደመጡ ፡፡የክልል መንግስት መስረታ ውስጥ የገባው ኦብነግ ድሬደዋን ዋና መቀመጫ አድርጎ መረጠ ፡፡ ይሁን እንጅ ድሬደዋ ላይ የኦሮሚያ ይገባኛል ጥያቄ በመነሳቱ ለጊዜው ጎዴን ምርጫው አደረገ፡፡

ክልሉን የሚመራ ምክር ቤት ሲቋቋም ግን አካሄዱ አላስደሰተኝም ያለው ሸክ ኢብራሂም ክልሉን ከመምራት አፈገፈገ፡፡ በዚህ የተነሳም አብዱላ ሞሐመድ ሰዒድ የክልሉ ርዕሰ መሰተዳደር ሁኖ ተመረጠ፡፡ በነገሩ የተደሰቱት አቶ መለሰም አብዱላሂ ሞሐመድን አዲስ አበባ አስጠርተው በሁሉም ነገር ከጎኑ እንደሚሆኑ ነገር ግን የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር የሚለው ስያሜ ወደ ፓርቲነት እንዲቀየር አሳሰቡት፡፡

ሱማሌ ክልል ከኦጋዴን በተጨማሪ ሌሎች ጎሳዎች እንዳሉበት በማሳሰብም የስሙ መቀየር ላይ ድርድር እንደሌለ ቀጭን ትዕዛዝ ሠጡ፡፡ አመረኛ መናገር የማይችለው አብዱላሂ በጊዜው በሁለት አጣብቂኝ መሐል መገኘቱ እውነት ነበር፡፡ በአንድ በኩል የሽክ ኢብራሂም ረጅም ገመድ እግሩ ላይ እንደታሰረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ወታደራዊ ኃይሉ በእጃቸው ያለው አቶ መለስ ምን እያሰቡ አንደሆነ ዕርግጠኛ አይደለም፡፡

በዚህ ምክንያትም ልቡ የወደደውን ሊያደርግ ሲነደረደር አቶ መለስ ቀደሙት፡፡ ክልሉን ለመገንጠል ሲነቀሳሰቀስ ነበር የሚል ታፔላ ለጥፈው ዘብጥያ ወረወሩት፡፡ ሱማሌ ክልል ዳግም ከኢህአዴግ እጅ መውጣት ጀመረች፡፡ ይህ ያሰደነገጣቸው የምኒልክ ቤተ-መንግሰት ሰዎች የዛያድ ባሬ ጦር ኃይል አብራሪ የነበረውን ሀሰን ጀር ኸለንንን በረጅም ገመድ አስረው ሂደ ሱማሌን ጠብቅ ሊሉት ፈለጉ፡፡ የሀሰን ጀረ ስልጣን ግን ከቀደመውም የከፋ ሆነ፡፡ ኦብንግ በህገ-መንሰቱ የተሰጠኝን የመገንጠል መብት የመጠቀም መብት አለኝ የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄን ለኢህአዴግ ማሰማት ቀጠለ፡፡ ህገ-መንግስቱ ከጸደቀ ከሦስት ወራት በኋላም ጂግጂጋ ላይ በክልሉ ምክር ቤት በኩል የመገንጠል ጥያቄን በይፋ አጸድቆ ለፌደራል መግስቱ ላከ፡፡

በወቅቱ በተለያዩ አከባቢዎች የኦብነግን የመገንጠል ሃሳቡ የደገፉ ሰለፎች የተካሄዱ ሲሆን በዋርዴሩ ሰልፍ ላይ የተገኙት የኦብነጉ መሪም በመከላክያ ሀይሉ ቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ሸከ ሀሰን ለቀናት ማረሚያ ቢቆዩም ደም አፋሳሽ በሆነ የተኩስ ልውውጥ ከማረሚያ ሊያመልጡ ቻሉ፡፡ ይህ የታሪክ ወቅት ኦብነግ በሰላመዊ መንገድ መታገል ርባና ቢስ መሆኑን የተረዳበት ጊዜ ይመስላለ፡፡ በዚህ ምክንያትም ዋናው የኦብነግ አመራር ሀገር ጥሎ በወታደራዊ ትግል ነጻነቱን ለማግኘት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡

የቀረው አንጃ ተስፋ ሳይቆርጥ ፌደራሊዝሙን ለመተግበር ደፋ ቀና ማለትን ምርጫው አደረገ፡፡ የምኒል ቤተ-መንግስት ሰዎች በሱማሌ ክልል የፖለቲካ ልሂቃን ተስፋ ቢቆርጡም አዲስ ርዕሰ መሰተዳደር ለመሾም ግን ወደ ኋላ አላሉም፡፡ እናም በሁለት አመት ውስጥ ሦስተኛውን የክልሉ ፕ/ት አብዱራሐማን ኡጋስ ሞሐመድን መሾማቸው ተሰማ፡፡

አቶ መለስ በወቅቱ ወደ ሀረር በማምራት ለክልሉ ፖለቲከኞች ህገ-መንግስቱ ለህዝቡ እንጅ ለእናነተ ለፖለቲካ ነጋዴዎች አይደለም የመገንጠልን መብት የፈቀደው የሚል ማሳሰቢያን አሰተላለፉ፡፡ በዚህ ሳያበቁም የክልሉን የፖለቲካ ችግር ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ከኦብነግ የተነጠለውን አንጃ ከምዕራብ ሱማሌ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ጋር እንዲዋሀድና ለክልሉ መረጋጋት እንዲሰራ ምክር አቀረቡ፡፡

ይህን ባሉ በማግስቱም የኢትዮጵያ ሱማሌ ዴሞክራሲያዊ ሊግ ተመሰረተ፡፡ አህመድ ማካሂል ሀሰንም አዲሱ ሊቀመንበር ተደርጎ መሰይሙን ተከትሎም ክልሉን ማሰተዳደር ጀመረ፡፡ በዚህ ፊታቸውን የነጩት የቀድሞው ርዕሰ መሰተዳደር አብዱራሃመን ኡጋስ ሞሃመድም ስልጣናቸውን ለማስመለስ መሳሪያ ታጥቀው ደፋ ቀና ሲሉ በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡ ኢሱዴሊም ሱማሌን ለማረጋገት ቢጥርም የሚሳካለት አልሆነም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ከግለሰባዊ ለውጥ ይልቅ የፓርቲውን አደረጃጀት መቀየር አስፈላጊ ነው ብለው በማመናቸው ሱማሌ ክልል ከሌላ ፓርቲ ጋር ተዋወቀ ፡፡ የሱማሌ ህስዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የትናንት ታሪክን ሊያሽር አሀዱ ብሎ ጉዞ ጀመረ ፡፡ ከሀዲር ሙዓለምም የድርጅቱ መሪ ሁኖ ብቅ አለ፡፡ ጉሳ ተኮሩ የሱማሌ ፖለቲካ ግን ለዚህ ሰውም የሚበጅ አልሆነም ፡፡ እናም ሰዎች እየወጡ እየወረዱ አብዲ ሞሐመድ ኡመር ጋር ስልጠን ሲከንፍ ደረሰ፡፡

አብዲ ኢሌ በሚሌ ስም የሚታወቀው የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ዘርፍ ሀላፊ የነበረ ሰው የጅግጅጋው ቤተ-መንግስት ተቀምጦ ከትናንት የተሻለ ታሪክን ለመስራት ለምኒልክ ቤተ-መንግስት ሰዎች ቃል-ገባ፡፡ በመከላክያ ሀይሉ ታግዞም የክልሉን ሰላም በአሰገራሚ ሁኔታ ለማረጋጋት ቻለ፡፡ የሱማሌ ክልል ነዋሪዎች ለአፍታም ቢሆን ከጥይት ባሩድ ሽታ ለመራቅ ታደሉ፡፡ ከዲያስፖራው ጋር በፈጠረው ግንኙነትም ጂግጂጋን ከታዳጊ ክልል ከተሞች በተሻለ ሁኔታ እንድትለማ አደረገ፡፡

የኢህአዴግ ሰዎች አብዲን አመኑት፡፡ በረጅም ያሰሩት ገመዳቸውን በጥሰው ያሻህን አድርግ አሉት፡፡ አብዲ ሞሐመድ አላመንም፡፡ በክልሉ ፈላጭ ቆራች ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡ የሱማሌ ህዘብ ታሪካዊ መሪ ነኝ ብሎ ታሪካዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ ባተለ፡፡ ከባቢሌ እሰከ ሞያሌ የዘለቀውን የሱማሌና የኦሮሚያ ክልል የወሰን ውዝግብ ለመፍታት በኃይል የታጀበ አማራጭን መጠቀም ምርጫው አደረ፡፡

አብዲ ሞሃመድ ኡመር ዛሬ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል፡፡ በአንድ በኩል አሁን ያለው የምንሊክ ቤተ-መንገስት ሰው የሾመው አይደለም፡፡ ከላይ አንደጠቀስኩት ጂግጂጋ ቤተ-መንገስት ለመግባት ቡራኬው ያለው አዲስ አበባ ላይ ነው፡፡ በሌላ በኩል የጎሳ ፖለቲከኞች አጋጣሚውን ተጠቅመው ከስልጣን እንዲወርድ መወትወታቸውን ቀጥለዋል፡፡

27 ዓመት ሙሉ ጊዜያዊ ጥገና ሲደረግለት የኖረው የሱማሌ ክልል ፖለቲካ ዳግም ወደኋላ ሊመልስ በቋፍ ላይ ይገኛል፡፡ አብዲ ሞሐመድ ኡመር ከዚህ በፊት ክልሉን እንደመሩት 11 ርዕሰ መስተዳደሮች መጨረሻው ዘብጥያ ወይንስ ሙገሳ የሚለው ግን ገና ያለየለት ጥያቄ ይመስላል፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የቴሌያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close