Connect with us

Ethiopia

የኃይሌ ፊዳ ፍዳ!

Published

on

የኃይሌ ፊዳ ፍዳ!

የኃይሌ ፊዳ ፍዳ! | ማዕረግ ጌታቸው በድሬቲዩብ

ዳኛቸው ወርቁ ከሞልቬር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የኢትዮጵያን አብዮት አደፍረስ ልቦለድ ላይ ካለውም በላይ ምናባዊ ነበር ይላል፡፡እወነት ነው፡፡ የ1960ዎቹ ትውልድ ሀገር ወዳድነትና መስዋዕትነት በዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ፍፁም ምናባዊ ነበረ፡፡

በላባደርና ወዛደር፣ በእናሸንፋልና እናቸንፋለን ቃላት ሳይቀር መቆራቆዝ ከዛም ለቃል ታምኖ መሞት ልቦለድንም የሚያስንቅ የምናብ ዓለም ውስጥ መግባትን ይጠይቃል፡፡ ለዚያ ዘመን አብዮተኞች ኢትዮጵያ ያለችው ምናብ ውስጥ እንጅ ምድር ላይ አልነበረም፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ከሌላው የሚለየውም በዚህ ባህሪው የተነሳ ይመስለኛል፡፡

በሌላው ዓለም አብዮተኞቹ የተፋለሙት የቡርዣውን ስርዓት ሲሆን በእኛ ሀገር ግን ጦርነቱ የነበረው በራሳቸው በአብዮተኞቹ መካከል ነበር፡፡ ይህም የኛን ሀገር አብዮት ” ልቦለድ “አብዮተኞችንም “ገጸ-ባህሪያት ” አድርገን እንድንመለከት ያስገድደናል፡፡ እንዲህ ያለው ስሜት ደግሞ የየራሳችን ምርጥ ገፀ-ባህሪ ጋር ያስተዋውቀናል ፡፡ ፍቅር እስከ-መቃብር ውስጥ እንዳሉት በዛብህና ሰብለወንጌል፣አድፍረስ ውስጥ እንዳሉት ጺወኔና አደፍረስ ፣ከአድማስ ባሻገር ውስጥ እንዳሉት አበራና ሉሊት አብዮቱም የራሱ የማይረሱ ገፀ-ባህሪያት ነበሩት፡፡

ከእነዚህ ገጸ-ባህሪያት መካከል ዛሬም ነግም የማይደበዝዘው ቁጥር አንዱ ሰው ኃይሌ ፊዳ ነው፡፡ ዝምተኛው የአብዮቱ ማሃንዲስ በጠላቶቹም በወዳጆቹም ዕኩል የሚፈራ የሚከበር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ማርክሲስት አንደሚባለው ፊዲስት ተብሎ የተወራለት፤ ዐዕላፍ ተከታይ የነበረው ሰው መሆኑም ዕሙን ነው፡፡ ኃይሌ ጀርመን ከዩንቨርስቲ መምህርነቱ ለቆ ሀገር ነፃ ሊያወጣ ሲመጣ እንደሚሞት ዕርግጠኛ ነበር፡፡ ግን በጊዜው የአቅምን ሞክሮ ከመሞት የተሻለ ዕድል ከየት ይመጣል ብሎ ያሰበ ይመስላል፡፡

በዚህ ምክንያትም የነኩትን ሁሉ ቅርጥፍጥፍ አድረጎ የሚበላውን መንግስቱ ኃይለማሪያምን ለማዳ አድረጌ አንድ ትውልድ ዕታደጋለሁ በሎ ጓድ ሊቀመንበሩን ቀረባቸው፡፡ ነብሩን ለማጥመድ ዋሻ መግባት ግድ ነው ከዛ ግን ወይ ማጥመድ ወይ መበላት የህይወት ዕጣህ ነው በሚለው አባባል ተደፋፍሮም ቁጥውን ሰው ሊያሰግር ምኒሊክ ቤተ-መንግስት ወረደ፡፡

ኮለኔል መንግስቱን እንደፀባያቸው እያስታመመ ከጊዜ ጋር ወደፊት ነጎደ፡፡ በዚህ ጊዜ ውሥጥ ግን ኃይሌ እወነትም ኢትዮጵያዊ ማርክስ መሆኑን ማሳየት ጀመረ፡፡ ሰለአብዮታዊት ብቻ ሳይሆን ከአዕላፍ ዓመታት በኋላ ስለምትኖረው ኢትዮጵያ ትንቢቱን መናገር ቀጠለ፡፡

የኤርትራን ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልተቻለ ኤርትራ ተረት ትሆናለች እያለ ጮኸ፡፡ ደርግን ከሻአብያ ጋር ሊያደራድር ደፋ ቀና አለ፡፡ ተሳካለት፡፡

ግን ኮለኔል መንግሰቱ የጦርነት ወልፋቸው ተነስቶ በጦርነት መጀመሪያ እንሞክራቸው ብለው ድርድሩን አሻፈረኝ አሉ፡፡ ኃይሌም ኤርትራ ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ መሆኗ እንደቀረ ተረድቶ ይሰራበት ከነበረው የኤርትራ ኮሚሽን በገዛ ፍቃዱ ለቀቀ፡፡ ይህ ከሆነ ከ14 ዓመታት በኋላ ትንቢቱ ደረሰ፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል መኾኗ ቀርቶ ጎረቤት ተባለች፡፡

ኃይሌ ፊዳ ምናባዊ ነው ባልነው የኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ ፍረንጆች ገፀ-ክርስቶስ ( Christ figure ወይም ፍፁማዊ )የሚባል ዓይነት ገጸ-ባህሪ ነበረ፡፡ ለዚህ ሌላም መከራከሪያ ማምጣት ይቻልል፡፡ የዛያድ ባሬ መንግስተ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሊያካሄድ መሆኑን ቀድሞ የተነበየው ሰው ኃይሌ ፊዳ ነው፡፡ ነግር ግን ደረግ ሊሰማው አልፈለገም፡፡ እናም ከአመት በኋላ የሱማሊያ ጦር ሽምጥ ጋልቦ አዋሽ አርባ ደረሰ፡፡ ደርጎችም ግራ ሲጋቡ ኃይሌ አማራጩ ሚኒሻ ማስታጠቅ እንደሆነ ነገራቸው፡፡

የአብዮቱ ማሃንዲስ ሰሚ በማጣት ጦርነቱን ማስቀረት ባይችልም የሀገራችንን ሉዓላዊነት የማስከበሪያ መንገድ ግን አልነሳንም፡፡ ኃይሌ ዛሬ ኢህአዴግ የሚመፃደቅበትን የአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ውህደትን ቀድሞ እንደሚያስፈልግ የተናገረ ፤አብዮቱም ከማንም ድጋፍ ውጭ ኢትዮጵያዊ መልክ ሊኖረው ይገባል ብሎ የተሟገተ ሰው ነበረ፡፡

ጥራዝ ነጠቅ አብዮተኛ ሀገር ያጠፋል እያለ የለፈፈ፤ የኢህፓን አካሄድ በአደባባይ የኮነነ ፤ እንደዛሬ ዘመን ፖለቲከኞች ከውጭ ሁኖ ዕሳት ዕያቀጣጠለ የድሃ ልጅ ከመማገድ ይልቅ እራሱን ማግዶ ያሳየ ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ያልተለመደ መንገድን የቀየሰ ባለሟል ነው፡፡

የዛሬ ዘመን የአንድነታችንን ጠንቅ የአክራሪ ብሄርተኝነት ጉዳይ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የተነተ ኢትዮጵያዊነትና ብሄርተኝነት ተመጣጥነው ካልሄዱ መጥፊያችን መሆኑን የተነበየ ገፀ-ክርስቶሰ ገፀ-ባህሪ ነበረ፡፡

ይህን ሁሉ ያደረገው ሰው ግን በመጨረሻ በራሱ ትንቢት ተጠልፎ ወደቀ፡፡ ነብሩን ለማጥመድ ከገባበት ዋሻ ሳይመለስ ቀረ፡፡ ኃይሌ ፊዳ የሚባል ትልቅ ፖለቲከኛ ድንገት በርቶ ድንገት ጠፋ፡፡ 37 ዓመት ከኖረባት ምድር ለአንድ ለሀገሩ ሲል መሰናበትን ምርጫው አደረገ፡፡

ጓድ መንግስቱም በደም ዕጃቸው እንደጨቀየ ኃይሌ ፊዳን የሚህል ትልቅ ሰው ማጣታችን ያሳዝናል ብለው ጭራሽ ሀዘናችን አበረቱት፡ህግ አራዊት በሚግዛው ስርዓት ውስጥ ሰው የመሆን እዳው ሞት ብቻ ነው። አይ አንች ሀገር!

(የዚህ ፅሁፍ መነሻየ በቅርብ ለንባብ የበቃው በአማረ ተግባሩ(ዶ/ር) የተዘጋጀው “ኃይሌ ፊዳና የግሌ ትዝታ ” መፅሀፍ ነው )

DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close