Connect with us

Ethiopia

ከህገ-መንግስቱ የተኳረፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ!

Published

on

ከህገ-መንግስቱ የተኳረፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ!

ከህገ-መንግስቱ የተኳረፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ! | ይነገር ጌታቸው በድሬቲዩብ

ጭጋግ ባጠላበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ድንገት በርሃን የፈነጠቁት ሰው ምኒልክ ቤተ-መንግስት ከገቡ 14 ቀን ሆናቸው፡፡ በእነዚህ ቀናት ቃላቸው ከሰማይ እንደወረደ መና ብዙዎችን አጥግቧል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን አለምልሟል፡፡ ለአንድ ሀገር ህዝብ የአንድነት መሰሶ የሚሆነውን ተሰፋ ፈንጥቋል፡፡

ይህ አይነቱ የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ መንገድ ግን ጥያቄ የማይነሳበት ፍፁም ተደርጎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ከሀገሪቱ ህገ-መንግስት ጋር ተኮራርፈዋል፡፡ በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገና ስራ በውሉ ባልጀመሩበት ወቅት ስህተቶችን እየፈለጉ ማጉላቱ ተገቢ አይደለም፤ ለሀገርም አይበጅም፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ መሰረታዊ ችግሩ የህግ የበላይነት አለመከበር በመሆኑ በዚህ በኩል የሚፈጠረውን ስሀተት ማለፍ ተገቢ አይደለም፡፡ በመሆኑም የህግ የበላይነት አለመስፈን በፈጠረው ተቃውሞ ለስልጣን የበቁትን ጠቅላይ ሚንስተር በጣሷቸው ህጎች ልንጠይቃቸው ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የመጀመሪያ ንግግራቸውን ሲያደርጉ በመጀመሪያዎቹ ዓረፈተነገሮች ላይ ህገ-መንግስቱ የማያውቀውን ሀሳብ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ኃይለማሪያምን ለማመስገን ባለመው ንግግራቸው የዛሬዋ ቀን በሰላማዊ መንገድ የስልጣን ሽግግር የተደረገባት ታሪካዊ ቀን ናት ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይህ ሀሳብ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ምን አይነት የስልጣን ሽግግር ተደረገ? ማን ነው ለማን ስልጣን ያሸጋገረው?

በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 73/2 በግልፅ እንደሰፈረው መንግስታዊ ሰልጣን የሚመሰረተው በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ባለው ፓርቲ አማካይነት እንጅ በግለሰብ አይደለም ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ የአቶ ኃይለማሪያም በዶክተር ዐብይ መቀየር በአንድ ፓርቲ ውስጥ ያለ የአመራር መተካካት እንጅ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሌላ ፓርቲ ባለመሆኑ የስልጣን ሽግግርን አያመለክትም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ስለጣናቸውን አሃዱ ባሉበት ንግገራቸው ላይ ህገ-መንግስቱ ኢትዮጵያዊነትን ከሚያይበት መንገድ በተለየ አካሄድ ሲተረጉሙት ተስተውለዋል፡፡ ህገ-መንግስቱ ኢትዮጵያዊ አንድነትን የተረጎመው የወል የሆነ ማንነት የፈጠረውና በአንድ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ግንባታ ህልው የሚሆን አድርጎ ነው፡፡

ይህ የህገ-መንግስቱ አተያይ ሀገር ማለት ሰው ነው ከሚል እሳቤ የሚመነጭ ነው፡፡ እሳቤው ብዙ ክርክሮች እንዳሉበት ቢታወቅም ህገ-መንግስቱን ሳያሻሽሉ ግን ኢትዮጵያዊ አንድነትን በነገስታቱ ዘመን እንደነበረው አተያይ የግዛት አንድነት የወለደው ማስመሰሉ ስህተት ነው፡፡

በዚህ ምክንያትም ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ ኢትዮጵያዊነትን የተመለከቱበት ግዛት ተኮር ዕይታ በቁሙ ትክክል ቢመስልም በህገ-መንግስቱ ኢትዮጵያ ከተተረጎመበት እንፃር ግን ስሀተት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

የጠቅላይ ሚንስትሩን የ14 ቀናት የአመራርነት ጉዳይና የህግ-የበላይነት ሀሳብ ምልከታችንን ስንቀጥል ሌላው ስህተት ሁኖ የሚገኘው ሃሳብ በየሄዱበት ቦታ በየአከባቢው ቋንቋ ማውራታቸው ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 5/2 ላይ እንደሰፈረው የፌደራል መንግስቱ የስራ ቋንቋ አማረኛ ነው፡፡ ከዚህ መነሻም የጠቅላይ ሚንስተሩ በተለያዩ አከባቢዎች ተገኝተው በተለያዩ ቋንቋዎች ማውራት ከህገ-መንግስቱ ጋር የሚጣረስ ነው፡፡

በርግጥ አንዳንድ ወገኖች የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በትግረኛ ንግግር ያደርጉ ነበር ምኑ ነው አዲሱ ነገር የሚል ክርክር ሲያነሱ ይደመጣል፡፡ ነገር ግን ፖለቲካችን ዕደገት እንዲያመጣ ከተመኘን ከትናንት ስሀተት መማር እንጅ ያለፈን ዕክል ዕርስት ማደረግ ተገቢ አይደለም፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከላይ ከጠቀስናቸው ስህተቶቻቸው በተጨማሪም ሁሉም ሰው በህግ ፊት ዕኩል ነው የሚለውንም መርህ ሲጥሱ ተስተውለዋል፡፡ በርካቶች በሽብር ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግኝኙነት አድርገዋል ሊያደርጉ አስበዋል ተብለው በፀረ ሽብር ህጉ ማጣቀሻ ዘብጥያ በወረዱበት ሀገር እሳቸው ግን ፓርላማው የፀረ ሽብር ህጉን ባላነሳበት ሁኔታ በልዩ ልዩ መንገድ ከሚታገለሁ ሃይሎች ለመወያያት እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በእኔ ዕመነት ጠቅላይ ሚንሰት ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ሀገራዊ መረጋጋትንና የአንድነት መንፈስን ወደ ህዝበ በማጋባት በኩል አመታት የሚወስድ የመሰለውን ተግባር በጥቂት ቀናት ለማሳካት ጥረዋል፡፡

ሰዎኛ በሆነ መንገድ ከታሰበም ከህገ-መንግስቱ ጋር የተለያዩባቸው አንቀፆች ብዙ የሚያሰወቅሱ ላይሆኑ ይችሉ ፡፡ ነገር ግን የአንድ ሀገር የፖለቲካ ዕደገት መሰረታዊ መመዘኛ የህግ-የበላይነት እስከሆነ ድረስ የጠቅላይ ሚንሰትሩ ከህገ-መንግስት መኳረፍ ተራ ጉዳይ አድርጎ መደምደም አይገባም፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close