Connect with us

Business

የእምቦጭ አረምን በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦ የሚያስወግድ ማሽን ስራ ጀመረ

Published

on

የእምቦጭ አረምን በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦ የሚያስወግድ ማሽን ስራ ጀመረ

በጣና ሃይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም በዘመናዊ መንገድ ሰብስቦ ማስወገድ የሚችል ማሽን ትናንት በይፋ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።

በአማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የተገዛው ይኸው ማሽን አንድ ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን በሰዓት 5 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገኝ የእምቦጭ አረም የማስወገድ አቅም አለው፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ጎመንጌ በተባለው የሃይቁ ዳርቻ ትናንት በተካሄደው ስነ-ስርአት የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተርር በላይነህ አየለ እንደተናገሩት በሃይቁ ላይ የተጋረጠውን የእምቦጭ አረም ስጋት ለመቀነስ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡

እየተከናወኑ ካሉት ተግባራት መካከልም በህዝቡ ተሳትፎ የሚካሄደው የማስወገድ ስራ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን የክልሉ ባለሀብቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና በውጪ የሚኖሩ ተወላጆችም እየተሳተፉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

”አማጋ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከቻይና ሀገር ያስመጣው የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያ ማሽን ስራ እንዲጀምር መደረጉ የባለሀብቶች ተሳትፎ አንዱ ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ተመሳሳይ ማሽኖችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በቅርቡ የተቋቋመው የጣና ፈንድም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጪ ድጋፎችን በማስተባበር ሃይቁን ለመታደግ ሰፊ ርብርብ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አማጋ ላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ተወካይ አቶ ፍቅሬ ፎጌ የጣና ሐይቅ ከክልሉ አልፎ የሀገር ሀብት እንደመሆኑ ድርጅቱ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ በማድረግ ማሽኑን ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ስራ እንዲጀምር ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

ማሽኑ በሰአት 5ሺ ካሬ ሜትር ሃይቁን የወረረውን የእምቦጭ አረም የማስወገድ አቅም እንዳለው ገልፀው ማሽኑ ለተከታታይ 30 ሰዓት ያለእረፍት የመስራት አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የፌደራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ይማም በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ሃይቁን ለመታደግ እየተደረገ ላለው ርብርብ በምርምር፣ በፋይናንስና በቁሳቁስ ጭምር ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

በዚህ አመት ብቻ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን ”በስሩ የሚገኙ ኢንስቲትዩቶችም የሀይቁን ብዝሃ ሕይወት ለመታደግ የሚያስችሉ ምርምሮች እያካሄዱ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

የማእከላዊ ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ጣምያለው ሃይቁን በሚያዋስነው በጎንደር ዙሪያ ምእራብና ምስራቅ ደንቢያ ወረዳዎች ከ167ሺ በላይ አርሶ አደሮች በእምቦጭ አረም ማስወገድ ስራ መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሃይቁን የወረረውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ላለፉት 5 አመታት ጉልበታችንን አፍሰናል ያሉት ደግሞ የሀይቁ አዋሳኝ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አበረ ሽፈራው ናቸው፡፡

”የማሽኑ መምጣት ድካማችን ይቀንሰዋል ብለን ተስፋ አድርገናል” ያሉት አርሶአደር አበረ ከችግሩ ስፋት አኳያ በአንድ ማሽን የሀይቁን አረም ማስወገድ የማይቻል በመሆኑ ተጨማሪ ማሽን ተገዝቶ ሊመጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በማሽኑ የማስጀመሪያ ስነ ሰርአት ላይ ከፌደራል፣ ከክልልና ከማእከላዊ ጎንደር ዞን የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና የአካባቢው አርሶ አደሮች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

ማሽኑን በግዢ ለአበረከተው ለአማጋ የግል ድርጅት የክልሉ መንግስት ያዘጋጀው የእውቅና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ ለድርጅቱ ተወካይ በስጦታ ተበርክቷል፡፡

ምንጭ፦ ኢዜአ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close