Connect with us

Ethiopia

ህልሟን የተነጠቀች ሀገር

Published

on

ህልሟን የተነጠቀች ሀገር

ህልሟን የተነጠቀች ሀገር / አፄ ቴዎድሮስ Vs የዋለልኝ መኮንን
ይነገር ጌታቸው በድሬቲዩብ

በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አፄ ቴዎድሮስ የመጀመሪያው ህልመኛ መሪ መሆናቸው ከሞላ ጎደል የሚያሰማማ ነው ፡፡ በዘመነ መሳፍንት ወቅት የተበጣጠሰችውን ሀገር አንድ ለማድረግ የደከሙት ንጉሱ በኋላ ላይ በኃይልም ቢሆን አንዲት ኢትዮጵያን ለመመስረት ችለዋል፡፡

የአፄ ቴዎድሮስ ህልም ግን በዚህ ብቻ የተገታ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ስርዓት ሊበጅላት ይገባል የሚል ሀሳብ ነበራቸው፡፡ ንጉሱ በወቅቱ በኃይል አንድ ያደረጓትን ሀገር በስርዓት ወደፊት ጠንካራ ለማድረግም የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አካሂደዋል፡፡

ነገር ግን ወጥናቸው ከዳር የደረሰ አልነበረም፡፡ ገብረ ህይወት ባይካድኝ “አፄ ምኒሊክ እና ኢትዮጵያ” በተሰኘ መፅሀፋቸው አፄ ቴዎድሮስ በህልፈታቸው ሰሞን “የሀገሬው ሰው በኔ ላይ የተነሳው ስርዓት ስለሌለው ነው ማለታቸውን ይገልጻል፡፡

እዚህ ላይ ግን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ እንደ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል ያስፈልጋል የሚሉት ስርዓት ምን ነበር ? በተለይም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ገዥዎች በአመፁ ጊዜ የወሰዱት እርምጃስ ምን ይመስላል ? በታሪክ ላይ ምርምራቸውን ያደርጉ ምሁራን አጼ ቴዎድሮስ ምኞታቸው እንጅ የሄዱበት መንገድ ተገቢ አልነበረም ይላሉ፡፡

ባህሩ ዘውዴ What Did We Dream? What Did we achtive? And Where are we heading? በተሰኘ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር ባቀረቡት ጥናታቸው የአፄ ቴዎድሮስ መንገድ በዘመኑ ዓውድ ሲታይ በተቀናቃኝ ላይ የታወጀ ቀይ ሽበር ነው ይሉታል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ህልማቸውን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ስህተት ቢሆንም ህልማቸው ግን እንደ ህልም ስህተት አልነበረም፡፡ በመሆኑም ድህረ የጣሊያን ወረራን ተከትለው የመጡት የሀገሪቱ ልሂቃን የአጼ ቴዎድሮስን ህልም ለመፍታት ተንቀሳቅሰዋል፡፡ ከዚህ በፊት ባልታየ መልኩም አፄ ቴዎድሮስን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ በርካታ ተግበራትን ሲፈፅመሙ ተስተውለዋል፡፡ በርካታ መፅሀፍት እና ተውኔቶችም የንጉሱን ታላቅነት ለማንንፀባረቅ ተደርሰዋል፡፡ (በኔ ግምት አጼ ቴውድሮስ እንደዛ ዘመን የተሞገሱበት ወቅት የለም፡፡)

በአውሮፓ ያሉ የኢትዮጵያዊያን ተመሪዎች ህብረትም ያሳትም የነበረውን መፅሔት በንጉሱ የፈረሰ ስም “ታጥቃ” ያለበት ምክንያት ለጊዜው ፖለቲካዊ ጉዞው ከአጼ ቴዎድሮስ በላይ መደላደል ስለሌለ ነበር፡፡

በ1960ዎቹ መባቻ የንጉሱን ህልም ህልማቸው ያደረጉ የወቅቱ ተማሪዎች በፖለቲካው በኩል የነበራቸው ተሳትፎ እየጎላ የመጣ ሲሆን በሀገሪቱ ያለው ስርዓት ኢትዮጵያን ወደ ኋላ እየጎተተ በመሆኑ ሊስተካከል ይገባዋል የሚል ጥያቄን በተደጋጋሚ አንስተዋል፡፡

ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በ1961 ዓ.ም መረን እያለፈ የሄደ ሲሆን የተቃውሞ ሰልፎችን ማካሄድ እና ትምህርትን ማቋረጥን በመሰሉ ተግባራት የታጀበ ነበር፡፡ ይህን ዘመን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ህልሟን ለመውለድ ምጥ የበዛበት ጊዜዋ አድረገን ልንመለከተው እንችላለን ፡፡

ምክንያቱም ዋለልኝ መኮንን “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” የተበባለ ፅሁፍን ለንባብ ያበቃበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከረኩት አፄ ቴዎድሮሳዊት አንዲት ኢትዮጵያ በምትቀነቀንበት በዚያን ዘመን ከዚህም ከፍ ሲል በንጉሱ ፈረስ ስም በሚጠራው ታጠቅ መፅሔት ላይ ከአንድነት ሞዶ ያለን ሀሳብ የያዘ ፅሁፍ መውጣቱ ብዙ ጥያቄን ያስከተለ ነበር፡፡

ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖራቸው ሳይሆን ከሆነ ብሔር በመፈጠራቸው ነው ጭቆና የሚደርስባቸው የሚል ክርክርም መነሳት ጀመረ፡፡ ዋለልኝ መኮንን የብሔር ጭቆናን ሀሳብ ፈጠረው ወይንስ የብሔር ጭቆናው ሀሳብ ነው ዋለልኝን የፈጠረው የሚለው ግን መሰረታዊ ጥያቄ ሆኖ ዛሬም ሲነሳ ይስተዋላል፡፡

ዋለልኝ እንደ ሮማን ፕሮቻዝካ
ሮማን ፕሮቻዝካ ከጣሊያን ወረራ ዘመን በፊት አዲስ አበባ ላይ የከተመ ኦስትሪያዊ የህግ ባለሙያ ሲሆን “Abyssinia the power barrel” የተባለ መፅሀፍን በወረራው ዋዜማ ሰሞን በ1928 ለንባብ አብቅቷል፡፡ ፕሮቻዝካ ከፊል ዕውነት ከፊል ተረት በሚመስል መፅሀፍ ኢትዮጵያዊያን ለነጮች ያላቸው ንቀት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ይተርካል፡፡ በዚህ ሳያበቃም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ወደፊት ለአለም ስጋት መሆኗ አይቀርም በማለት የራሱን ምክር ለአውሮፓውያን መንግስታት ያስተላልፋል፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች ያሏት ሀገር በመሆኗ እነሱን በመከፋፈል ሀገሪቷን ማድከም ይቻላል ሲልም ይገልጻል፡፡

የፕሮቻዝካ የብሔሮችን ልዩነት ካጎላን ኢትዮጵያ እንደ ሀገር አትቀጥልም የሚል አስተሳስብ ሰይጣናዊ የጠላት ሴራ ተደርጎ በመቆጠሩ በጊዜው ብዙ ቦታ ያገኘ አልነበረም ፡፡ ይሁን እንጅ ሀሳቡ ከዚያ ዘመን ራቀ እንጅ ጨርሶ ሊጠፋ የሚችል አልነበረም ፡፡በዚህ የተነሳም በ1960ዎቹ መጀመሪያ ይኼው የጠላት ሴራ የተባለ ሀሳብ ሀገራዊ መልክ ተላብሶ መሰማት ጀመረ ፡፡አንዳንድ ምሁራን ይህን የፕሮቻዝካ ሀሳብ በመተግበር በኩል የዋለልኝን ያህል ባለውለታ የለም የሚሉትም በዚህ የተነሳ ነው ፡፡

አለም እሸቴ “on the question of Ethiopian Nationa liyes” walelegn as roman prochazka” በተሰኘ ጥናቱ “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” የሚለው ፅሁፍ በዋለልኝ ብቻ የተቀነባበረ ነው ለማለት እንደሚቸገር ይገልጻል፡፡ ለዚህ ሀሳቡ ደግሞ ጠንካራ መከራከሪያ አድርጎ የሚያቀርበው የወቅቱን የ CIA ኢትዮጵያ የማፈራረስ ሴራ መሰረት በማድረግ ነው፡፡

እንደሚታወቀው በ1961 ዓ.ም CIA በኢትዮጵያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ ውስጥ የነበረው ተሳትፎ እያደገ የመጣበት ወቅት ነበር፡፡ ለአብነት ያህል የኤርትራን ትግል ውስጥ ለውስጥ በመደገፍ በኩል የዚህ ድርጅት ሚና የጎላ እንደነበር ሲገለፅ ይሰማል፡፡

የራሱን ዕድል በራስ መወሰን አቀንቃኙ ፖል ሄንዝ በኢትዮጵያ ኑራቸውን ማድረጋቸውና ይህን አስተሳሰባቸውን በይፍም ባይሆን ውስጥ ለውስጥ መንዛታቸው CIA እና ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበራቸውን ጉዳይ በድጋሚ በውሉ እንድናጤን ያስገድዳል፡፡ አለም እሸቴ ቀደም ተብሎ በተጠቀሰ ጥናቱ ዋለልኝን ያነሳውን ሀሳብ ከ CIA ተልዕኮ የተለየ አይደለም የሚል ክርክር ያነሳል፡፡

የአለምን መከራከሪያ ሙሉ በሙሉ መቀበል አዳጋች ቢሆንም እንኳን ከዋለልኝ ጀርባ ማን ነበር የሚለውን ጥያቄ መልሶ መላልሶ ማንሳት ግን ሀጥያት የሚሆን አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ብዙ ፍንጮች አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ኢቪሊን ፋረከስ Fractured States and U.S. Foreign Policy በተባለ መፅሐፉ አሜሪካ በ1960ዎቹም ቢሆን በኢትዮጵያ የነበረዉን የራስን ዕድል በራስ መወሰን ሃሳብ ትደግፍ እንደነበር መግለፁን ልብ ይሏል ፡፡

ልደቱ አያሌው “መድሎት” በተባለው መፅሀፍ ሶሻሊዝምን ለሚያቀነቅነው ዋለልኝ በበቂ ሁኔታ ለመደብ ትግል መሰረት የሚሆን ነገር በማጣቱ ብሔር የሚልን ጉዳይን ተጠቅሞበታል ይላል፡፡ ዋለልኝ ኢምፔራሊስትም ይሁን ሶሻሊስት በአንድ ነገር ላይ ግን መስማማት ያስፈልጋል፡፡ እሱም የብሔር ጭቆና ዋለልኝ ስላነሳው ብቻ ፖለቲካዊ መሰረት ኑሮት ወደፊት ሊራመድ አይችልም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ሁለተኛ ምኞቷ አልያም ህልሟ የብሔሮችን እኩልነት ማረጋገጥ ነው፡፡

እዚህ ላይ ሁለቱ ህልሞች እርስ በዕርሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸውን እንመለከታለን፡፡ ህልሞቹም ብቻ ሳይሆኑ ህልሞቹም ሊፈቱበት የተሄደበት መንገድ በተቃርኖ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ለአብነት ያህል ሁለቱን ስርዓቶች ደርግ እና ኢህአዴግን ብንመለከት እንኳን አሀዳዊ እና ፌደራላዊ ስርዓትን የተከተሉ በመሆናቸ የህልም አፈታታቸው ተቃርኖ አለበት፡፡

ዶ/ር መረራ ጉደና “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች- የኢህአዴግ ቆርጦ ቀጥል ፖለቲካ”በተሰኘ መፅሀፋቸው ይህ አይነቱ የህልም ፀብ በስርዓቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚው ጎራም ላይ የሚስተዋል መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በርግጥም ጆሀር እና ታማኝ አንድ ሰልፍ ላይ የሚይዙት ሰንደቃላማ መለያየትም የህልማችን ኩሪፊያ ማሳያ ነው፡፡

እነዚህ የፖለቲካ አስተሳሰብ ኩርፊዎች centrifuglim እና Centripetalism በሚሉ ሁለት የፖለቲካ ምሁራን ቃላት የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ የህልማችን ማቀፊያዎችም እንደ ሀገር እነዚህ ቃላት ናቸው ፡፡አንደኛው ወገን አንዲት ኢትዮጵ እንጅ ብሄር የለኝም የሚል ክርክር ሲያነሳ ሌላኛው ብሄር ከሌለ ኢትዮዮጵ አትኖርም ሲል ይሞግታል ፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለመጓዝ የተሰናት በየጊዜው የሚመጡ መንግስታት አንዱን ጥለው አንዱን ሰለሚያነሱ ነው ፡፡ የህልሞች ኩርፊያ ለሀገር አደጋ ከሆነ መፍትሄውም እነሱን ማስታረቅ ብቻ ነው ፡፡ ለእሱ ግን አሁንም አልታደልንም ፡፡ በህልሞቹ መሀል ያለውን ውኃልክ እያሰተካከለ ሀገር የሚገነባ ፖለቲከኛ ከወዴት አለ ? ከየትም ፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close