Connect with us

Ethiopia

የኢሕአዴግ ወላጅ እናት የእድሜ ዘመን መሪዋን መረጠች

Published

on

የኢሕአዴግ ወላጅ እናት የእድሜ ዘመን መሪዋን መረጠች

የኢሕአዴግ ወላጅ እናት የእድሜ ዘመን መሪዋን መረጠች፤
(በኃይሉ ሚዴቅሳ በድሬቲዩብ)

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2010 (ድሬቲዩብ) ኢሕአዴግ ነፍሴ አራት ኪሎ ተሰብስቦ ችግር ሲፈታና ሲያስር መዋል ከጀመረ ሶስት ቀን ሆኖታል፡፡የእርሱ ችግር በጸበልም በሐኪምም አለያም በጠብመንጃ መታገስ ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን ያቅታል፡፡ፈጣሪ ይርዳው!! እርሱ እዚህ ተሰብስቦ ሲደክም ከ40 ዓመታት በላይ ለአስትምሕሮቷ ሲተጋላት የነበረችው ቻይና ግን የእድሜ ዘመን ፕሬዚዳንት መርጣለች፡፡

አዎ ሺ ጂንፒንግ በቻይና ምድር ሞት እንጂ ሥርዓት የማያወርደው ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲቀጥሉ ተወስኗል፡፡ ባሳለፍነው እሁድ 2958 ሰዎች ደግፈዋቸው፣ከሁለት ሰዎች ብቻ ተቃውሞ ገጥሞአቸው የ1.3 ቢሊዮን ሕዝብ አለቃ የሚሆኑበትን ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ አድርገዋል፡፡ከ1978 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ሲሰራበት የነበረው በየ10 ዓመቱ መሪ የመቀየር ፖሊሰ ከዚህ በኋላ ቀርቷል፡፡

ሕገመንግሥቱ ተሻሽሎ የወቅቱ የአገሪቱ መሪ ‹‹ንጉስ ሆይ ሺህ ዓመት ይንገሱ፤እድሜ ዘመዎንትንም ይግዙን›› ተብለው ተቀብተዋል፡፡ ይህ በቻይና የተደረገ ነው፡፡ቻይና በዚህ መልኩ ዘላለማዊ መሪዋን መርጣለች፡፡የአራት ኪሎው የጂንፒንግ ወዳጅ ግን አሁንም መሪ በሌላት አገር ውስጥ ተሰብስቧል፡፡

የቻይናን ሞዴል ተከትለው ገዥ የሆኑ የአፍሪካ መንግሥታት ቁጥራቸው ጥቂት አይደለም፡፡ከ22ቢሊዮን ዶላር የሚበልጥ ገንዘብ በአፍሪካ ኢንቨስት ያደረገችው ቻይና፣ከአንድ ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎቿ በዚሁ በአፍሪካ ውስጥ ይኖራሉ፡፡ሃገሪቱ በአሕጉሩ ልማት ላይ ግዙፍ ተዋናይ ነች፡፡ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በኮንጎ ኪንሻሳም፣በኤርትራም፣በጋናም፣በኢትዮጵያም ኢንቨስት እያደረገች ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት ደግሞ ርዕዮተ ዓለሟን ሳይቀር ቀድተው መንግሥታዊ አስተሳሰብ አድርገውታል፡፡በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ ሃገር እየመራ ያለው ኢሕአዴግ የሦሻሊስታዊ ሀልዮት ምንጩ ቻይና ነች፡፡የዚያች አገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለ ዴሞክራሲ መምጣቱን ማንሳት የማይሻው ኢሕአዴግ፣ምጣኔ ሃብታዊ ግስጋሴ ወደ ዴሞክራሲያዊ ለሚደረገው ጉዞ መደላድል እንደሆነ የሚገልጽ ያልተጻፈ ሕግ አለው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለሁሉም ነገር መልስ ይሆናል የሚል ይዘት ያለው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ሊቀመንበሩን የእድሜ ዘመን ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡ እንደ ኢሕአዴግ ላሉ ወዳጆቹ የሚያስተላልፈው መልዕክት ከባድ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡

ፓርቲው የአገሪቱን ሕገመንግሥት አሻሽሎ ሺ የዘላለም ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የወሰነው በጸረ-ሙስና ዘመቻ ላይ የጀመሩትን ሥራ ለማስቀጠል፣ቻይናን በዓለም ወታደራዊ መድረክ ልዕለ-ኃያል ለማድረግና በኢኮኖሚ ፖሊሲ መስክ የወጠኑትን ማሻሻያ ለመቋጨት ጊዜ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው ተብሏል፡፡ይህ ነው እንደ ኢሕአዴግ ላሉ ወዳጅ አፍሪካዊያን የማይጥም መልዕክት ያለው፡፡

ሺ ጀምረውታል የተባለው ለውጥ ቀጣይነት የሚኖረው እርሳቸው ሲኖሩ ብቻ ከሆነ ብሔራዊ ኪሳራ ነው፡፡ከ90 ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ፓርቲው፣3000 የሚጠጋ የፓርላማ አባል ያለው ድርጅቱ አንድ አዳኛችም ሺ ብቻ ናቸው ካለ ኪሳራ ነው፡፡

እርሳቸው አንድ ቀን የልብ በሽታ ወይም እንደ ስታሊን አደጋ ሲጥ ቢያደርጋቸው ሙስናውም ይስፋፋል፤የቻይና ልዕለኃያልነትም አፈር ይበላዋል ማለት ነው፡፡

ፍራንሲስ ፍኩያማ የተባሉት የዴሞክራሲ ተመራማሪ እንደ ሺ ጂንፒንግ ያሉ አምባገነን መሪዎች በዚህ መልኩ ሥልጣን ላይ መጥተው የእድሜ ልክ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ሊገጥም የሚችለውን ችግር ሰሞኑን ተንትነውት ነበር፡፡

እንደ ተመራማሪው ገለጻ ሺ አንድ ቀን በድንገተኛ ሕመም ቢያርፉ ሁለት አደገኛ ክስተቶች ይከሰታሉ፡፡አንደኛ የሥልጣን ክፍተት ይኖራል፤በዚህም በክፍተቱ ላይ የታየችውን ቦታ ለመያዝ በፓርቲው ልሂቃን በኩል ሽኩቻና ፓርቲ የሚያፈርስ አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል፡፡ሁለተኛ ማኅበረሰባዊና መደባዊ ግጭት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡

ይህን እኛ አገር ከሆነው ነገር ጋር አገናኝተን እንመልከተው፡፡በ2012 ነሐሴ (እ.ኤ.አ) አቶ መለስ ዜናዊ ድንገት ካለፉ በሁዋላ ሁለቱም ተከስተዋል፡፡

በወቅቱ ተፈጥሮ የነበረውን ክፍት ቦታ (ጠቅላይ ሚኒስትርነት) ለመያዝ በግለሰቦች ደረጃ ያን ያህል አለመግባባት ስለመከሰቱ የተባለ አልነበረም(አንዳንድ አለመግባባቶች እንደነበሩ ባይካድም)፡

፡ይሁን እንጂ አሁን አቶ ኃይለማርያም ድንገት ሥልጣን ሲለቁ ሁሉም ወንበሯን ለመያዝ ሽኩቻና አሉባልታ እያደረገ ነው፡፡እኔ ካልሆንኩ አገር መፍረሷ አይቀርም የሚል ዛቻም እያሰማ ነው፡፡ይህ ወዴት እንደሚያደርስ አልታወቀም፡፡

ሁለተኛው መደባዊና ማኅበረሰባዊ ግጭት መቀሰቀስ ነው፡፡በዚህ ረገድ የጎላ ማሳያ አለ፡፡አቶ መለስ ካረፉ በኋላ የጎላ መደባዊ ግጭት ባይታይም፣ዘር ላይ መሰረት ያደረገ ማኅበረሰባዊ ደም አፋሳሽ ግጭት ግን ተከስቷል፡፡ይህ የኮሙዩኒስት ፖለቲካን የሚያጠኑ ሰዎች “Big Man“ የሚሉት አካሄድ ውጤት ነው፡፡በስርህ ያሉት ሰዎች ሃሳብ አመንጪ ሳይሆን ታዛዥ፣ ፖሊሲ አውጪ ሳይሆን አድማጭ ከሆኑና መጨረሻ ላይ አንተ ከሞትክ መዳረሻህ እንደ አሁኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካና ፖለቲከኞች መሆን ነው፡፡

የቻይና እጣፈንታ ከዚህ ጋር ስለመያያዙ ጊዜ ነው-የሚያውቀው፡፡ግን የእድሜ ዘመን ፕሬዚዳንቷ ሺ ጂንፒግ “Big Man“ ሆነው ፈላጭ ቆራጭ ሊሆኑ ሕገመንግሥታዊ ይሁንታ አግኝተዋል፡፡

አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለምንጠብቀው ለኛ ለኢትዮጵያዊያንም ጥሩ ትምህርት አይሰጥም፡፡ የአገራችንን መሪ የሥልጣን ዘመን የማይገድብ ሕገመንግሥት ላለንና ቻይናን አርዐያ ያደረገ መንግሥት ለሚመራን ለእኛ እጅጉን ጥሩ ዜና አይመስልም፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close