Connect with us

Ethiopia

ተደምረን ሀገራችንን ወደ ላቀ እድገትና ብልፅግና እናሸጋግራለን – ኢህአዴግ

FanaBC

Published

on

ተደምረን ሀገራችንን ወደ ላቀ እድገትና ብልፅግና እናሸጋግራለን - ኢህአዴግ

የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር /ኢህአዴግ/ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ አወጥቷል።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።

ድርጅታችን ኢሕአዴግ ለሶስት አስርት አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሀገርን የመምራት ሃላፊነት ተረክቦ በሁሉም መስክ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በእነዚህ አመታት ከዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መስመር የሚቀዱ የለውጥ ስትራቴጂዎችን ነድፎ መላውን ህዝብ በማረባረብ መተግበር ችሏል፡፡ በዚህም ሀገራችን ለዘመናት ስትታወቅበት የነበረውን ረሃብ፣ ጦርነትና ኋላ ቀርነት ከመሰረቱ ለመለወጥ የሚያስችሉ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡

ይህንና የመጡ ለውጦች ሁሉን አቀፍ አለመሆናቸውና የህዝቡን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣ ፍላጎት ማርካት ያለመቻላቸው ብሎም ከራሱ ከድርጅታችን ውስጥ በመነጩ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ባህሪዎች የተነሳ ካለፉት ሁለትና ሶስት አመታት ወዲህ በሀገራችን ከፍተኛ አለመረጋጋቶች ሲከሰቱና ያልተገባ ዋጋ ሲያስከፍሉን ቆይተዋል፡፡

ኢህአዴግ የመሪነት ሚናው በከፍተኛ ሁኔታ እየተጓደለና መርህ ወደ መልቀቅ እየተጓዘ መሆኑን በጥልቅ ተሃድሶ በሚገባ ገምግሟል፡፡ በግምገማው የተለዩ ችግሮችን ግዝፈትና አስከፊነት በመረዳትም ሰፊ የማስተካካያ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ በሀገራችን የተጀመረውን ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ለማሳለጥ ብሎም ረጅሙን የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት የአመራር ለውጥ በማድረግ ወደ ተጨባጭ ስራ ገብቷል፡፡

አዲሱ አመራር የኢሕአዴግ ስራ አስፈፃሚና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባስቀመጡት አቅጣጫ ብሎም ባደገና በጎለበተ አስተሳሰብ በመመራት ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም እጦትና ሲስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን በጥቂት ጊዜያት በመቅረፍ በአንድነት፣ በፍቅርና በመደመር እሳቤ ሀገራችንን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ እየለወጣት ይገኛል፡፡ ሀገራችን አንጻራዊ መረጋጋት ማግኘት የቻለች ከመሆኗም ባሻገር መላ ህዝቦቿ ለቀጣይ ለውጥ ተስፋ የሰነቁባት መሆን ችላለች፡፡

ኢሕአዴግ ለብልሽት የዳረጉንን አላስፈላጊና ከድርጅታችን ባህሪ ውጭ የሆኑ ባዕድ አስተሳሰቦችንና ድርጊቶችን ለይቶ በመሰረታዊነት ወደ ማስተካከል የተሸጋገረበት ሁኔታም ተስተውሏል፡፡ ለአብነት የህግ የበላይነትን በማስከበር ሽፋን ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ሲፈፀምባቸው የነበሩ ተቋማት በግምገማ ተለይተው ሪፎርም እንዲደረጉና በአመራርም በተቋምም ደረጃ እንዲስተካከሉ ተደርገዋል፡፡

የዜጎች ሰብዓዊ መብት ቅድሚያ ተሰጥቶት በማረሚያ ቤት ተፈርዶባቸው የሚገኙና ጉዳያቸው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በይቅርታና በምህረት እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ ይህ ታራሚዎችን ነፃ የማውጣት ጉዳይ በተለያዩ ሀገራት ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያማከለ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋትም የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በውጪ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በሰላማዊ መንገድ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ተደርጓል፤ ጥሪውን ተቀብለው የገቡም አሉ፡፡

በተጨማሪ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነትና ወዳጅነት ለማጠናከር በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም የባህልና የታሪክ ቁርኝት ካለው የኤርትራ ህዝብ ጋር ሰላምን ለመመለስ የኢሕአዴግን ስራ አስፈፃሚ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ የድርጅታችን ሊቀመንበር ያቀረቡት የሰላም ጥሪ በኤርትራ መንግስት ተቀባይነት በማግኘቱ በሀገራቱ መካከል ታሪካዊ፣ ጊዜ የማይሽረውና ከአፍሪካ አልፎ ለመላው አለም አርዓያ የሆነ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡ በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ በድርጅታችን አመራርነት ተፈጥሮ የነበረው ጠባሳ እንዲሽር የሚያስችሉ ርምጃዎችም በመወሰድ ላይ ናቸው፡፡

ባለፈው ሳምንት የለውጡ መሪ የሆኑት የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ ዶ/ር አቢይ አህመድ በአሜሪካን ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኖች ጋር በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ባደረጉት ውይይትም በእጅጉ ተራርቆና በተለያየ ፅንፍ ላይ ቆሞ ሲወቃቀስ በነበረው ዲያስፓራ መካከል ያለውን የጥላቻ ግንብ አፍርሰዋል፡፡ እነዚህ የአንድነትና የመደመር መድረኮች በመንግስትና በዲያስፖራው መካከል ለሀገር ልማት በጋራ ለመስራት መግባባት የፈጠሩ ናቸው፡፡ በውጪ የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ለሀገር ልማት የሚጠበቅባቸውን ድርሻ ለመወጣትና የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታቸውን ገልፀዋል፡፡ መድረኮቹ ለረጅም ጊዜ ተሞክሮ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ያልተቻለበትን ሀገራዊ መግባባት የመፍጠር አላማ ከማሳካት አንፃርም ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ሆነው በታሪክ የሚመዘገቡ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ ኢሕአዴግ በጥልቅ ተሃድሶ የለያቸውን ችግሮች በጊዜ የለኝም መንፈስ እየፈታ ህዝባችንን ተስፋ ያስቆረጡ ችግሮችን በማስወገድ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከመቼውም ጊዜ በላይ ሌት ከቀን ያለእረፍት እየሰራ ይገኛል፡፡ እነዚህ በድርጅታችን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የሀገራችን ህዝቦች በድርጅታችንና በመንግስት ላይ ያላቸውን እምነት በእጅጉ ከማሳደጋቸውም አልፎ በሁሉም እንቅስቃሴያችን ከጎናች እንደሚሆኑ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ አቋሙን እንዲገልፅ አድርገውታል፡፡

እስካሁን በተመዘገቡ ድሎች የመላው የሀገራችን ህዝቦች ድጋፍና ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ድርጅታችን ጠንቅቆ የሚረዳው ነው፡፡ በቀጣይ እነዚህን ድሎች ጠብቆ ለመዝለቅና አዳዲስ ስኬቶችን መጎናፀፍ እንችል ዘንድ ይሄው ወደር የሌለው የሀገራችን ህዝቦች ድጋፍ አብሮን እንደሚዘልቅ ኢሕአዴግ ሙሉ እምነት አለው፡፡

ተደምረን ለላቀ ድል እንተጋለን!!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close