Connect with us

Art and Culture

የሻከረው የጥምቀትና የሎሚ ወዳጅነት

Published

on

የሻከረው የጥምቀትና የሎሚ ወዳጅነት

በኢትዮጵያ የሚከበሩ የተለያዩ ሃይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው የያዙት ተፈጥሯዊና ታሪካዊ እሴትና መስህብ የአገር ውስጥና የውጭ አገሮች ጎብኚዎችን ቀልብ ይስባሉ።

የጥምቀት በዓል ደግሞ ለዚህ አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው። በዓሉን የእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የሌላ እምነት ተከታዮችም በጉጉትና በናፍቆት የሚጠብቁትና የሚያከብሩት ነው።

የስነ መለኮት ምሁራን ‘’ጥምቀት’’ የሚለውን ቃል መነከር፣ መታጠብ ወይም መረጨት በሚል ይተረጉሙታል።

በጥምቀት ዋዜማ ከተራ ጥር 10 ቀን ከቀትር በኋላ በየአድባራቱ ያሉ ታቦታት በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ አልባሳት በለበሱ ምዕመናን ታጅበው ጉዟቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር (የታቦት ማደሪያ ስፍራ) ያደርጋሉ።

የታሪክ ድርሳናት ላይ እንደሰፈረው በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል መከበር የጀመረው በአጼ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት ነው።

ከ1486–1500 ዓ.ም የነገሱት አጼ ናኦድ ደግሞ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች በሙሉ ታቦተ ህጉ ወደ ባህረ ጥምቀቱ በሚሄድበትና ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ በማጀብ መሸኘት እንዳለባቸው በማወጃቸው ተግባራዊ መሆን መጀመሩ በተለያዩ የታሪክ መጽሃፍት ሰፍሮ እናገኛለን።

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው። በዓሉ የተለያዩ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላዊ ጭፈራቸውንና ትዕይንት የሚያሳዩበት ነው። የሌላ እምነት ተከታዮችም በትዕይንቱ ተማርከው በጋራ ደስታቸውን የሚካፈሉበት ነው።

የጥምቀት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ቀልብ እየሳበ በመምጣቱ መንግስት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባሕል ድርጅት (UNESCO) ጥበቃ ስር በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ። በነጻነትና በፍቅር ይጫወታሉ፤ይጨፍራሉ። ከዚህ ባለፈ በፍቅር መተጫጨት የሚፈልጉ ወጣቶች በቀላሉ ለመተያየት፣ ለመተዋወቅና ለመግባባት ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። ይህ ዓይነቱ መስተጋብር ታዲያ የበዓሉን ማህበራዊ ፋይዳ የበለጠ የጎላ እንዲሆን የሚያደርግ ነው።

’’ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁት’’ እንዳለችው አቀንቃኟ፤ የጥምቀት በዓል ሲመጣ ሎሚን የማያስታውስ ወይም በሎሚ ትዝታ የማይኖረው ምናልባትም ያሁኑ ትውልድ ብቻ ሊሆን ይችላል።

ሎሚና ጥምቀት ከጥንት ጀምሮ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው። በተለይ በገጠሩ የአገሪቷ አካባቢዎች ኮበሌው ልቡ የፈለጋት ኮረዳ ላይ ሎሚ በመወርወር መተጫጨቱና አብሮ መጨዋወቱ የተለመደ ባህል ነው። ጥምቀት ሲመጣ ሎሚ በሰዎች ልቦና ውስጥ የማይረሳ ቦታ አለው። ምናልባትም እርስዎ ወይም የቅርብ ወዳጆ በዚሁ በጥምቀት በዓል ሎሚ ተወርውሮባችሁ ይሆናል ከትዳር አጋርዎ ጋር የተገናኙት።

አሁን አሁን ሎሚና ጥምቀት የነበራቸው ጥብቅ ወዳጅነት በተለያዩ ምክንያቶች እየሻከረ መምጣቱን መታዘብ ይቻላል። እንዴት?

’’በድሮ በሬ ያረሰ ማን አለ፤ ሁሉም አዲስ ነው አድሮ እየዋለ’’ እንዳሉት አበው አሁን አሁን ዕድሜ ለቴክኖሎጂ በጥምቀት በዓል ልቡ ያረፈባትን ኮረዳ ለማማለል ሎሚ መወርወር ያለፈ ፋሽን ከሆነ ሰነባብቷል።

በተለይ ከተሞች አካባቢ ያሉ ወጣቶች በዕለቱ ሎሚ ከመወርወር ይልቅ በማህበራዊ ድረ-ገፆች የተዋወቁትን ሰው በአካል አግኝቶ የበለጠ ለመተዋወቅ በዓሉ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮላቸዋል። ታዲያ በዚህ ቀን ልቡ የከጀላትን ወጣት በአካል አግኝቶ ሻይ ቡና መባባሉ አብሮ መጨፈሩና ብሎም ለፍቅር መጠያየቁ ቀላል ሆኗል።

ከዚህ ባለፈ በበዓሉ ዕለት ልቡ የደነገጠላትን ወይም ልቧ የደነገጠለትን ወጣት ሎሚ ሳይወረውሩ ጠጋ ብሎ ስልክ ቁጥር መቀበል ወይም በጨዋታ በጨዋታ መግባባትና መተዋወቅም ዘመን አመጣሹ የጥምቀት በዓል ገጸ በረከት ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል።

ሎሚ ከመልካም ሽታው ባለፈ ለተለያዩ የጤና እክሎች ፈውስ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ለባክቴሪያ፣ ለካንሰር፣ ለጉበት፣ ለመገጣጠሚያ አካላት፣ ለኮልስትሮል፣ ቆዳ ላይ የሚወጡ ጥቋቁር ነጠብጣቦች ለማጥፋትና ለቆዳ ውበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይጠቀሳል።

ይህ ታድያ ሎሚ ለጤና ከሚሰጣቸው ጥቅሞች መካከል ጥቂቱ ነው። በጥምቀት ደግሞ በተለይም ድሮ ድሮ ሁለት ተፈላላጊ ልቦችን በማገናኘት ጥቅሙ በተለየ መልኩ ጎልቶ ይወጣ ነበር።

ለመሆኑ ሎሚና ጥምቀትን ሆድና ጀርባ ያደረጋቸው ማን ይሆን? ይህ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሎሚ ዋጋ የማይቀመስ እየሆነ መምጣቱ ግልጽ ነው። ይሁንና ሎሚ ዋጋውን የጨመረው ጥምቀትን ተገን አድርጎ አይደለም። ይህ ደግሞ ሎሚ ለበዓሉ የነበረውን ተፈላጊነት ማጣቱን ያሳያል።

ሎሚን ከጥምቀት ይልቅ ለተለያዩ የጤና እክሎች ብሎም ለዶሮ ማጠቢያ መጠቀም የተለመደ ሆኗል። በቅርቡ በተከበረው የገና በዓል እንኳን አንድ ሎሚ ከአምስት እስከ ሰባት ብር ሲገዛ እንደነበር ማስታወስ በቂ ነው።

ሎሚና ጥምቀት የነበራቸው ወዳጅነት ‘’በነበር’’ የቀረ እየሆነ መጥቷል። ወዳጅነታቸውን ያሻከረው ግን ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ ወይስ የዋጋ ንረት መልሱን በያላችሁበት ተወያዩበት።

ምንጭ: ትንሣኤ ገመቹ /ኢዜአ/

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close