Connect with us

Business

ድንጋይ በዶላር የምትገዛው ኦሮሚያ

Published

on

ድንጋይ በዶላር የምትገዛው ኦሮሚያ

ድንጋይ በዶላር የምትገዛው ኦሮሚያ | በኃይሉ ሚዴቅሳ

የአዲስ አበባ ብርጭቆና ጠርሙስ ፋብሪካ ባቢሌ አካባቢ የፋብሪካ ግብዓት ማምረቻ ቦታ አለው፡፡በዚህ ማምረቻ ቦታ ላይ የተቀጠሩት ሰራተኞች በሙሉ የአካባቢው ሰዎች ናቸው፡፡

ይህ ኩባንያ 200 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሌላ ፋብሪካ በቦታው ለመገንባት እና ተጨማሪ የሥራ ዕድል ምንጭ ሊሆን ጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ሆኖም በአካባቢው ማንነታቸው የማይታወቁ ጎረምሶች በተደጋጋሚ ምክንያቱ የማይታወቅ ገንዘብ እየጠየቁ ካልተሰጣቸውም ከቦታው የሚንቀሳቀሱ የኩባንያውን መኪኖች እየሰባበሩ አስቸገሩ፡፡እናም ፋብሪካው ሥራውን እርግፍ አድርጎ ተወ፡፡

ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይኖረዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሕዝብም ይህንንም አጣው፡፡ከፋብሪካው ሥራ አስኪያጆች አንዱ ይህንን ይላል፡፡

ምሬት በሚያደምጠው አዳራሽ ውስጥ ሌላ ተሳታፊ እጃቸውን አወጡ፡፡‹‹የኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት አደጋ ውስጥ ከገባ ቆየ፡፡የክልሉ መንግሥት ለወጣቶች መሬት ለማስረከብ ሲል ባለሃብቶችን የሚነጥቅበት መንገድ ያልተጠናና መናበብ የሌለው፣ወረዳዎችና የታችኛው መዋቅር በአግባቡ ያልተረዳው ነው›› ብለው በስሜት እየተናገሩ ቀጠሉ፡፡

እኒህ ሰው ፈሙ ኢንዱስትሪያል ኢንጀነሪንግ ከተባለ ኩባንያ የመጡ ናቸው፡፡በኦሮሚያ ክልል አንድ ወረዳ ላይ የጅብሰም ጥሬ ዕቃ ማምረቻ ፋብሪካ አላቸው፡፡‹‹ድርጅቴ …››አሉ ሰውዬው፣በዚሁ በኦሮሚያ ክልል ስላለው ድርጅታቸው እያወሩ፡፡‹‹ድርጅቴ ምርት ካቆመ 13 ወራት ተቆጠሩ፡፡በቦታው ቀጥሬያቸው የነበሩትን ሰራተኞችም በትኛለሁ››፡፡ሰውዬው ይህንን ያደረጉት በአካባቢው ጎረምሶችና አስተዳደር ጥቃት ስለደረሰባቸው ነው፡፡

ሰውዬው ሳግ እየተናነቃቸው ቀጥለዋል…
‹‹ጥሬ ዕቃም ከውጭ እየገዛን ነው፡፡የሚገርመው 85 በመቶ የሚሆነው የጅብሰም ምርት የሚሰራው ከድንጋይ ነው፡፡እንግዲህ ድንጋይ በውጭ ምንዛሬ እየገዛን ነው ማለት ነው፡፡ይህ የሆነው በአገራችን ያለውን ድንጋይ ሕጋዊ ሆነን፣ግብር ከፍለን፣ፈቃድ ወስደን፣ እየሰራን ስለተዘጋብን ነው፡፡››

የአዋሽ መልካሳ አልሙኒየም ሰልፌት ፋብሪካ ምክትል ሥራ አስኪያጅ እንደሚናገሩት ከሁለት ሳምንት በኋላ ምርት ማቆም ይጀምራሉ፡፡ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ‹‹ግብዓት እያመረተ የሚልክልን ድርጅት በኦሮሚያ ክልል ነው የሚገኘው፡፡ከወራት በፊት ግን በአካባቢው ሰዎች ጥቃት ስለደረሰበት ማምረት መላኩን አቁሟል፡፡››

ይህ ሁሉ እየተደመጠ ያለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ ነው፡፡በጉባኤው ላይ በአገሪቱ የማምረቻው ዘርፍ ያለበት ደረጃ እና የባለሃብቶች ፈተና እየተተረከ ነው፡፡

ሌላኛው ተሳታፊ ቀጠሉ፡፡ከኢስት ሴሜንት የመጡ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡ፋብሪካቸው ጥሬ ዕቃ የሚያገኘው 25 ኪሎሜትር ከተጓዘ በኋላ መሆኑን አብራሩ፡፡‹‹ ይቺ 25 ኪሎሜትር መንግድ ፒስታ ነች…እናም አቧራ ቦነነብን ያሉት ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይቺን 25 ኪሎሜትር አስፓልት መንገድ አድርጋችሁ ካልገነባችሁ መኪኖቻችሁ አያልፉም ብለውን ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ምርት አቁመናል፤ሰራተኛም በትነናል›› ብለዋል፡፡

ይህ ሁሉ የተሰማው በኦሮሚያ ክልል የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ችግራቸውን ሲናዘዙ ነው፡፡በእውነቱ ኢንቨስትመንት በኦሮሚያ አደጋ ውስጥ ነው፡፡ለወትሮው በርካታ ባለሃብቶች ግርር ብለው የሚመርጡት ኦሮሚያ አሁን ተስፋው እየጨለመ ነው፡፡ይህ ችግር ምናልባትም ዘለግ ላሉ ዓመታት ሊቀጥል ይችላል፡፡ምክንያቱም ባለሃብቱ ኦሮሚያን ማመን ከብዶታል፡፡

አንዳንድ ኢንቨስተሮችም ፋብሪካዎቻቸውን ከክልሉ እየነቀሉ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ ነው፡፡ኦሮሚያ ክልል ከየትኛውም የአገሪቱ ክልል የበለጠ ፋብሪካዎች ያሉት ክልል ነው፡፡የሥራ አጥ ቁጥሩን ሲያቃልል የኖረው በነዚሁ ፋብሪካዎች ነው፡፡ሚሊዮኖች ጉሮሮአቸውን አልሰው የሚያድሩትም በነዚህ ፋብሪካዎች ተቀጥረው በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መድረክ ላይ ባለሃብቶቹ ያነሱት ሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው የክልሉ መንግሥት ያልተጠናና ያልተናበበ ውሳኔ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የአካባቢው ወጣቶች ጉልበተኛነትና ሕገወጥነት ነው፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close