Connect with us

Ethiopia

ጠ/ሚ/ዶ/ር አብይ የመንግስት ተቋማት ሊኖራቸው ስለሚገባው ራእይ፣እሴት እና ተልዕኮ የተናገሩት

Helen

Published

on

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ

ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን እየታየ ያለውን አገራዊ መነቃቃት ለመጠቀምና ወደፊት ለማራመድ የህብረተሰቡን ጥያቄ በአዲስ አሰራር መመለስ እንደሚያስፈልግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከከፍተኛ የስራ ኃላፊ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎችና ዋና ዳይሬክተሮች ጋር ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል።
በዚህ ወቅት ለውይይት መነሻ እንዲሆን ባቀረቡት ጽሁፍ የህዝበ አገልጋይ የሆነ አመራር ምን አይነት ሰብዕና ሊላበስ እንደሚገባ ማብራሪያ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራሩ ኢትዮጵያ አድጋለች ከማለት ባሻገር በተጨባጭ ህዝቡ ምን ያህል ተጠቅሟል የሚለውን መፈተሽና ማረጋገጥ አንዳለበት ነው የጠቆሙት። አሁን ላይ በአገሪቷ ተስፋ ሰጪ የሆነ የህብረተሰብ መነቃቃት ቢኖርም በፍጥነት መልስ ሊያገኙ የሚገባቸው በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልፀዋል።

የመንግስት አመራር አሰራሩን ግልጽና ለህዝብ የማይደበቅ ማድረግ እንደሚጠበቅበት በውይይት ወቅት አንስተዋል። ችግሮቸንም ለመፍታት በዚህ ወቅት ሀገሪቱ እየተጠቀመችባቸው ያሉት አሰራሮች እንደማያዋጡ እና አሰራሩ ሀገር መለወጥ የማያስችል መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። ችግሮቹን ለመፍታት በተሻለ ዘዴና ቅልጥፍና ስራዎችን ማከናወን መፍትሄ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።  ስራን ከማቀድ ጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ በምን ያህል ጊዜና ወጪ መስራት እንደሚገባ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አያይዘውም፥ በውጭ አገራት ባንኮች አካውንት ያላቸው የመንግስት ባለስልጣናት በአካውንቶቻቸው ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑንና ለዚህም ሀገራት ትብብር እያደረጉ እንደሆነም ገልፀዋል።

የፌዴራል መንግስት የካቢኔ አባላት የሥራ ኃላፊነት የቆይታ ጊዜ የሚወሰነው ኃላፊዎቹ በሚኖራቸው የሥራ አፈፃፀም ምዘና መሰረት ብቻ አንደሚሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታውቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ገለፃቸው እያንዳንዱን የሚኒስቴር መስሪያ ቤት የሚመሩ የሥራ ኃላፊዎች ከመጪው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ጋር የሥራ ውል ስምምነት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። በዚህም ሚኒስትሮቹ ተቆጥሮ የተሰጣቸውን ሥራ ቆጥረው በማስረከብ አፈፃፀማቸው እየተለካ ባላቸው ውጤት መሰረት ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ገልፀዋል። በዓመቱ መጨረሻ በቋሚ ኮሚቴ የሚገመገሙ ሚኒስትሮች በቀጥታ ለህዝብ ክፍት በሆነ ጥያቄ ይገመገማሉ፤ በግምገማው መሰረት ኃላፊነታቸውን በውጤታማነት ያልፈፀሙ ሥልጣን ላይ እንደማይቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

አሰራሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጠይቅ ብቻ ሳይሆን ለህዝብ የገባውን ቃል የሚፈጽም ተቋም መሆኑ የሚታይበት ይሆናል ብለዋል። የገባውን ቃል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ያልፈፀመ ኃላፊ ደግሞ በማግስቱ የማስተካከያ እርምጃ የሚወሰድበት እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ዶክተር አብይ አክለውም የካቢኔ አባላቱ በሚመሯቸው መስሪያ ቤቶች ከሰራተኞቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት ቀለል ያለ እና ውጤታማነትን ማዕከል ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም በየሳምንቱ እለተ ዓርብ ይካሄድ የነበረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወይም ካቢኔ ስብሰባ ወደ ቅዳሜ እንዲዛወር መወሰኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ አስታውቀዋል።

መነቃቃቱንና ተስፋው ለማስቀጠል

አገሪቱን አጠቃላይ የስራ ሁኔታ ለመቀየር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ለላቀ ውጤታማነት መነሳሳት እንደሚገባቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አሳስበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚህ ዙሪያ ባደረጉት ገለፃ፥ ራዕይ ማስቀመጥ፣ ወጥ የሆነ የአሰራር እሴት መገንባትና የጊዜና ሃብት አጠቃቀም ለስኬታማነትና ተሽሎ ለመገኘት ወሳኝ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ያለውን መነቃቃትና ተስፋ ለማስቀጠል በርካታ ስራዎች ይጠብቁናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለመደውን አሰራር መከተል ዋስትና አይሆንም ብለዋል። ችግሮቹን ለመፍታት በተሻለ ዘዴና ቅልጥፍና ስራዎችን ማከናወን መፍትሄ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close