Connect with us

News

የዓለም የጦር የበላይነትና አስፈሪው ፉክክር

Published

on

የዓለም የጦር የበላይነትና አስፈሪው ፉክክር

እኤአ ከ1990ዎቹ ወዲህ በወታደራዊ ዘርፍ የዓለምን የበላይነት ተቆጣጥራ ያለችው አገር አሜሪካ የሩቅ ምስራቅ አገሪቷ ቻይና እንዲሁም የቀድሞ የሶቭየት ህብረት የአሁኗ የቭላድሚር ፑቲን አገር የሆነችው ሩሲያ እየተቀናቀኗት መምጣታቸው ለአሜሪካውያን አሳሳቢ መሆኑ አልቀረም።

ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ በአውሮፓና ኤስያ በመሬትና በአየር ወታደራዊ ቦታዎችን መያዝ መቻሏ በሌሎች ሃያላን አገራት ላይ የበላይነትን እንድትቆጣጠር የረዳት አሜሪካን የበላይነቷን ለማስቀጠል ከስድስት መቶ ቢሊየን ዶላር በላይ በመመደብ እየተንቀሳቀሰች እንደምትገኝ ይታወቃል።

አሜሪካ ለመከላከያ ሃይሏ የቻይናን ሦስት እጥፍና የሩሲያን ስድስት እጥፍ ወጪ ብታወጣም አብዛኛው ወጪዋ የሚውለው በኢራቅና ሶሪያ የሚንቀሳቀሰውን ሽብርተኛ ቡድን አይ ኤስን ለመዋጋት ነው። የአሜሪካን የጦር ሃይሎች በሌሎች አገራት ምድር በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ለሚያደርጉት ግዳጅ ይውል ዘንድ የሚያወጡት ወጪ መብዛቱ ችግር እያመጣ መሆኑን የሚናገሩት በራንድ ትብብር ማዕከል የመከላከያ ጥናት ከፍተኛ ባለሙያ ዴቪድ ኦክማን ናቸው።

በአንፃሩ ቻይናና ሩሲያ ያላቸውን የመከላከያ አቅም በማሳደግና ዘመናዊ በማድረግ ወታደሮቻ ቸውንና የጦር መሳሪያቸውን ጥራትና አዳዲስ የጦር መሳሪ ያዎችን በማምረት መጠመዳቸው ቀጣይ ጊዜያትን በበላይነት ለመቆጣጠር ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል።

በተለይም ባለፉት አስራ አምስት ዓመታት በቻይና እየታየ የመጣው ወታደራዊ ለውጥ ለአሜሪካ አስደንጋጭ እንደሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። ባሊስቲክ ሚሳዔል፤ የጦር መርከቦችና የኤሌክትሪክ የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ በዘመናዊ ወታደራዊ ግንባታ ላይ የምታወጣው ወጪና ትኩረት መጨመሩ የበላይነቱን እንደምትረከብ ማሳያ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ። ያም ሆኖ ወታደራዊ አጥኚዎቹ እንደሚናገሩት የኤሽያ ፓሲፊክ አካባቢን ቻይና ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት እንጂ አሜሪካንን ለመቀናቀን እንዳልሆነ ያስቀምጣሉ።

በአዲሱ አሜሪካን ሴኪዩሪቲ ምርምር ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ሄሪ ሪክሳ እንደሚሉት በአሜሪካና ቻይና መካከል ልዩነቱ ዓለምን አና ቀጣናን መቆጣጠር ቢሆንም የአሜሪካንን የሎጀስቲክስና ኮሚኒኬሽን ማጥቃት የሚያስችል የሳይበር ሲስተም እንዲሁም የፀረ ሚሳዔሎችን ጨምሮ በእጇ ማስገባቷን ተከትሎ አደጋው የከፋ ይሆናል።

በዓለም አቀፍ የስትራቴጂ ምርምር ተቋም እንደተነገረው የቻይና የአየር ባየር የጦር መሳሪያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እድገት እያሳየ መምጣቱ ኤፍ 35ና ደጋፊ የጦር መሳሪያዎችን ለማንቀሳቀስ አስቸጋሪ እንዲሆን አድርጎታል። በሌላ በኩል ሩሲያ አሜሪካ በአውሮፓና በኤሽያ ያላትን የበላይነት ለመቀነስ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለመስራት በጥረት ላይ እንደምትገኝ ሲነገር፤ በተለይም የኒውኩሌር ጦር መሳሪያዎቿን ማዘመንና የአሜሪካንን የሚሳዔል መከላከያ ሲስተም በቀላሉ ማለፍ የሚችል መሆኑ አደጋው የበዛ ሆኗል ተብሏል።

እኤአ በ2016 የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን « እያንዳንዱን ጉዳይ ማብራራት አልፈልግም ነገር ግን የጦር ሃይላችንና መከላከያችንን በዘመናዊ መልኩ እያደራጀን ነው፤ ተናግረነው ነበር አድርገነዋል» ያሉትን ያስታወሱት የመካከለኛው የስትራቴጂክና የዓለምአቀፍ ጥናት የብሔራዊ ደህንነት ተቋም ተንታኝ ቶኒ ከርሉስማን ናቸው። የሩሲያ ጦር መሳሪያ መጠናከር ለአሜሪካ አሳሳቢ መሆኑንም ተንታኙ ያስቀምጣሉ። ቲ 14 የተባለው የጦር መሳሪያ ቀጣዩ የጦርነት ጊዜያትን የሚወስን ቴክኖሎጂ መሆኑንና በሩሲያ እጅ መገኘቱ ለሃያሏ አሜሪካ ከባድ ፈተና መሆኑን ተናግረዋል።

ቻይናውያን በኢኮኖሚ ዘርፉና በወታደራዊ መስኩ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሲሆን ሩሲያም የቻይናውያንን መንገድ በመከተል የጦር መሳሪያዎቿንና ወታደራዊ አቅሟን በዘመናዊ መንገድ ለማሳደግ ስትል የምታወጣው ወጪ ኢኮኖሚዋን እየጎዳ መምጣቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። እንደ ዓለም ባንክ ገለፃ ከሆነ እኤአ በ2015 ሩሲያ አምስት በመቶ የአገሪቷ በጀትን ለወታደራዊ አቅም ስትጠቀም፤ በቻይና በኩል ሁለት በመቶና በአሜሪካን ሦስት ነጥብ ሦስት በመቶ መበለጧን ያሳያል።

አወዛጋቢው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በያዝነው የፈረንጆች ዓመት የአገሪቷን ወጪ በተጨማሪ አስር በመቶ ለማሳደግ ማሰባቸው መነገሩን ተከትሎ የቻይናው መሪ የመከላከያቸውን በጀት በተጨማሪ ሰባት በመቶ ለመጨመር ማዘዛቸው ጉዳዩን የበለጠ እንዲጋጋል አድርጎታል።

የክሬሚያ ጉዳይን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ተደጋጋሚ ማዕቀብ የጣሉት የአውሮፓ አገራትና አሜሪካን የአገሪቱ የመከላከያ በጀት ላይ ጉዳት ለማድረስ ያለመ እንደሆነ ቢነገርም ሩሲያና ቻይና አህጉር ተሻጋሪ የባሊስቲክ ሚሳዔል ሙከራ በደቡብ ቻይና ባህር አቅራቢያ ማድረጋቸው የተፈለገውን ለማግኘት እንዳያስችል አድርጓል ተብሏል።

የአሜሪካው መከላከያ ሚኒስትር እንደገለፀው ቻይና ዘመናዊ የተባለውን የኒውኩሌር ሙከራ ስታደርግ የድምፅ ፍጥነቱ በአምስት ጊዜ የሚበልጥና የዓለምን የኒውኩሌር ጦርነትን ለማስጀመር ከግማሽ ሰዓት ያነሰ ጊዜ የሚፈጅ አቅም ያዘለ ነው ሲል፤ ከአስር ወራት በፊት የተሞከረው የሩሲያ ስትራቴጂክ ሚሳዔልም የተሳካ ነው ብሏል። አገራቱ የቆየ ተቀናቃኝነትን የሚያሳዩ እንደሆነ ቢታወቅም የወቅቱ የአገራት የበላይ መሆኗ የሚገለፀው አሜሪካ በኢኮኖሚና በወታደራዊ መስክ የሚደርስባትን ከፍተኛ ፉክክር ለመቋቋምና በአሸናፊነት ለመወጣት ከባድ የቤት ስራ ከፊቷ ተቀምጧል።

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close