Connect with us

Business

የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከአልበሽር በኋላ?

Published

on

የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከአልበሽር በኋላ? | በኃይሉ ሚዴቅሳ በድሬቲዩብ

ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ ሁለተኛው የውጭ ጉዟቸው ሱዳን ነበረች፡፡በሱዳን በነበራቸው ቆይታም ኢትዮጵያዊያን እስረኞች እንዲፈቱ፣ነጻ የድንበር ላይ ንግድ እንዲጀመር፣የጋራ ወደብ ልማት ሥራ እንዲከወን ወዘተ ተስማምተዋል፡፡ይህ የዚህ ሰሞን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ሆኖ የሰነበተ ጉዳይ ነው፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት ግንኙነት ታሪክ በጎ ነገር የለውም፡፡በድንበር ግጭት፣በቅጥር ጦርነት (proxy war)፣በእስላማዊ አክራሪነት (በ1987 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ከሱዳን በመጡ የሽብር ኃይሎች የግብጹ ፕሬዚዳንት ሊገደሉ እንደነበር ያስታውሷል)፣ወዘተ የታጀበ ነበር፡፡

የሁለቱ ወዳጅነት ፈር እየያዘ የመጣው ባለፉት 20 ዓመታት ነው፡፡በተለይ እስላማዊ ፖለቲካ የሚያቀነቅኑ ሰዎች ከአልበሽር አስተዳደር ውስጥ ከተወገዱ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሠረቱ የጋራ ጥቅም ሆኗል፡፡

ከ300 በላይ ሱዳናዊ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ፤ሱዳን ከ100 ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ታገኛለች፤ከአዲስ አበባ ካርቱም የአውቶቡስ ትራንስፖርት አለ፤አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን በሱዳን ይኖራሉ፤…የሚሉት አሀዞች የተፈጠሩት ባለፉት ሁለት አስርታት ነው፡፡

ይህንን ግንኙነት በዚህ መልክ በጎ ገጽታ እንዲኖረው ለማድረግ ቀላል የማይባል የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚያስፈልግ እሙን ነው፡፡ይሁን እንጂ ግንኙነቱ ተቋማዊ ቅርጽ ስለመያዙ ጥርጥር አለ፡፡የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት፣መንግሥታት ላይና ግልሰብ ላይ ያተኮረ ላለመሆኑ ማስረጃ የለም፡፡በቀጥተኛ አገላለጽ የሱዳንና የኢትዮጵያ ግንኙነት ከአልበሽር መንግሥትና ከኢሕአዴግ አስተዳደር በኋላ ይቀጥላል ወይ የሚል ግዙፍ ጥያቄ አለ፡፡በኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት ላይ የተለመዱ ፊቶችና ሰዎች አሉ፡፡እነዚህ ሰዎች ባይኖሩ ግንኙነቱ መቀጠሉን ለማረጋገጥ ይህ ዘመን ወሳኝነት አለው፡፡

የጠቅላይሚኒስትር ዓብይ የሥልጣን ዘመናትም ይህንን ጉዳይ በማረቅ በኩል ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ሲታረቅም ግን ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ይኸውም በሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ላይ ግዙፍ ሚና ያላቸው የደኅንነትና የፖለቲካ ሰዎች ድንገት ከመድረኩ ላይ መሠናበት የለባቸውም፡፡በቅድሚያ ተቋማዊ ቅርጽ ይኖረው ዘንድ መመካከርና ሰዎቹም ለተተኪዎች ጉዳዮቹን ማዋየትና ማስረከብ ይገባቸዋል፡፡ያ ካልሆነ ሁለት ኪሳራ ሊገጥም ይችላል፡፡

አንደኛው ፕሬዚዳንት አልበሽር የሚያምኗቸውንና ለዓመታት አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩትን የኢትዮጵያን ሰዎች ከግንኙነቱ መድረክ ላይ ሲያጡ በአዲሱ አመራር ላይ እምነት ሊያጡ ይችላሉ፡፡ሁለተኛው የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅሞችንና መንገዶቹን የሚያውቁት ጥቂት ሰዎች ከሆኑ የግንኙነቱ ጤናማነት ጥርጣሬ ውስጥ ሊወድቅ ይችላል፡፡ስለዚህ ይህ ግንኙነት ስትራቴጂካዊነቱን ጠብቆ እንዲጓዝ ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራርን ይጠይቃል፡፡ይህ በቀጥታ ለጅቡቲም ይሰራል፡፡

ከጊሌህ አስተዳደር በኋላ ከጅቡቲ ጋር ያለው የኢትዮጵያ ግንኙነት ይቀጥል ዘንድ ተቋማዊ ቅርጽ ሊይዝ ይገባዋል፡፡70 በመቶ ገቢዋን ከኢትዮጵያ ብቻ የምታገኘው ጅቡቲ የሚባለው ኢኮኖሚያዊ ውህደት ይመጣ ዘንድ ግንኙነቱ ከግለሰቦች ትከሻ ላይ ወርዶ ተቋማዊ ደንብ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡

የኢትዮ-ሱዳን ጉዳይን የሚወስነው ሌላ ጉዳይ የሕዳሴ ግድብ ነው፡፡የግድቡን ግንባታ ሱዳን መደገፏን በይፋ ገልጻለች፡፡ይህንን ማድረጓ ግብጾችን ያስከፋና የማያስደስት ቢሆንም ቅሉ መሠረቱ ግን ይለያል፡፡የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ፣ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ፣ለሱዳን ግብርና፣ለግብጽ ፖለቲካ ነው፡፡የግድቡ መገንባት ብዙ ቶን እህል ከውጭ ለምታስገባው ሱዳን የእርሻ አቅሟን ያዳብረዋል፡፡ይህ ለግብጽ ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡ሱዳን ለኢትዮጵያ ግድብ የሰጠችውን ድጋፍ የሚናደዱበት አንዱ ምክንያትም በዚህ ሰበብ ነው፡፡ስለዚህ ይህንን በዘላቂነት ለማሳወቅና ለማስረዳት ግዙፍ የድፕሎማሲ ሥራ ይጠይቃል፡፡

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከአምስቱም ጎረቤቶቿ ጋር የድንበር ማካለል አላደረገችም፡፡ይህ ሳይደረግ ከቆየባቸው ድንበሮች አንዱ የኢትዮጵያና ሱዳን ግንኙነት ነው፡፡ ጉዳዩ በሁለቱም ሀገራት የፖለቲካ ኃይሎች ተነስቶ እየተጣለ ዛሬም ቀጥሏል፡፡ብዙ ገበሬዎች የሁለቱን ሀገራት ድንበር እየተሻገሩ ያርሳሉ፡፡ይህ የግጭትና የአለመግባባት ሰበብ ሆኗል፡፡

አንዳንድ ይፋ ያልሆኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፕሬዚዳንት አልበሽር ይህ የድንበር ጉዳይ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ፍላጎት አላቸው፡፡ይህንንም ለጠቅላይሚኒስትር ዓብይ በግልጽ ቋንቋ አንስተውላቸዋል፡፡የጠቅላይሚኒስትሩ መንግሥት ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ መግባባትና ፖለቲካዊ መረጋጋት አለው ወይ የሚለው እንዳለ ሆኖ የድንበሩ ጉዳይ ግን የሁለቱንም ሀገራት ሰለምና ትብብር በማያናጋ፣ሕዝባዊ ቅሬታን በማያስነሳ መልኩ ይጠናቀቅ ዘንድ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

ሱዳንና ኢጋድ

ከላይ የተጠቀሰው የአቶ መለስ ዜናዊ ሰነድ እንደሚያብራራው፣በቀጣናው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻለው እንደ ኢጋድ ባሉ የጋራ መድረኮችም ጭምር ነው፡፡ይህ መድረክ ሱዳንንም ያካተተ ነው፡፡ይሁን እንጂ ሱዳን በሼርዓ የሚተዳደር አገር ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የአረብ ሊግ አባል ነው፡፡ግብጽ በአውራነት በምትጠራበት የአረብ ሊግ ውስጥ ለብዙ ዓመታት አባል የሆነችው ሱዳን፣ለኢጋድ ያላት ስሜት ቀዝቃዛ ነው፡፡ለአብነት ሁሉም የኢጋድ አባላት ጦር ባዘመቱበት የአልሸባብ ዉጊያ ላይ ሱዳን ጦር አልላከችም፡፡

Katharina Newbery የተባለ የአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት ጉዳዮች አጥኚ ‹‹Mapping national security interests in the horn of Africa›› በሚለው ሥራው እንደሚለው ሱዳን ኢጋድን የአሜሪካ መሣሪያ አድርጋ ታየው ነበር፡፡

ሆኖም አልበሽር በዓለም አቀፉ ፍርድቤት የቀረበባቸውን ክስ በመቃወም፣ በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል የተፈረመውን ሥምምነት በማግባባት፣አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለችው ማዕቀብ እንዲነሳ በመሥራት ኢጋድ ሚና ከተጫወተ በኋላ ካርቱም ለድርጅቱ አዎንታዊ አስተያየት አዳብራለች፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ኢጋድን ከአረብ ሊግ አታስበልጠውም፡፡ከኢጋድ ይልቅ በአረብ ሊግ ውስጥ መታቀፍ እንደሚጠቅማት ታስባለች፡፡ለዚህም ምክንያቶች አሏት፡፡የኢትዮ-ኤርትራን ችግር መፍታት አልቻለም፤የሶማሊያን ግጭት አላስቆመም፤የደቡብ ሱዳንን ብጥብጥ አልዳኘም ወዘተ የሚሉ መከራከሪያዎቿ ኢጋድ ላይ እምነት እንዳትጥል አድርጓታል፡፡

ከመግቢያ ላይ የተጠቀሰው የአቶ መለስ ዜናዊ ትንተና እንደሚለው የኢጋድ አባል ሀገራት የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ የአመራር ቦታዎችን ለነሱ መስጠት እንደሚገባ ይገለጻል፡፡‹‹የጋራ ድርጅታችንን ኢጋድን የማጠናከር ሥራ ከምንም በላይ ቀድመን በመገኘት መሥራት ሲኖርብን በተቋሙ ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ በተመለከተ ቅድሚያ ለጎረቤቶቻችን በመስጠት የባለቤትነት መንፈስ እንዲያድርባቸው ማድረግ አለብን›› ይላል ሰነዱ፡፡

ይሁን እንጂ Katharina Newbery በጥናቱ ላይ እንደሚለው፣በኢጋድ እምነት የሚያጡ አባል ሀገራት የመብዛታቸው ምክንያት ተቋሙ በኢትዮጵያ ተጽዕኖ ሥር ወድቋል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡በርግጥ የድርጅቱን በጀት በማዋጣት ረገድ ምንም ዕዳ የሌለባት ሀገር ኢትዮጵያ ነች፡፡በዚያው ልክ ደግሞ አብዛኞቹን የአመራር ቦታዎች የያዘችው እርሷ ናት፡፡አሁንም የውጭ ጉዳይሚኒስትሮች ሰብሳቢ፣አሁንም የኢጋድም ሊቀመንበር ኢትዮጵያ ነች፡፡እናም እንደ ሱዳን ያሉ ሀገራት ኢጋድን አምነው በድርጅቱ ውስጥ የሚኖራቸው ፖለቲካዊና አከባቢያዊ ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ከሱዳን ጋር በተያያዘ የጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ መንግሥት የቤት ሥራም አንዱ ይህ ነው፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close