Connect with us

Ethiopia

‹‹መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይቅር እንበላቸው›› ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ

Published

on

‹‹መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይቅር እንበላቸው›› ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ

‹‹መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይቅር እንበላቸው›› ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ | በኃይሉ ሚዴቅሳ በድሬቲዩብ

‹‹ቀይ ሽብር በይፋ የተጀመረው ጥር 24-1969 ዓ.ም ነው፤ ጥሪውን ያቀረበው ራሱ መንግሥቱ ነው፤ ሽብሩን ወደ አናርኪስቶች ካምፕ ውሰዱት አለ፤ከኛ አንድ ታጋይ ቢሞት ሺህ አናርኪስት እንገድላለን አለ፤ግደሉ ብሎ አዘዘ…ግደሉ አለ፡፡ ከግንቦት 1 እስከ 15 1969 ዓ.ም ድረስ ባንድ ሌሊት ብቻ ደርግ ራሱ 1ሺህ713 ሰዎች መገደላቸውን አሳውቋል፡፡…ትህሳስ 6-1969 ዓ.ም ባንድ ሌሊት ብቻበአዲስ አበባ 300 ያህል ሰዎች ተገድለው የተቆራረጠው ሬሳቸው መንገድ ላይ ተጣለ፡፡

‹‹በወቅቱ አዲስ አበባን ይጎበኙ የነበሩ ሁለት የአሜሪካ ም/ቤት አባሎች ቢያንስ 50 ሬሳ መንገድ ላይ ተጥሎ አይተዋል፡፡…ከታህሳስ 6 በፊት ከአዲስ አበባ 385፣ከትግራይ 56፣ከወሎ74፣ከጨቦና ጉራጌ32፣ከጎንደር 56 እስረኞች ተገድለዋል…በአዲስ አበባ በሜይዴይ ዋዜማ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ 1500 ሰዎች ተገድለዋል፡፡የሲዊድሽ የሕጻናት አድን ድርጅት ዋና ጸሐፊ በየቀኑ በግንቦት 1969 ከ100-150 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል፡፡…በአጠቃላይ ከ1967-1971 ድረስ ብቻ በቀይ ሽብር ከ250ሺህ ሕዝብ በላይ ተገድሏል፡፡›› እነዚህ አሀዞች የተገኙት፣ To Kill A Generation ከሚለው የBabile Tola መጽሐፍ ነው፡፡

ጥቅሱ ውስጥ የተካተቱት ቁጥሮች የሚያመለክቱት የአራት ዓመት አሀዝ ነው፡፡ከቀይ ሽብር ወዲህ ባለ ጊዜም ሆነ ከዚያ በፊት (በነጭ ሽብር፣በፒያኖ ገመድ ኦፕሬሽን፣በመንጥር ኦፕሬሽን ወዘተ) በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው በመንግሥቱ ኃይለማርያም ወልዴ ትዕዛዝ ነው፡፡ይህንን ሁሉም ገለልተኛ ተቋማትና ሀገራት የተስማሙበት ሀቅ ነው፡፡ሪካርዶ ኦዘሪዮ Talk To Devils በሚለው መጽሐፉ እንዳለው መንግሥቱ ኃይለማርያም ዓለማችን ካስተናገደቻቸው 10 አምባገነኖች አንዱ ናቸው፡፡

እኒህን ሰው ነው እንግዲህ ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ አሕመድ ‹‹ይቅር እንበላቸው›› ያሉት፡፡ይህንን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ታዋቂ ሰዎችን፣ምሁራንና መሰል ሰዎችን እራት በጋበዙበት ዕለት ባሳለፍነው ቅዳሜ ምሽት ነው፡፡በርግጥ ይቅርታ ጥሩ ነው፡፡የትኛውም ሀይማኖትም ይቅርታን ያዛል፡፡

የሰው ልጅ ግን ሕግ አብጅቶ፣በመንግሥታት ውስጥ የሚኖረው ይቅርታን የማያውቅ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የሕግ የበላይነት ጉዳይም ስለሚያሳስብ ነው፡፡በዘር ማጥፋት ወንጀል የተከሰሱት መንግሥቱ ኃይለማርያም አንድ ትውልድን በመግደል፣ታሪክም ሕግም ይቅር የማይለው ጥፋት ፈጽመው በመጨረሻም አገር ትተው በመፈርጠጥ፣ሕዝባቸውንም ስራህ ያውጣህ ብለው ቤተሰባቸውንና ራሳቸውን አድነዋል፡፡ ጓደኞቻቸው ከሁለት አስርታት በላይ ለእስር የተዳረጉት፣ በእስርቤትም የሞቱት ኮሎኔል መንግሥቱ የሰጧቸውን ትዕዛዝ በመፈጸማቸው ነው፡፡

ይቅርታና የሕግ የበላይነት አብረው አይሄዱም፡፡ ሕግ ጉልበተኛውን ከደካማው እኩል የሚያደርግ፣ በአብዛኛው ደግሞ ለደካማው የቆመ ሥርዓት ነው፡፡ እናም ሕግ የጣሰ ጉልበተኛ የሚዳኘው በሕግ እንጂ በይቅርታ አይደለም፡፡ ለ17 ዓመት በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት እየፈጠሩ፣ ጦርነት ሲያስተዳድሩ ለነበሩት ለያኔው ፕሬዚዳንት ይቅርታ ጥፋታቸውን አያካክስም፡፡ ደግሞም ለመንግሥቱ ኃይለማርያምን ይቅር ማለት የሚችለው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ጠቅላይሚኒስትሩ አይደሉም፡፡

በርግጥ ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ እንዳሉት ይቅርታ ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ግን መንግሥቱ ይቅርታ ተደረገላቸው ቢባሉ አምስት ልጆቻቸውን በአንድ ሌሊት ያጡ እናቶች ምን ይላሉ፤የልጆቻቸውን አስከሬን ከምኒልክ ሆስፒታል የገዙ ወላጆች ምን ይሰማቸዋል፤ስድስት ልጆቿን በአንድ ጉድጓድ አስቀብራ ያለ ጧሪ ቀባሪ የቀረችው እናት ምን ልትል ትችላለች…ይህ ሁሉ ነገር ነው መጤን ያለበት፡፡በርግጥ መንግሥቱ ቀይ ሽብር ብለው ሕዝብን ሲያፋጁ ዶ/ር ዓብይ አራስ ስለነበሩና እነ በሻሻና አጋሮም ለዚህ ሽብር ስላልተጋለጡ ጦሱን አያውቁትም፡፡እንጂማ ከአይኤስም ከአልሸባብም በፊት፣ከነቢላድንም፣ ከነ አልባግዳዲም ቀድመው ሽብር የጀመሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ናቸው፡፡

ጎበዝ! በቀይ ሽብር ልጆቻቸውና ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ስንት ሺህ ሰዎች እኮ እርማቸውን ያወጡት የዛሬ 7 እና 8 ዓመት ነው፡፡ሀዘናቸው እኮ ትኩስ ነው፡፡የማስታወስ ችሎታችን እጅጉን አናሳ ስለሆነ ነው እንጂ እኮ የቀይ ሽብር ሰማእታት መታሰቢያ ሙዚየም የተመረቀ ዕለት ስንት ሺህ ሕዝብ ወጥቶ በእንባ ከተራጨ 10 ዓመት አልሞላውም፡፡እንደ አዲስ እኮ ነው ወጥቶ የተላቀሰው፡፡ኮሎኔል መንግሥቱ እኮ ስድሳ የአገር ባለውለታዎችን ያስገደሉት ገና ሥልጣን ይዘው ሶስት ወር ሳይሞላቸው ነው፡፡እኒህን ሰው በይቅርታ ማለፍስ ምን ዓይነት ተገቢነት አለው የሕግን የበላይነትስ ማኮሰስ አይሆንምን?

ጠቅላይሚኒስትር ዓብይ ይህን ያህል ይቅር ባይ ከሆኑ ለምን የይቅርታ ቦርድን አይቀላቀሉም ብዬ ማፌዝ አልፈልግም፡፡ ግን ሰውዬው የዕውነት ‹ያልተነካ ግልግል ያውቃል› አለያም ‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት› እንደሚባለው ካልሆኑ በቀር ለመንግሥቱ ኃይለማርያም ይቅር ለማለት ከመባከን ይልቅ እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ይቅር የሚሏቸው ሰዎች እንዳሉላቸው መጠቆም እፈልጋለሁ፡፡

17 ዓመት ሙሉ አገርን ከወራሪ ሲጠብቁ፣ ለአገር ለወገን አጥንታቸውን ሰከሰክሱ የነበሩት እነ ጀኔራል አዲስ ተድላ እዚህ ጣሊያን ኤምባሲ ከቆሙት በታች ከሞቱትም በላይ ሆነው እየኖሩ መሆኑን መቼም ጠቅላይሚኒስትራችን ሰምተዋል፡፡እስኪ እነሱን ይፍቷቸው፡፡መቼም በድሎት በናጠጠ ሀብት ላይ ከሚኖሩት መንግሥቱ እዚህ ከስድስት ኪሎ ከፍ ብሎ በአገራቸው ላይ ጥገኛ የሆኑት ሰዎች ያሳዝናሉ፡፡ከዚምቧብዌም እዚህ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ይቀርባል!! DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close