Connect with us

Ethiopia

ዝክረ መተማ

Published

on

ዝክረ መተማ

ዝክረ መተማ
[ክቡር መተኪያ ሃይለሚካኤል በድሬ ቲዩብ]
(ክፍል አንድና ክፍል ሁለት)

“የኢትዮጵያ ልጅ ሆይ ልብ አድርገህ ተመልከት ኢትዮጵያ የተባለችው አንደኛ እናትህ ናት ሁለተኛ ዘውድህ ናት ሶስተኛ ሚስትህ ናት አራተኛም ልጅህ ናት አምስተኛም መቃብርህ ናት እንግዲህ የእናት ፍቅር የዘውድ ክብር የሚስት ደግነት የልጅ ደስታ የመቃብር አቃፊነት እንደዚህ መሆኑን አውቀህ ተነሳ”

የአጼ ዮሃንስ የክተት አዋጅ 1881 አመተ ምህረት

ይሄ የአጼ ዮሃንስ የክተት አዋጅ አክሱም በሚገኘው መቃብራቸው ላይ ተከትቦ ይታያል::አጼ ዮሃንስ የሃገራቸውን ዳር ድምበር ለማስከበር ጎንደር መተማ ድረስ ዘምተው ከተሰው በኋላ የደርቡሽ ጦር የራስ ቅላቸውን ቆርጦ ወስዶ ገበያ ለገበያ ሲያዞረው ከዋለ በኋላ አንድ ሙዚየም ውስጥ እንዳስቀመጠውና ከአርባ አመታት በኋላም የኢትዮጵያ መንግስት ከሱዳን ጋር ተደራድሮ የአጼ ዮሃንስን የራስ ቅል አስመጥቶ አጽማቸው አክሱም ላይ እንዲያርፍ እንዳስደረገ ሰምቻለሁ::እነሆ መጋቢት አንድ ቀን የተደረገውንና አጼ ዮሃንስ ለሃገራቸው ሲሉ የተሰዉበትን ታሪክ ይሄ ትውልድ የተከፈለለትን የደምና የአጥንት ዋጋ አይዘነጋ ዘንድ እንዘክረዋለን::

ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደኋላ ከክርስቶ ስ ልደት በፊትም ይሁን በኋላ ስፍረ ዘመኑ ተዘርግቶና ወደ ሶስት ሺህ አመታት ተቆጥሮ በሚዘከረው ታሪኳ ውስጥ አንድም ክፍለ ዘመን ያለ ጦርነት ያሳለፈችው የሰላም አመት የለም::ጥንተ ታሪኳና ገናና ስልጣኔዋ ከሩቅም ይሁን ከቅርብ ብዙ ጠላት እንድታፈራ ስላደረጋት ዙሪያ ገባዋ ያሉ ሃገራት በድንበርም ይሁን በማስገበር ሰበብ ሲወጓት ኖረዋል::

ኢትዮጵያም ጥቃቷን ስትመልስና ሉአላዊነቷን ስታስከብር ዛሬ ላይ ደርሳለች::ነገስታቶቿና ወታደሮቿ “የሃገሬን አንዲት ስንዝር መሬት ለጠላት አሳልፌ ከምሰጥ የመቃብር ድንጋይ እላዬ ላይ ቢጫን እመርጣለሁ” ያሉና የበሬ ግንባር ለምታህል ግዛት የደም ዋጋ የሚከፍሉ ጀግኖች ናቸው:: በዚህም የዛሬ 129 አመት በዚህ ሰሞንም የኢትዮጵያው ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሃንስ አራተኛ በመተማ ከወራሪው የደርቡሽ ሰራዊት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቀው ሲዋጉ ውለው መጋቢት ሁለት ቀን 1881 መተማ ላይ ተሰዉ::

ቅድመ ዮሃንስ ኢትዮጵያ

በየመንደሩና በየአውራጃው የራሳቸውን ወታደር እያደራጁ የደከመውን በዱላ የበረታውን በድርድር እያስገበሩና ግዛታቸውን እያስፋፉ የነበሩ መሳፍንትና መኳንንቶች ህልውናቸው ያከተመው የቋራው ካሳ (አጼ ቴዎድሮስ) ብርቱ ክናዳቸውን እያቀመሱ ጸጥ ለጥ አድርገው በንጉሰ ነገስትነት ማእረግ ነግሰው ካስገበሯቸው በኋላ ነው::

አጼ ቴዎድሮስ ለብዙ ዘመናት ተበታትና የነበረችዋን ሃገር ወደ አንድነት ያመጡ የምእተ አመቱ ታላቅ ንጉሰ ነገስት የነበሩ ቢሆኑም የአንድነቱ ችቦ ተቀጣጥሎ በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነበር መቋጫ ያገኘው::አጼ ቴዎድሮስ በትረ ስልጣኑን ጨብጠው ሃገር ሲያስተዳድሩ በነበረበት ወቅት ግን በየቦታው (የኋልኞቹ አጼ ዮሃንስና አጼ ምኒልክን ጨምሮ)በቴዎድሮስ አገዛዝ ያኮረፉና በትረ ስልጣኑን ለመያዝ ያደፈጡ የጎበዝ አለቆች በማእከላዊው መንግስት ላይ ሲያፈነግጡና በተለያየ መንገድ ላለመገዛት እምቢኝ ሲሉ እንደነበር የታሪክ ጸሃፍት ከትበውታል::

የአጼ ዮሃንሷ ኢትዮጵያ

አጼ ዮሃንስ ኢትዮጵያን ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ለአስራ ስምንት አመታት ያስተዳደሩ ታላቅ ንጉሰ ነገስት ናቸው::እንደነ ተክለጻዲቅ መኩሪያ አይነት ታላላቅ የታሪክ ጸሃፍት እንደሚሉት ስለ አጼ ዮሃንስ ይህ ነው የሚባልና ቁልጭ ብሎ በጽሁፍ ተከትቦ የተገኘና ስለትውልድ እድገታቸው እንዲሁም ስለልጅነታቸው ህይወት የሚናገር የሰነድ ማስረጃ አልተገኘም::ሆኖም ግን በተለያዩ የታሪክ መዛግብት እንደተነገረው የያኔው ካሳ (የኋላው አጼ ዮሃንስ)አባት የተንቤኑ ካሳ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ ስላስ ትባላለች::አጼ ዮሃንስ በአባታቸው በኩል የዘር ሃረጋቸው የጎንደርን ለብዙ ዘመን ካስገበሩት ከእነ ራስ ሚካኤል ስሁል የሚመዘዝና ንጉሳዊ ቤተሰብ ሊባሉ የሚችሉ ሰው ናቸው::

ከሽፍትነት እስከ ጠንካራ ንጉስነት

አጼ ዮሃንስ በጉልምስና እድሜያቸው በወቅቱ ስመ ገናና ለነበሩት ለአጼ ቴዎድሮስ በአሽከርነት ከቤተ መንግስታቸው ገብተው ነበር::ሆኖም ግን አጼ ቴዎድሮስ ለጉግሳ ለማሩና ከአጼ ዮሃንስ በአስራ አንድ አመት ለሚያንሱትና በአምቻ ጋብቻ ለተሳሰሩት ለአጼ ምኒልክ የደጃዝማችነት ማእረግ ሲሰጡ ለእርሳቸው የባራምባራስነት ማእረግ ተሰጣቸው::ይሄም አስኮርፏቸው ልባቸው ሸፈተባቸው::ከዚያም ወደ ትውልድ ሃገራቸው ወደ ትግራይ በመሄድ ሃይላቸውን እያጠናከሩና እያሰባሰቡ ቆይተው ጡንቻቸው በሚገባ ሲደድር የትግራይ ንጉስ ነኝ ብለው አወጁና አረፉት::

አጼ ዮሃንስ ከአጼ ቴዎድሮስና ከአጼ ምኒልክ የተውጣጣ የሚመስል ባህርይ ያላቸው ንጉስ ናቸው::በሃገራቸውና በህልውናቸው ላይ ለመጣው ምንም አይነት ምድራዊ ሃይል እንደ አጼ ቴዎድሮስ ጸባቸው የመረረ ሲሆኑ በዲፕሎማሲውና ወዳጅን በፍቅር የመያዝ ልዩ ጥበባቸው ደግሞ ከአጼ ምኒልክ ጋር በእጅጉ የሚያመሳስላቸው ነው::በዚህም አጼ ዮሃንስ ሃይላቸውን ለማጠናከርና በባህር ማዶ ያላቸውን ተቀባይነትና እውቅና ለማጠናከር ከፈረንሳዩ ንጉስ ከናፖሊዮ ቦናፓርት ጋር መልእክት መጻጻፍ ጀመሩ::ቀስ በቀስም ሃይላቸውን እያጠናከሩ ሄደው ለማእከላዊ መንግስት ስጋት እስከመሆን ደረሱ::

የአጼ ቴዎድሮስ ፍጻሜና የአጼ ዮሃንስ ንግስና

የኢትዮጵያ አንድነት ችቦ ለኳሽ የሆኑት አጼ ቴዎድሮስ ለሃገራቸው ከነበራቸው ቀናኢነትና ጽኑ ፍቅር የተነሳ ወታደራዊ ሃይላቸውን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ በማስታጠቅ ወራሪ ሃይልን ለመመከትና ታላቋ ኢትዮጵያን ለማጽናት አስበው በተለያየ ተልእኮ ውስጥ የነበሩ ሚሲዮናዊያንንና ሌሎች አውሮፓውያንን በግድ አስረው የጦር መሳሪያ እንዲሰሩላቸው ማስገደድ ጀመሩ::ሆኖም ግን ዜጎቻቸው የታገቱባቸው አውሮፓውያን ይበልጡኑም እንግሊዝ በጀነራል ናፒየር የሚመራ ጦር ልካ ዜጎቿን ለማስለቀቅ ወሰነች::

ለዚህም የሃገሩን መልክአ ምድር የአየር ንብረቱን መውጫ መግቢያውንና ሌሎች የንጉሰ ነገስት አጼ ቴዎድሮስን ወታደራዊ አቅም የሚያውቅ ሁነኛ ሰው አስፈልጓቸው ነበርና የቀድሞ ወዳጃቸውን ንጉሰ ትግሬ ዮሃንስን ለዚህ ዘመቻ አጯቸው::አጼ ዮሃንስም በተለያየ ግዜ ከእንግሊዞች የቀረበላቸው የጦር መሳሪያና የውትድርና አሰልጣኝ ውለታ ስላለባቸው እንዲሁም የቀድሞ ተቀናቃኛቸውን አጼ ቴዎድሮስን የዘውድ ዙፋን መውረስ ይሹ ስለነበር የእነ ናፔርን ጦር እስከ አጼ ቴዎድሮስ የጦር ሰፈር እስከ መቅደላ አምባ ድረስ እየመሩ አመጡና የአጼ ቴዎድሮስ ፍጻሜ ሆነ::በዚህ ግዜም የሸዋው ንጉስ ምኒልክ የአባታቸውን የንጉስ ሃይለመለኮትን ዙፋን ወርሰው “”ሞ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ምኒልክ ንጉሰ ነገስት” የሚል ማህተም ሲያስቀርጹ ዮሃንስም በበኩላቸው “ንጉሰ ነገስት ዮሃንስ ንጉሰ ጽዮን ዘኢትዮጵያ” የሚል ማህተም አስቀርጸው ሁለቱም የሃገሪቱ ንጉስ እኔ ነኝ እያሉ ማስተዳደሩን ቀጠሉ::

ከንጉሰ ትግሬ ወደ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ

እንግዲህ አንባቢ እንዲረዳ የሚያስፈልግ አንድ ቁም ነገር አለ::አሁን ባለንበት ዘመን ከአመታት በፊት ሶማሊያን በታላቅ እብሪትና በጥንካሬ ሲያስተዳድር የነበረው ሞሃመድ ዚያድ ባሬ ከስልጣን ከወረደ በኋላ አንድ ታላቅ የነበረችው ሃገር ሶስት ቦታ ተበታትና አንድም የጸና መንግስት ሳይኖራት እየተባላች ትገኛለች::

የሊቢያው ጠንካራ መሪ ሞአመር ጋዳፊ በአመጽ ከወረደና ከተገደለ በኋላም ያቺ ምድራዊ ገነት ሃገር ሊቢያ ሶስት ቦታ ተከፋፍላ እርስ በርሷ እየተናከሰችና እየተባላች የተኩስ መለማመጃ ሜዳ መስላ አለች::እንደ አጼ ቴዎድሮስ ያለ ጠንካራ ንጉስ ሲወርድ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ለሁለት የመከፈል አደጋ የረበበባት ቢመስልም በአጼ ዮሃንስ ብስለትና ጥንካሬ እንዲሁም በምኒልክ አርቆ አሳቢነት በ1870 አመተ ምህረት የልቼ ስምምነት ተብሎ ምኒልክ ንጉሰ ሸዋ እንዲሆኑና ለአጼ ዮሃንስ እንዲገብሩ አጼ ዮሃንስም ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ሆነው እንዲቀጥሉ ሆነው ተስማሙ::

አጼ ዮሃንስ ለንግስና ካበቃቸው ምክንያት ዋነኛው በወቅቱ ከአጼ ምኒልክ በተሻለ ወታደራዊ ጥንካሬ ስለነበራቸውና ግዛታቸውም ሰፊ ስለነበረ ቢሆንም በሃገሪቱ ደንብና ህግ መሰረት ንግስና የሚጸናው በጳጳስ እጅ ቅብአ ቅዱስ የተቀባው ንጉስ ስለሆነ በአለቃ ብሩና በመሃመድ አብዱራሂም አማካኝነት ለግብጹ ገዥ ለኬህዲቭ ኢስማኤልና ለፓትርያርኩ ለአባ ዲሜጥሮስ 20000 (ሃያ ሺህ )የማርያ ትሬዛ ብር ገጸበረከት ልከው አቡነ አትናቲዮስን የኢትዮጵያ ፓትረያርክ አስደርገው በማስሾም በጥር 13 ቀን 1864 አመተ ምህረት አክሱም ላይ ነገሱ::በአለ ሲመቱም ታላቅ እንደነበረ የሚመሰክሩት የአይን እማኞች አራት ሺህ ሰንጋ ሃምሳ ጉንዶ ማር አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ ገንቦ ማር ለድግሱ ማድመቂያ እንደዋለ ይናገራሉ::

በውስጥና በውጭ የነበረባቸው ጫና

ንጉሰ ነገስቱ በውስጥ በተለያየ ቦታዎች የሚነሱባቸው አልገብር ባይ ሽፍቶችና ራሶችን ሲዋጉ ነው የኖሩት ሁለት አስርት እንኳ በማይሞላ የንግስና ዘመናቸው ከሱዳኖች ከጣልያኖችና ከግብጾች ጋር አንዴ ሲሞቅ አንዴ ሲቀዘቅዝ የቆየ የጦርነት ወላፈን የእርሳቸውን ዙፋንና ሃገራችን ኢትዮጵያን ሲለበልባት ቆየ::ነገሩን ይበልጥ ያከፋው ግን የኢትዮጵያ ዋና የባህር በር የሆነው ትልቁ የምጽዋ ወደብ በግብጾች መያዙ ነው::ሃገራችን ኢትዮጵያም የውጭ ንግዷ ቱርክን ተክቶ ምጽዋን በያዘው በግብጽ መንግስት በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ሆነ::አጼ ዮሃንስ ይህንን የተጋረጠባቸውን ችግር በተደጋጋሚ በድርድር ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተው በአንድ የታሪክ አጋጣሚ የህይወት ስምምነት ደረሰላቸው::

የህይወት ስምምነት

እንግሊዞች በቀይ ባህርና አካባቢው ያላቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላትን ሱዳን ለመቆጣጠር ባሰቡ ግዜ ከግብጽ ጋር ግንባር ፈጥረው ሱዳንን ይወጉ ጀመር::ሆኖም ግን ከሱዳኖቹ ደርቡሾች የገጠማቸው ምከታ እጅግ አስደንጋጭ ነበር::ደርቡሾች ግብጾቹን በዱር በገደል እያሳደዱ ከምድር ይደባልቋቸው ጀመር::የሃገራቸውን መውጫ መግቢያ ጠንቅቀው የሚያውቁት ሱዳኖች ግብጾችን በከበባ መውጫ መግቢያ አሳጧቸው::

በተለይ ደግሞ በከሰላ አውደ ውጊያ ላይ ደርቡሾች ግብጾቹን አላፈናፍን አሏቸው::በዚህ ግዜ እንግሊዞች ሪር አድሚራል ዊልያም ሂዎትን ከአጼ ዮሃንስ ዘንድ ለተማጽኖ በመላክ ግብጾች በኢትዮጵያ ምድር አድርገውና የኢትዮጵያን የውግያ እርዳታ አግኝተው ከከበባው እንዲያመልጡ ለዚህ ውለታቸው ደግሞ በግብጾች የተያዘው ታላቁ የምጽዋ ወደብ ለኢትዮጵያ እንዲመለስ የህይወት ስምምነት የሚባለውን የውል ሰነድ አቀረቡ::

አጼ ዮሃንስም የውል ስምምነታቸው እውን ይሆን ዘንድ ታላቁን የአፍሪካ ጦር አዋቂ ራስ አሉላን ለዚህ ታላቅ ውጊያ አጯቸው::ራስ አሉላ አባነጋም ወደ ጦር ሜዳው ዘምተውና የሁለት ቀን መራር ትግል አድርገው ግብጾችን ነጻ ካወጡና ታላቅ ድል ከተቀዳጅጁ በኋላ ወደ ጦር ሰፈራቸው ተመለሱ::

የህይወት ስምምነት በዚህ መልኩ ከተፈጸመ ከግዜያት በኋላ አጼ ዮሃንስ ከሁለት ያጡ መሆናቸውን ተረዱት::እንግሊዞች እንኳን በቃላቸው መሰረት ምጽዋን ሊሰጧቸው ቀርቶ በበርሊን የቅኝ ግዛት ውል መሰረት ምጽዋን ለጣልያን አሳልፈው ሰጡ::አጼ ዮሃንስም የተረፋቸው ከደርቡሾች ጋር የመረረ ቂም መያያዝ ብቻ ሆነ::የግብጽን ሰራዊት ድባቅ እየመታ ሲያሸንፍ የነበረው የደርቡሽ ጦር የጋመ ቁጣውንና ቂሙን ሊወጣ ወደ አጼ ዮሃንስ ፊቱን አዞረ::ለዚህም ኢትዮጵያን ጠቅልሎ ለመውረር በአዋሳኝ ከተማዋ በጎንደር በኩል በጥር ወር በ1881 አመተ ምህረት ጦሩን ልኮ በኢትዮጵያውያን ላይ ከፍ ጭካኔ የተመላበት ወረራ አደረገ::አንዳንድ ጸሃፍክ ከሶስት ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በምርኮ ወደ ሱዳን ተወስደው በባርነት እንደተፈነገሉ ይናገራሉ::

ዘኪ ቱማል የሚመራው የሱዳኑ ጦር በውስጡ የተንቀለቀለውን የበቀል ስሜት ለማብረድ አሁንም ያገኘው ድል የበቃው አይመስልም::ጦሩን በጎንደር በኩል እስከ ደምቢያ ያስጠጋ ጀመር::አጼ ዮሃንስ በውጭ የሱዳን የግብጽና የጣልያን በውስጥ ደግሞ ከመኳንንቱ ጋር ስምምነት ማጣት እጅግ ፈታኝ ሆኖባቸዋል::ከአጼ ምኒልክ ጋር ፈጽሞ ስምምነት አጥተዋል::

ራስ አሉላ አባ ነጋን ከኔ ትእዛዝ ውጪ ከጣልያን ተዋግተካል ብለው ከጦር አዛዥነታቸው አንስተዋቸዋል:: (በተለይ የአሉላ አባ ነጋ ከጦር አዛዥነታቸው መነሳት በአንድ በኩል በዶጋሊ ውጊያ ላይ አምስት መቶ የጣልያን ወታደሮችን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው የደመሰሱትን ጀግና የጦር መሪ ሞራል መንካትና የሌላውንም ወታደር ስሜት መጉዳት ተደርጎ ሲታይ በአንድ በኩል ደግሞ እንግሊዞች በሴራ እና በተንኮል ተብትበዋቸው ተወዳጁንና ጀግናውን አሉላን ከአውደ ዉጊያው ገለል እንዳረጓቸው የሚናገሩ አሉ::)

በትግራይ በኩል ደግሞ ጣልያን እግር በእግር እየተከተለ ግዛቱን ሊያስፋፋ እንደ እባብ እየተንፏቀቀ እየመጣ ነው::እንግዲህ አጼ ዮሃንስ እንዲህ ባለው ፈታኝ ሁኔታ ነው ወደ መተማ የዘመቱት::በሶስት ግምባር የተሰለፈው የአጼ ዮሃንስ ጦር በቀኝ በኩል በራስ መንገሻ ጉግሳ በግራ ራስ ሃይለማርያም ጉግሳ ሲመራ የመሃሉ ደግሞ በራሳቸው በአጼ ዮሃንስ ፊት አውራሪነት የሚመራ ሆኖ የሱዳንን ጦር ሊገጥም ተዘጋጀ::

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የዛሬ 129 አመት የመተማ ጦርነት በመጋቢት አንድ ቀን ሲደረግ የዋለው በቅዳሜ ቀን ነበር::አንድ መቶ ሺህ እግረኛና ሃያ ሺህ ፈረሰኛ ጦር የሚመሩት አጼ ዮሃንስ የጦር ማዘዣው ኦምዱርማን የሆነውንና በዋና አዛዡ ከሊፋ አብዱላሂ በአዝማቹ ዛኪ ቱማል የሚመራውን ባለ ሁለት ዙር ምሽግ የገነባውን የደርቡሽ ጦር ማጥቃት ጀመሩ::

በዚያ አሰቃቂ ውጊያ ላይ አጼ ዮሃንስ የሚመሩት ጦር ድንገት ምሽጉን በወኔ ጥሶ ሲገባ አንዲት ጥይት የቀኝ እጃቸውን መትታ አቆሰለቻቸው::ሆኖም ግን ክዳቸውን በጨርቅ ጠቅልለው ጠላታቸውን መዋጋታቸውን ቀጠሉ::ከጥቂት ሰአታት በኋላ አንዲት ሌላ ጥይት የግራ ክንዳቸውን ሰንጥቃ ደረታቸው ላይ ተሰነቀረች::ይሄኔም በሰራዊቱ ዘንድ የአጼ ዮሃንስ በጥይት የመመታት ወሬ በስፋት ተወራ:: “ጦሩ ከፈታው ወሬ የፈታው ይብሳል” እንዲል የሃገ

ራችን ሰው የአጼ ዮሃንስ ጦር ተፈታ::ተደናገጠ::የኢትዮጵያ ጦርም መሸሽ በደርቡሽ ጎራዴ መሞሽለቅ በጦር መወጋት በጥይት መመታት እጣው ሆነ::አጼ ዮሃንስም በጦር አበጋዞቻቸው አጃቢነት ከወደቁበት ተነስተው ህክምና እያገኙ ሳለ ብዙ ደም ፈሷቸው በንጋታው መጋቢት ሁለት ቀን 1881 ህይወታቸው አለፈ::

ሰራዊቱም በአራት መንታ እያነባ የንጉሰ ነገስቱን አስክሬን ተሸክሞ ከድንኳኑ ከቦ ባለበት ሰአት የሱዳን ጦር ድንገት ቢደርስ “የንጉሳችንን አስክሬንማ ቢላ በአንገታችን ቢሰነዘር እንኳ አንሰጥም” ብለው እጅግ መራር ውጊያ ተዋጉ::ሆኖም ግን አይለው የመጡባቸውን የሱዳን ጦር ሊቋቋሙ ተሳናቸው::ለደርቡሾች የድል ጸሃይ የወጣች መሰለ::ቀን በጸሃይ ሌት በጨለማ ያባነናቸውን የአጼ ዮሃንስን አስክሬን አግኝተው የራስ ቅላቸውን ቆርጠው ገበያ ለገበያ ሲያሳዩት ዋሉ::

አጼ ዮሃንስ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ሲዋጉ ተሰው::ደማቸውም ደማቅ ቀለም ሆኖ በኢትዮጵያ የአንድነት ታሪክ መዝገብ ላይ ታተመ::ታላቁ ንጉሰ ነገስት አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ሲሰዉ ሃገሪቷን አንድነቷ ሳይሸራረፍ የጠበቁት አጼ ዮሃንስ በእግራቸው እንደተተኩት ሁሉ አጼ ዮሃንስም መተማ ላይ እንደተሰዉ የኢትዮጵያ የስልጣኔ አባት እምዬ ምኒልክ ተተክተው የኢትዮጵያ አንድነቷንና ዳር ድምበሯን ጠብቀው ለተተኪው ንጉስ አስረክበዋል::

በሱዳኖቹ ሃገርስ ምን ሆነ?

ደርቡሾች በድል ላይ ድል በአሸናፊነት ላይ አሸናፊነት ይዞ መጓዙ ምዙም አልቀናቸውም::እንደፈለጉ የሰው ሃገር እየወረሩ ድል ማድረጉን እንደሩቅ ግዜ ትዝታ ይቆጥሩትና እንደ ተረት ያወሩት ጀመር:: የቅኝ ገዥዋ እንግሊዝ አዛዥ ጀነራል ጎርዶን መሞት እጅጉ ያበሳጨው የእንግሊዝ ጦር ሆ ብሎ ወደ ሱዳን ዘምቶ አዛዡ ከሊፋ አብዱላሂን እጁን ያዙት:: የሞት ፍርድ ፈርደው ደሙም ደመ ከልብ አደረጉት::

መተማ ላይ ድል የቀናው ዛኪ ቱማልም በማእረግ ላይ ማእረግ በሜዳልያ ላይ ሜዳልያ ይሰገጥልኛል ብሎ ተስፋ ያደረገ ቢሆንም አዛዡ ከሊፋ አብዱላሁ በክህደት ጠርጥሮት አስሮ በችጋር አንገብግቦ ገደለው:: ኢትዮጵያኖች የነጻነት አየርን እየማጉ በራሳቸው ንጉስ በራሳቸው ወታደር በተድላና በደስታ ሲኖሩ ሱዳኖቹ የቅኝ ግዛት ቀምበር ከጫንቃቸው ላይ ለሰማንያ አመታት ገደማ ተጭኖ ሲያጎብጣቸው ኖረ::

ልብ እንበል….
የሃገራችንን የግዛት ወሰን ለማስከበርና ማእከላዊ መንግስትን ለማጠናከር ነገስታቱና መኳንንቱ በተለያየ ግዜ ይሆነኛል ይበጀኛል ያሉትን (በዛሬ ሚዛን ኢ-ሰብአዊ ልንለው የምንችለውን ነገር ጨምሮ)መንገዶች ሁሉ ተጉዘውበታል::

አጼ ቴዎድሮስ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማሰራት ከነበራቸው ህልም የተነሳ ጋፋት በተባለ ቦታ ከተራ መልእክተኞችና አንጥረኞች ጀምረው ቆዳቸው እስከነጣ ተራ ዜጋ ድረስ ሰብስበው በግዳጅ ብረት ሲያስቀጠቅጧቸውና የባሩድ ዱቄት ሲያስዝቋቸው ከርመው ህልማቸው እውን ሳይሆንና መድፉም ሳይሰራ ከወዳጃቸው ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ኩርፊያና ጸብ ተርፏቸው የመሞቻቸው ዋነኛ ምክንያት ሆነና አለፈ::

እዚህ ላይ አጼው ለሃገራቸው ካላቸው ጽኑ ፍቅርና ወታደራዊ ጀግንነት የተነሳ በወረራ የተያዘችውን እየሩሳሌምንም ጭምር ነጻ የማውጣት ፍላጎት እንደነበራቸው የእርሳቸውን ዳና እየተከተሉ ዝክረ ነገራቸውን ይከትቡ የነበሩ የታሪክ ጸሃፊያን መስክረዋል::

እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባውና ከስር አስምረን ልንይዘው የሚገባው ቁም ነገር የአጼ ቴዎድሮስ ጭካኔና የማይፈታ ግምባር የግል ሃብታቸውን ለማካበት የቤተሰባቸውን ህይወት ለመቀየር ወይንም የዘር ሃረጋቸውን እየመዘዙ የሌላውን ዘር ለማጥፋት ያቀደ ሳይሆን ስለዝች ደሃ ሀገር ስለአንዲት ኢትዮጵያ ብለው መሆኑን ነው::ለዚህም ደማቸውን እንዳፈሰሱላት አጥንታቸውን እንደከሰከሱላት እንደ ቀደሙት ጀግኖች አባቶቻችን ሆነው የገዛ ሽጉጣቸውን ጠጥተው ዳግም የማያገኙትን ህይወታቸውን ሰውተውላታል::
መተማ ሜዳ ላይ ደማቸውን ያፈሰሱት የአጼ ዮሃንስም ጉዳይ

ከዚህ ከአጼ ቴዎድሮስ ጀግንነት ተነጥሎ መታየት የለበትም::አጼ ዮሃንስ ለአጼ ቴዎድሮስ በአሽከርነት ካገለገሉበት ቤተ መንግስት ሸፍተው ወጥተው ወደ ሃገራቸው ወደ ትግራይ ከተጓዙበት እለት አንስተው ለእንግሊዟ ንግስትና ለፈረንሳዩ ንጉስ ለናፖሊዮ ቦናፓርት የወዳጅነት ደብዳቤ በመጻፍ ወታደሮቻቸውን በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ለማጠናከር ብርቱ ጥረስ ሲያደርጉ ቆይተዋል::ያም ጥረታቸው ሰምሮላቸው 12 መድፎችን ዘጠኝ መቶ ጠመንጃዎችንና ከብዙ ጥይት ጋር ለማግኘት ችለዋል::በወቅቱ የጦር መሳሪያ የበላይነት ሃገርን ለማስከበርና ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ወደር የሌለው አይነተኛ መንገድ መሆኑን ቀደም ብለው የተረዱት አጼ ዮሃንስ አድዋ ላይ ንጉስ ተክለጊዮርጊስን በአስደናቂ ሁኔታ ድል ነስተው ወደ ንግስና መጓዛቸው ጥሩ ማሳያ ነው::

በተለያየ የታሪክ ጸሃፍት ዘንድ የሚወቀሱበትና ከጀነራል ናፒየር ጋር የነበራቸው ጥሩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም ከዚህ ተነጥሎ መታየት ያለበት አይመስለኝም:: እርግጥ ጀነራል ናፒየር በአጼ ዮሃንስ እየተመራ መጥቶ መቅደላ አምባን ለመቆጣጠር ችሎ ነበር:: ለአጼ ቴዎድሮስም ሽንፈት የዉሃ መንገድ ሆኖ አመችቶ ሊሆን ይችላል:: ነገር ግን እዚህ ጋር ልብ ማለት ያለብን ቁምነገር በወቅቱ እንደ እንግሊዝ ያለች የአለም ሃያል ሃገር (እንደዛሬዋ አሜሪካ) ዜጎቿ በጥቁር ህዝቦች ታግተውባት ዝም ልትል እንደማይችል ግልጽ ነው:: የናፔር ጦር እንደ አጼ ዮሃንስ አይነት ተባባሪ ባያገኝ እንኳ ሌሎች አጼ ቴዎድሮስ ላይ ያቄሙ መኳንንቶችን አስተባብሮ መምጣቱ የሚቀር ጉዳይ አይመስልም::

አብዩ ጉዳይ ግን የአጼ ዮሃንስና የአጼ ቴዎድሮስ የስልጣን ሹክቻ ከአጼ ዮሃንስና ከአጼ ምኒልክ የስልጣን ሹክቻ ያልተለየ የታሪክ ሂደት ነው:: እንዲያዉም እንግሊዞች ለአጼ ዮሃንስ የገቡትን ቃል ጠብቀው ሃገሪቷን ከነ ዳር ድምበሯ አስረክበው መውጣታቸውና በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የተከሉትን የቅኝ ግዛት ችካል አለመትከላቸው አንድም የአጼ ዮሃንስን የረቀቀ የዲፕሎማሲ ጥበብ አንድም የደረጀ ወታደራዊ አቅማቸውን ያሳያል ብዬ አምናለሁ::

እናም አጼ ዮሃንስ ከናፔር ጋር ማበር ቀደም ባለው ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በነበራቸው ቁርሾና የስልጣን ይገባኛል ጥያቄ መነሻነት እንጂ ሃገርን እንደ ባንዳ አሳልፎ ከመስጠት ፍላጎት የተነሳ እንዳልሆነ የናፔር ጦር ወዲያው ሃገራችንን ለቆ መውጣቱ (የድካሙንና የወራሪነቱን ድርሻ ቅርስ መዝረፉ እንዳለ ሆኖ)እንዲሁም አጼ ዮሃንስ የሃገራቸውን ሉአላዊነት አስጠብቀው ለዳር ድምበሯ መከበር ሲሉ አንገታቸውን መቀላታቸው ጥሩ ማስተማመኛ ይመስለኛል::

የዛሬ ዛሬ ጥቂት ምሁራንና ኤሊቶች

“የጎንደሬውን የአጼ ቴዎድሮስ ዘውድ እንዴት ትግሬው አጼ ዮሃንስ ይወስዳል ?” : “የትግሬውን የአጼ ዮሃንስን በትረ ስልጣን የሸዋው አማራ ምኒልክ እንዴት ይነጥቃል?” : “የወለዬውን የልጅ እያሱን ዘውድ እንዴት የሸዋዋ ዘውዲቱና የሃረሩ ሃይለስላሴ ይነጥቃሉ ?”::

“በዚህ እና በዚህኛው ተንኮል ነው እንጂ ይሄኛው ስልጣን ከዚህ ጎሳ ወይም ከዚህ ጎጥ ወይም ከዚህ ብሄር አይወጣም ነበር” እየተባባሉ ለስልጣን ቅሚያ አንዱ ንጉስ በአንዱ ላይ ግዜና ወቅቱ እንዳመጣው ፈሊጥ ነገስታቱ ያደርጉት የነበሩትን ፍልሚያ ወደኋላ መቶ ምናምን አመት እየጎተቱ የብሄር ታፔላ መለጠፍና እራስን ከኢትዮጵያ አንድነት መንፈስ ማውጣት እጅግ መውረድ ነው ብዬ አምናለሁ::

የአጼ ቴዎድሮስ በጠላት እጅ ከመውደቅ እራስን መሰዋት ጀግንነት ሆኖ የአጼ ዮሃንስ ለዳር ድምበሯ ሲዋጉ መሞትና አንገት መቆረጥ ግድ ካልሰጠህ አደራ አንተ ደረትህን ነፍተህ ኢትዮጵያዊ ነኝ እንዳትል::የአጼ ዮሃንስ የሃገር ሰው በመሆንህ ብቻ የእርሳቸው መተማ ላይ መሰዋትን እንደ ጀግንነት ቆጥረህ የአጼ ቴዎድሮስ በጠላት እጅ ከምወድቅ ሽጉጤን ብጠጣ ይሻላል ብሎ መሰዋትን የምታጣጥል ከሆንክ አንተ እውነተኛው ጎጠኛ ነህ::

የአድዋ ድልን ከአጼ ምኒልክ የንጉስነትና የአመራር ብስለት ነጥለህ እያንቆለጳጰስክ ግብጾች አፈር ከድሜ በልተው የሸሹበትን የጉንደት የኩአቲትና የጉራእ ጦርነት ለአጼ ዮሃንስ ብቻ የምትሰጥ ከሆነ ቆም በልና የራስህን የታሪክ እውቀትና ኢትዮጵያዊነት መርምር::

ስለ አንድነታችንና ስለዝህች ኢትዮጵያ ስለምንላት ሃገር ሉአላዊነት ሲባል ጊዜው እንደፈቀደና እንደየድርሻው ወይንም እንደየሰውዬው ምርጫ መንገድ :በዘመነ መሳፍንት ተበታትና ከነበረችው ኢትዮጵያ አንድነት ጀምሮ እስከ ፓን አፍሪካኒዝም ድረስ ነገስታቶቻችን የደምም የላብም የእውቀትም መስዋእትነት እንደየደረጃው ከፍለዋል::

እርግጥ ከሰው ስህተት ከብረት ዝገት አይጠፋምና : ደግሞም ትክክል የመሰላቸው መንገድ በዛሬው ሚዛን ጥሩ ላይሆን ይችላልና መልካምነታቸውና አርአያነታቸውን ወስደን ስህተታቸውን ከቻልን ለታሪክ ተመራማሪ ትተን ካልቻልን በቅን ልቦና ተወያይተንበት እስካላለፍን ድረስ ወደ ኋላ እያዩ ወደ ፊት ያዳግተናልና እዚህ ጋር መንቃት ያለብን ይመስለኛል::

የአጼ ቴዎድሮስን አንድነት ለማስከበር ከመሳፍንቱ ጋር የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሰው እጅ የሰው እግር መቁረጥና ሌሎች በዛሬ ሚዛን “ኢ ሰብአዊ”የሚባሉ እርምጃዎችን ያካተተ የጦርነት ውጤት ነው::አጼ ዮሃንስም አጼ ቴዎድሮስ የጀመሩላቸውን የታላቋ ኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት ለማምጣት ብዙ ደም ያፋሰሰ ጦርነት አካሂደው ሲያበቁና ለሃይማኖታቸው እጅግ ቀናኢ ከመሆናቸው የተነሳ ቦሩ ሜዳ በተባለው ስፍራ የሃይማኖት ክርክር አስደርገው ሁሉንም ዜጋ ክርስትና ካላስጠመቅኩ ብለው የፈራውን በውዳጅ እምቢ ያለውን በግዳጅ ክርስትና አስነስተዋል::

አጼ ምኒልክ በወላይታ በአርሲ በሲዳሞ በጉራጌ በሃረርና በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች አልገብር ብሎ ያመጸባቸውን ሽፍታና መሳፍንት ከነወታደሩ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ ፈጅተውታል::ይሄን ሁላ የምንጠቅሰው የነገስታቱን ሃጥያትና ጭካኔ ለማጉላት ሳይሆን ለሃገር አንድነት ሲባል ሁሉም ንጉስ ከዛሬው “ሰብአዊነት” የወጣ ተግባር ይፈጽሙ እንደነበርና ያለ ደም መፋሰስም መሰረቱ የጸና ምሰሶው የረጋ ሃገር እንዳሌለ ለማሳየት ጥቂት ምሳሌ ይሆናል ብለን ነው::

እኛም አንዲት ነገር ጠብ ላይልልን ነገስታቱን በብሄር ከፋፍለን እንደ ብሩንዶ ስጋ እየበለትን መከፋፈላችንን ተወት አርገን ታሪካችንን መበሻሸቂያ ሳይሆን ትውልድን ማስተማሪያ ብናደርገው መባረክ እና መታደል ነው ብዬ አምናለሁ::

የሃገራችን አዝማሪ አቅራና ገጣሚ ስለ አጼ ዮሃንስ የተቀኘውን ከብዙው እጅግ በጥቂቱ ለዝክረ ነገር ታህል አንስተን ወጋችንን እንቋጭ::የአጼ ዮሃንስ ሞት ካንገበገባቸውና እንደ አንድ ተራ ወታደር አውደ ውጊያ ላይ በመሳተፋቸው የሞት ምክንያታቸው ሆኗል ብሎ ያሰበ አንድ ገጣሚ
-አጼ ዮሃንስ ሞኝ ናቸው
እኛም በመሃል ናቅናቸው
ንጉስ ቢሏቸው በመሃሉ
ወሰን ጠባቂ ልሁን አሉ
*********** ብሎላቸዋል::

በተደጋጋሚ ሃገራችንን ለመውረር ከጥንት ጀምራ ምራቋን ስትውጥና ስትቋምጥ የነበረችውን ግብጽ አጼው ከአንዴም ሁለቴ ብርቱ ክንዳቸውን አቅምሰው መመለሳቸውን ለማስታወስ
እስካሁን ድረስ አልጠፋ አጥንቱ
ግብጽን እንደ በልግ የወቃበቱ
*********** ተብሎላቸዋል::
በመጨረሻም ለኢትዮጵያ ዳር ድምበር መከበር ህይወታቸውን ቤዛ አድርገውላት ስለሞቱት አጼ ዮሃንስ እንዲህ ተብሎ ነበር::
በጎንደር መተኮስ በደምቢያ መታረድ አዝኖ ዮሃንስ
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ
ክብር ለዳር ድምበራችን መከበር ደማቸውን ላፈሰሱ ጀግኖች አባቶቻችን::

(FACEBOOK.COM /KIBUR METEKIA HAILEMICHAEL )

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close