Connect with us

Art and Culture

ወንደላጤዎችን ከትዳር አደጋ የሚታደገው የአባወራው ኑዛዜ….

Published

on

ወንደላጤዎችን ከትዳር አደጋ የሚታደገው የአባወራው ኑዛዜ….

ወንደላጤዎችን ከትዳር አደጋ የሚታደገው የአባወራው ኑዛዜ…. | አሳዬ ደርቤ በድሬቲዩብ

ንግስቷ ጽፋ የሰጠችኝ ወርሃዊ አስቤዛዎች፡-

ሩዝ… መኮረኒ… ፓስታ… ዘይት…. ኦሞ… ናዝሬት ሳሙና…. ክክ (ለሰላሱት የሚሆን)…. አተር ክክ… ማንከሽከሻ… ዘቃቅቤ??… ፋፋ… ሴሪፋም… አጃ… አምባረ-ጭቃ… ማጥለያ… እንቁላል… የጎድን ስጋ (ከሸማቾች)… ብረት ድስት (መካከለኛ ሳይዝ የሆነና ጆሮ ያለው)…. ዳይፐር… ዊግ… መጣጢሳ… በረኪና (ልትጠጣው ይሆን ልታጠጣኝ?)… ወተት (ሊፕቶሞል)… የእቃ ማጠቢያ ሽቦ… ጨው…… አብሽ…… (ዝርዝሩን አንብቤ ሳልጨርስ በፊት ‹‹አቤቱ የሚደረግብንን አስብ!›› በማለት እንባዬን ወደ ምድር ደፋሁት፡፡

ውድ ወንድሜ ትዳር መስርተኻል? መልስህ ‹‹አይ ወንደላጤ ነኝ›› የሚል ከሆነ በዓለም ላይ ካሉ የታደሉ ወንዶች መሃከል አንዱ ነህና ደስ ይበልህ! አንተ በግራ-አጥንት ጥቃት ግራ ከሚጋቡት መሃከል አይደለህምና አምላክህን አመስግነው!

እንደው ግን ለምናልባቱ…. ሚስት ባለማግባትህ የጎዶሎነት ስሜት ይሰማህ ይሆን? እንግዲያውስ መፍትሄውን ልንገርህ፡፡ የበለጠ እንዳትጎድል ሚስት አታግባ! ይልቅስ በለጬህን በመጉረስና ድራፍትህን በመቸለስ ቀዳዳውን ለመድፈን ሞክር፡፡

ጉድለቱ በዚህ የማይሰተካከል ከሆነ ግን አንዲት ኮረዳ ፈልግና ያዝ! በፍቅር እንዳትያዝ ግን ተጠንቀቅ! ምናልባትም ከቁጥጥርህ ውጭ በሆነ መልኩ የማፍቅር ስሜት ከተሰማህ ቀጣዩ ምዕራፍ ሰርግና ምላሽ ስለሆነ ያለምንም ማንገራገር ሱሪህን ታጥቀህ የስራ-ቦታህን ቀይር፡፡

‹‹ፍቅር›› የሚባል ወደ ትዳር የመግቢያ ‹‹ቃብድ›› ከዳሰሰብህ ቦታ………….. እንደ ወልድያ ስፖርት ክለብ በ500 ኪሎ ሜትር ራቅ፡፡

ውድ ወንድሜ ‹‹ሴቶች ወደ ወንድ ልብ የመግቢያ አቋራጭ መንገዱ በሆዱ በኩል መግባት ነው›› በማለት ያስባሉ፡፡ እናም ወደ ቤታቸው በወሰዱህ እለት ‹‹ቋንጣ እናፈርፍርልህ፣ ጨጨብሳ እናጨብስልህ፣ ጥብስ እንጥበስልህ›› ወዘተረፈ በማለት ያግባቡሃል፡፡

እኔ ግን እልሃለሁ…. ‹‹ጾም ነው አልበላም›› በላቸው፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት ከውበታቸው በተጨማሪ በሙያቸው አንተን ለማሰር የሚተበተብ ሴራ ነውና…. ተዓምር ቢሆን በእጃቸው የተሰራ ምግብ እንዳትቀምስ!

አልጋ ላይም ጥንቃቄ አድርግ! ‹ውሃ! ውሃ!› የሚያስብል ረመጥ ጭናቸውን፣ ጠመዥ፣ ጠመዥ የሚሸት ትንፋሻቸውን አታስውለው፡፡ ሁሌም ከገላቸው መሃከል ስትዋኝ ጥፍጥናን የሚለግስህ የራስህ ሆርሞን መሆኑን አስታውስ!

በልጅ ፍቅር ጠፍንገው በቁጥጥር ስር እንዳያውሉህም ምክሬንና ‹‹አሳዬ ደርቤ›› የሚለውን ስሜን በማስታወስ ኮንዶምህን ደርብ፡፡ ምክንያቱም ኮንዶም ከእርግዝናና ከአባላዘር በተጨማሪ ከትዳር የሚጠብቅህ በመሆኑ የዘወትር ትራስህ ይሁን፡፡

ውድ ወንድሜ፡- ‹‹ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ሴት አለች›› የሚለው አባባል የእመው እንጂ የአበው ስላልሆነ በልብህ ውስጥ አታሳድረው፡፡ ይልቅ ‹‹ከአንድ ስኬታማ ወንድ ጀርባ በምኞት የሚቁለጨለጩ በርካታ ሴቶች አሉ›› የሚለውን የጂም ኬሪን አባባል ሸምድደው፡፡

ከእዚህ ጋር በተገናኘም ዕጸ-በለስ አብልተው ወደ ምድር ያመጡንና አሳራችንን አብልተው ከምድረ-ገጽ የሚያጠፉን ‹‹ሴቶች›› ከጥፍር ሙረዳና ከጸጉር ጉንጎና በተረፋቸው ጊዜ… ኪችን ውስጥ የሚያወሯትን ብቸኛ ፍልስፍናቸውን ልንገርህ!

‹‹ስኬታማ ወንድ ማለት ሚስቱ ከምታጠፋው በላይ ገንዘብ የሚያገኝ ሰው ሲሆን…… ስኬታማ ሴት ማለት ደግሞ እንዲህ ያለውን ወንድ ያገባች ናት›› በማለት ዘወትር ያነበንባሉ፡፡ ይሄ መሰሪ ፍልስፍናቸው እንግዲህ የሴት ህልም እውን መሆኛ መንገዱ መንታ መሆኑን የሚናገር ነው፡፡ ህልማቸውን በራሳቸው ማሳካት ካልቻሉ ኮተታም ቅብዥራቸውን እውን የሚያደርግ ምስኪን ባል በማፈላለግ መረባቸውን ይጥሉበታል፡፡

እናም ወንድሜ ስኬት ባለበት ቦታ ሁሉ የሚያንዣብቡ ሴቶች ባይታጡም ሴት ባለበት ቦታ ግን ስኬት የሚባል ነገር የለም ስልህ እመነኝ፡፡ እነሱ የስኬት ተቋዳሽ እንጂ ጠንሳሽ ሆነው አያውቁም፡፡

እውነት እውነት እልሃለሁ ‹‹ትዳር ሳልመሰርት በፊት ጸጉሬ የሚጠቀለል፣ ወዜ የሚንፎለፎል፣ ሳቄን በጥርሴ፣ ገንዘቤን በኪሴ የማጭቅ ነጻ ወንደላጤ ነበርኩኝ፡፡ በፍላጎቴ ካልሆነ በቀር በአስቤዛ ሕይወቴን የምምራም አልነበርኩም፡፡

እናም በአንዱ ሰላቢ ምሽት ከደሞዜ በተጨማሪ ጸጉሬን የመምለጥና ወዜን የመምጠጥ ተልዕኮ የተሰጣት አንዲት ሴት ወደ ቤቴ ገባች፡፡ በማግስቱም ‹‹ያለኝን ነገር በሙላ ላካፍላት ቃል እገባለሁ›› የሚል ሰነድ ላይ አስፈርማ አገባችኝ፡፡

ከእዚያን ቀን አንስቶም እኔ ገንዘብ የማመጣ፤ እሷ አስቤዛ የምትጽፍ ሆነች፡፡ ‹‹ውጣ›› መባል እንጂ ‹‹ውጭልኝ›› ማለት የማልችል ሆንኩ፡፡ በመስሪያ ቤቴ ካሸርና በሚስቴ መሃከል የገንዘብ ልውውጥ የማካሂድ ATM ሆንኩ፡፡ በሚገርም ምትሐት እኔን ማሽን አድርጋ እሷ ማንዋል ሆነች፡፡

ብዙ ጊዜ ከቤት ስወጣ በነገር ሸንቁጣ ትሸኘኝና መስሪያ-ቤት ውዬ ስመለስ ከንፈሬን ስማ ትቀበለኛለች፡፡ ሆኖም ግን የምትስመኝ ናፍቆቷን ለመወጣት ሳይሆን ድራፍት አለመጠጣቴን ለማረጋገጥ ነው፡፡ (ሰቅ….ሰቅ…ሰቅ…ሰቅ….ሶፍት ስጡኝ እስኪ) እንባዬን አብሼ ወደ ምክሬ ስመለስ ከሚስት ይልቅ በአጋንንት መያዝን እንዲትመርጥ አሳስብሃለሁ! ምክንያቱም መምህር ግርማ ነጻ ያወጡሃልና!

ወደ ትዳር ከመግባት ደግሞ ወደ ቃሊቲ እስር- ቤት መግባት እንደሚቀል እነግርሃለሁ! (መለስ ዜናዊ ቢያስርህ ዶክተር አቢይ ይለቅሃልና!)

እንደ ዶክተር አቢይ በሚስት የተያዝክ ቀን ግን አለቀልህ! በቆምክበት መድረክ ሁሉ ባንተ አፍ የሚነበበው የሚስትህ ጽሑፍ ይሆናል፡፡ የአየር-ንብረት ለውጥ መድረክ ላይ ‹‹ስለ ሴቶች ታላቅነትና ስለሚስት ወሳኝነት›› ተናገር ካለችህ የተባልከውን ከመናገር ውጭ ‹‹አጀንዳው አይፈቅድልኝም›› የማለት መብት የለህም፡፡

ይሄም ሆኖ ግን ሌሎች እስረኞችን መፍታት እንጂ ሚስትህን መፍታትና ራስህን ነጻ ማውጣት አትችልም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም እስረኛ ምህረትን የመሻት መብቱ የተጠበቀ ቢሆንም እራሱን የመፍታት ስልጣን ግን የለውም፡፡

ስለዚህም ሁሉም ወንደላጤ ‹‹እሷ ያሰረችውን የምትፈታው እራሷ ብቻ መሆኗን አውቆ ላለመታሰር ጥንቃቄ ቢያደርግ ጥሩ ነው›› እያልኩ ዘላለማዊ ክብርና ሞገስን በትዳር ውስጥ ለተሰው ሰማዕታት ተመኝቼ ወደ ሸመታዬ ልሂድ፡፡

ከዚያ በፊት ግን… ኮሜንት መስጫው ላይ ‹‹ምን ዓይነት በረኪና መግዛት እንዳለብኝና እንዴት መጠቀም እንዳለብኝ›› ብትነግሩኝ ደስ ይለኛል፡፡ (ማለቴ…. ጨጓራዬ በጣም ሳይጎዳ እርሷ የተቀመጠችበትን ልቤን ብቻ ብጥስጥስ አድርጌ ለማሸለብ ስንት ሚሊ-ሊትር ብጠጣ ይበቃኝ ይሆን?))

DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close