Connect with us

Business

የጠቅላይሚኒስትሩ የእራት ግብዣዎች!

Published

on

የጠቅላይሚኒስትሩ የእራት ግብዣዎች!

የጠቅላይሚኒስትሩ የእራት ግብዣዎች! | በኃይሉ ሚዴቅሳ

ጠቅላይሚኒስትሩ ከበዓለ ሲመታቸው ጀምሮ እራት እየጋበዙ ነው፡፡ ለነገሩ የመጀመሪያው እራት ግብዣ በፕሬዚዳንቱ የተደረገ ነው፡፡ቀጥሎ ለተቃዋሚዎች ነው-ግብዣ የተከናወነው፡፡ሥልጣን በያዙ በዘጠነኛው ቀን የተጀመረው የጠቅላይሚኒስትሩ የእራት ግብዣ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከፖለቲከኞች የተጀመረው ግብዣ፣ባለፈው ቅዳሜ ማታም ተከናውኗል፡፡

ከፖለቲከኞቹ በኋላ ጠቅላይሚኒስትሩ እራት የጋበዙት የ ኦሮሚያ ክልል ታዋቂ ሰዎችን፣ አባገዳዎችን በአጠቃላይ ኦሮሞዎችን ነው፡፡ባሳለፍነው ቅዳሜ ደግሞ በተመሳሳይ ደረጃ ያሉ አማራዎችን ጠርተው እራት አብልተዋል፤ተወያይተዋልም፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ እራት የሚጋብዙአቸው ሰዎች ሲመጡ ስልክ፣ ድምጽ መቅጃ፣ ምስል መቅረጫ ወዘተ እንዲይዙ አይፈቀድላቸውም፡፡ከዚያም በግብዣው ላይ የሚናገሯቸው ነገሮች አነጋጋሪ ይሆናሉ፡፡ አነጋጋሪነታቸው ግን ማስረጃ የለውም፡፡ ግን ምንም ቢናገሩ የድምጽም የምስልም ማስረጃ ስለማይኖር፣ አለያም ግብዣው ላይ የሚሳተፉት ምስጢር ጠባቂ የሆኑ ‹የቤት ልጆች› ስለሆኑ ያን ያህል አጀንዳ ሲሆን አይታይም፡፡

በኦሮሞዎቹ የእራት ግብዣ ላይ የተናገሩትን አነጋጋሪ ነገር ለጊዜው እንለፈውና በቅዳሜለቱ የአማራዎቹ ግብዣ ላይ የተናገሩትን እናጣቅስ፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅር ሊባሉ እንደሚገባ፣ ሚስታቸው በሌሎች እራት ግብዣዎች ላይ ለመገኘት ፈቃደኛ እንዳልነበረች፣ የአሜሪካው ሲኖዶስ ለቤተ-ክርስቲያን ጥንካሬ ሲባል ወደ አገር ቤት እንዲመለስ እየጣሩ ስለመሆናቸው…ወዘተ አወሩ፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ ይህንን ለመናገራቸው የሰው እንጂ የሰነድ ማስረጃ አይገኝም፡፡ ምክንያቱም ድምጽም ምስልም መቅረጽ እንዳይቻል አስቀድሞ ማዕቀብ ተጥሏል፡፡ አስገራሚው ነገር ሰውዬው እራትም መጋበዛቸው፣ስልክና መቅረጸ-ድምጽ እንዳይገባ መከልከላቸውም ወዘተ አይደለም፡፡

በየ መድረኩ ስለ ኢትዮጵያና አንድነት ሲናገሩና ሲያስተምሩ የሚውሉት ጠቅላይሚኒስተሩ፣ በኢትዮጵያዊ ንግግራቸው አገርን ማረጋጋት የቻሉት እርሳቸው፣ ማዕዳችንም ገበታችንም አንድ ናት፤ እርሷም ኢትዮጵያ ናት ሲሉ የከረሙት ዶ/ር ዓብይ፣ ለምን በብሔር እራት ማብላት ፈለጉ? በእውነቱ ትክክለኛው የጠቅላይሚኒስትሩ ሰብዕናስ የትኛው ነው? የሚሉት ጥያቄዎች መላሽ የሌላቸው አንገብጋቢ ሐሳቦች ናቸው፡፡

ጠቅላይሚኒስትሩ ባሳለፍነው ቅዳሜ በነበረው የእራት ሥነ-ሥርዓት ላይ የተናገሩት ነገር ግን እጅጉን አነጋጋሪ ነው፡፡ ለኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅርታ እናድርግላቸው የሚለውን ንግግራቸውን በዝርዝር ‹‹መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይቅር እንበላቸው›› ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ- በሚል ርዕስ ስለተብራራ እዚያ ላይ ይመልከቱ፡፡

በውጭ ሀገር የሚኖረው (የአሜሪካው) ሲኖዶስ ወደ ሀገር ቤት እንዲገባና እንዲሰራ እያግባቡ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ቅዳሜ እስከ 4፡30 በቆየው የእራት ግብዣ ለይ ተናግረዋል፡፡ለዚህም አቡነ ማትያስን እንዳነጋገሯቸው፤አለመግባባቱ ተፈትቶ አንድ ጠንካራ ቤተ-ክርስቲያን እዲኖር ምኞታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ጥያቄው አማራዎችን እራት ጋብዘው፣ ስለቀይሽብር፣ ስለደርግ ሰዎች፣ ስለሲኖዶሶቹ ጸብ ለምን ማውራት ፈለጉ? ይቺን ነገር ለምን ከተቃዋሚዎቻቸው አለያም ከኦሮሞዎቹ ጋር በነበራቸው ምሽት ለምን አልተናገሯትም? ወዘተ የሚለውን ጥያቄ ወደ ጎን ትተነው፣ ይህ ከሕግ አንጻር ይቻላል ወይ? ሕገመንግሥቱንስ አይጥስም ወይ? ከተባለ ግን ግጥም አድርጎ ይጥሳል የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡

በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 27 እና በሌሎችም ማብራሪያዎችና ሕጎች በተደነገገው መሠረት መንግሥት በኃይማኖት ጣልቃ አይገባም፣ኃይማኖትም እንዲሁ!

ይህ ድንጋጌ መንግሥት ሲል የመንግሥት ባለሥልጣናትንም እንጂ እራሱን መንግሥትን ብቻ አይደለም፡፡ እናም ጠቅላይሚኒስትሩ በምንም ምክንያት ይሁን በሃይማኖት እና በሃይማኖተኞች ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል፡፡ይህ ድርጊታቸው ከሕግም ሆነ ከተገቢነት አንጻር ያለው ሁኔታ በባለሙያዎች ዝርዝር ይቀርብበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close