Connect with us

Ethiopia

የኢህአዴግ ነገር!…አንዱ ብስል፣አንዱ ጥሬ!

Published

on

የኢህአዴግ ነገር!...አንዱ ብስል፣አንዱ ጥሬ!

የኢህአዴግ ነገር!…አንዱ ብስል፣አንዱ ጥሬ! | ጫሊ በላይነህ በድሬቲዩብ

36 አባላት ያሉት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮምቴ በኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ ሰሞኑን የሰጠው የድንበር ኮምሽኑን ውሳኔ ያለቅድመ ሁኔታ ለመቀበል ያሳለፈው ውሳኔ ከሁለት የተቆረጠ ዛፍ አድርጎታል። ውሳኔው የበርካታ ኢትዮጵያዊያንን ድጋፍ ያሳጣውና ተቃውሞም ጭምር የቀሰቀሰበት ሆኗል። ሻዕቢያ በይፋ ባይናገርም ደንገጡሮቹ ውሳኔውን ማጣጣላቸው ጥሩ ምልክት የሚሰጥ አልሆነም።

ይህን ውሳኔ ተከትሎ እንደ አረና ያሉ ፓርቲዎች መሬት አንቀጥቅጥ ሰልፍ እንጠራለን ሲሉ መዛታቸው፣ የኢሮብ ሕዝብ በይፋ መቃወሙ መልሶ ኢህአዴግ/ ህወሓትን አስደንግጧል።

ውሳኔው ለምን ተቃውሞ ገጠመው፣

የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ በርካታ ኢትዮጵያውያን የደም መሰዋዕትነት የጠየቀ እንደነበር አንዘነጋውም። ጦርነቱን ተከትሎ የብዙ ቤተሰቦች ቤት ተዘግቷል፣ ሕይወት ተናግቷል።

ከ500 በላይ ነጋዴዎች በጠራራ ጸሐይ ከአሰብ ወደብ ላይ ንብረቶቻቸውን በሻዕቢያ ተዘርፈዋል። እንደ ያኮና ኢንጅነሪንግ ያሉ አገር በቀል ተቋማት ለኪሳራ ተዳርገው ከገበያ ወጥተዋል። አንዳንዶቹም በባንክ ዕዳ ተሸጠዋል።

እነዚህ ወገኖች ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት ችግር ውስጥ መግባታቸውን በመግለጽ ቢያንስ ለባንኮች መንግሥት ዋስትና እንዲሰጥላቸው በንግድ ምክርቤት እገዛ ጭምር ያደረጉት ጥረት ሰሚ ማግኘት ባለመቻሉ በአገር የመጣን ችግር ብቻቸውን እንዲሸከሙ ተፈርዶባቸዋል።

ከኤርትራ ምድር በርካታ ወገኖች ንብረታቸውን በግፍ ተነጥቀው ሲባረሩና ለጎዳና ሲዳረጉ ድምጹን ያላሰማ ግንባር ዛሬ የሕዝብ ጥቅም አሳቢ መስሎ ብቅ ማለቱ የብዙዎችን ቁጣ ቢቀሰቅስ ምን ይገርማል?!

ዛሬ ይህ ሁሉ ጉዳት ተረሳና ኢህአዴግ በራሱ ስህተት የገባውን የአልጀርስ አሳሪ ስምምነት ለማስፈጸም ወሰነ። ይህ ውሳኔ ቢያንስ ፓርላማው እንኳን ለወጉ ያህል እንዲሳተፍበት ሳይደረግ 36 ሰዎች በር ዘግተው መወሰናቸው ቁጣ ቢቀሰቅስ የማይገርመው ለዚህ ነው።

እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ሉዐላዊነት እና ጥቅም ላይ ማን ወሳኝ አደረጋቸው? ትላንት ይግባኝ የሌለውን የአልጀርስ ስምምነት ለመፈረም፣ በቅኝ ግዛት ውሎች ለመዳኘት ሲወስኑ የሰሩትን ታሪካዊ ስህተት አሁን ላይ መሬት ቆርሶ በመስጠት ለመዝጋት ማቀዳቸው ስህተትን በስህተት ከማረም በስተቀር ምን ሊባል ይችላል?

ለመሆኑ ‘አገርህ ዳርድንበርዋ ተደፈረ፣ ተነሳ’ ብለው የማገዱት በአስር ሺዎች የሚቆጠር ሰማዕት ዜጎች አጀንዳ በምን ሊዘጉት ይሆን?

ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል እንዲሉ ኢህአዲግ/ ህወሓት በገዛ ውሳኔው ያልገመተው ተቃውሞን ተቀጣጥሎበታል። ይህ ክስተትም አስደንግጦታል።

እናም ባልተለመደ መልኩ በግንባሩ የተላለፈው ውሳኔ ወደሀላ ተመልሶ በግንባሩ አንድ አባል ፓርቲ ህወሓት ምክክር ሊደረግበት የግድ ሆኗል። ህወሓት ‘ውሳኔው የሕዝብና የአገር ጥቅምን ያስከብራል’ ብላ ምስክርነት በሰጠች ማግስት በሕዝብ ግፊት ምላስዋን ለመሳብ አቆብቁባለች።

ቢዘገይም ከሕዝብ መራቅና ሕዝብንም አለማክበር ከበድ ያለ ዋጋ እንደሚያስከፍል ኢህአዴግ የገባው ይመስላል። ይህ ከሆነ የኢህአዴግ የሰሞኑ ውሳኔ ሻዕቢያ ቢቀበለውም እንኳን የመተግበር ዕድሉ እጅግ የጠበበ ይመስላል። ከሕዝብ ይሁንታ ውጪ ይተግበር ቢባል እንኳን ኢህአዴግ ሸምቀቆውን በአንገቱ ላይ ከማጥበቅ የዘለለ አዎንታዊ ውጤት ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም።

DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close