Connect with us

Ethiopia

ኢሳያስ አፈወርቂ የኢትዮጵያ ወዳጅ ወይስ ስጋትና ጠላት?

Helen

Published

on

ስጋትና ጠላት

የትኛውም አገር ይነስም ይብዛም፣ ስጋትና ጠላት አለው፡፡ጠላቱ ርዕዮተ ዓለም አለያም፣ሀገር/ሀገራት፣ቡድኖች ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡መንግሥትም ያንን ጠላት በምን መልኩ ሕዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ተንትኖ ያቀርባል፡፡ከዚያም ግለሰብም ይሁን ቡድኖች ያንን ጠላት የጋራ ጠላት አድርገው ይይዛሉ፡፡አገሪቱን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጋር ቅራኔ ቢኖራቸውም እንኳ በዚህ ውጫዊ ጠላታቸው ላይ የጋራ ሥምምነት አላቸው፡፡

 

የጋራ ጠላትም የጋራ ወዳጅም የሌላቸው የተቃውሞ ፖለቲከኞች | ጥግነህ ዓይተነው ከአቧሬ

የትኛውም አገር ይነስም ይብዛም፣ ይጠርም ይወፍርም ጠላት አለው፡፡ጠላቱ ርዕዮተ ዓለም አለያም፣ሀገር/ሀገራት፣ቡድኖች ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡መንግሥትም ያንን ጠላት በምን መልኩ ሕዝብ ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ተንትኖ ያቀርባል፡፡ከዚያም ግለሰብም ይሁን ቡድኖች ያንን ጠላት የጋራ ጠላት አድርገው ይይዛሉ፡፡አገሪቱን ከሚያስተዳድረው መንግሥት ጋር ቅራኔ ቢኖራቸውም እንኳ በዚህ ውጫዊ ጠላታቸው ላይ የጋራ ሥምምነት አላቸው፡፡

ለምሳሌ እያንዳንዱ ሩሲያዊ ሁሉንም አሜሪካዊ በጥርጣሬ ያያል፡፡ ከሶቭየት ሕብረት ዘመን አንስቶም ሆነ ከዚያ በፊት የአሜሪካ መንግሥታትና የሩሲያ መሪዎች ተስማምተው አያውቁም፡፡ኢራናዊያን የሚያምኑት የአረብ ፖለቲከኛ የለም፡፡ሁሉም የአረብ መንግሥታት ኢራንን ይጸየፋሉ፡፡ሕዝቡም እንደዚያው፡፡

ግብጾች በውስጥ ፖለቲካቸው የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ሁሉም ግብጻዊ ግን በኢትዮጵያ እና በአባይ ወንዝ ላይ ያለው አመለካከት ወጥና ተመሳሳይ ነው፡፡ከፈረዖን እስከ አልሲሲ ያለው መንግሥትም በዚህ ጉዳይ የተቀየረ ሀሳብ አቅርቦ አያውቅም፡፡ቋሚ ጠላት አድርጎ ያያል፡፡

ኢትዮጵያዊያንስ?

በዕውነቱ ኢትዮጵያዊያን የምናሳዝን ፍጡሮች ነን፡፡የጋራ የምንላቸውን ጀግኖች ‹‹የእኛና የእነሱ›› ብለን መከፋፈላችን ሳያንስ፣የጋራ ጠላቶቻችንን እንኳ እንደጠላት መቁጠር አልቻልንም፡፡ይህንን እንድል ያነሳሳኝ ባሳለፍነው ዕሁድ የኤርትራው ፕሬዚዳንት የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የፈነደቁ ኢትዮጵያዊያንን ስመለከት ነው፡፡አቶ ኢሳያስ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፍሴ ነው፤ከልቤ እወደዋለሁ፤ ወያኔ አጣላኝ እንጂ›› የሚል ይዘት ያለው ንግግር መናገራቸው ሳያንስ፣ ‹‹ከኢሕአዴግ በላይ ለኢትዮጵያ የማስብ ሰው ነኝ፤ስለኢትዮጵያ የሚጨነቅ ፕሬዚዳንት እንደኔ የለም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

በዚህ ንግግር ነው እንግዲህ የኢሕአዴግ መንግሥት ተቃዋሚዎች ከአስመራ በሚነሳ ማዕበል አራት ኪሎ እንደሚናወጥ ታይቷቸው፤ሳምሶናይታቸውንም ይዘው ከዋሽንግተን እና ከሚኒሶታ ለመምጣት የቋመጡት፡፡

እንግዲህ አቶ ኢሳያስ ማለት ኢትዮጵያዊያንን አድጊ (አሕያ) በማለት ከኤርትራ ምድር ጠራርገው ያስወጡ፣የጥርስና የጣት ወርቅ ሳይቀር አስነቅለውና አስወልቀው ሕዝብ ያባረሩ፣ሕጻናትን ከነደብተራቸው ያቃጠሉ ሰው ናቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ኢትዮጵያዊያን ተከፋፍለዋል፤አቅም የሌላቸው ፈሪዎች ናቸው›› በሚል የኢትዮጵያን ድንበር በኃይል ወርረው ብዙ ሺህ ኢትዮጵያዊያን የገደሉ ናቸው፡፡ እኒህ ሰው ላለፉት 57 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲወጋና ሲያስወጋ የኖረን ቡድን የሚመሩ ናቸው፡፡በኢትዮጵያ እስላማዊ ጦርነት ያወጀውን አልሸባብን በስንቅም፣በትጥቅም፣በሞራልም በርታ ሲሉ የኖሩ ናቸው፡፡ከግብጽና ካታር ሚሊዮን ዶላር እየተቀበሉ ሲወጉና ሲያፍኑ ነበር፡፡አሁንም ሕዳሴ ግድብን ሳይቀር ለመደብደብ እንደሚያሴሩ ማንም ሳይሆን አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና መንግሥታት የመሰከሩት ጉዳይ ነው፡፡

ታዲያ ከኢሕአዴግም መፈጠር በፊት ጀምረው (ባለፉት ሶስት መንግሥታት) የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲያደሙ የኖሩ እኒህ ሰው በምን ሒሳብ ነው የኢሕአዴግ ጠላት ብቻ የሚሆኑት? እርግጥ ነው ከኢሕአዴግ ሰዎች ጋር መናናቅ ያመጣው ጸብ አላቸው፡፡ከኢሕአዴግ ጋር ያላቸው ጸብ ግን ገና 20 ዓመቱ ነው፡፡እርሳቸው በይፋ የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው የተሰለፉት ግን ገና ከ57 ዓመታት በፊት አንስቶ ነው፡፡በ1960ዎቹ መጨረሻም ሶማሊያ ስትወረን እኒሁ ሰው የሳሕል ተዋጊዎቻቸውን ልከው ከዚያድ ባሬ ጎን ቆመዋል፡፡ታዲያ እኒህን ሰውዬና ድርጅታቸውን እንደ ብሔራዊ የጋራ ጠላት መቁጠር ለምን አቃተን?

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች ጠላት አድርጎ መቁጠር የሚቸግራቸው ሌላው ቡድን አልሸባብ ነው፡፡ይህ ስብስብ የክርስቲያን ሀገር በሚላት ኢትዮጵያ ላይ ምንም ሳትነካው እስላማዊ ጂሃድ አወጀ፡፡መንግሥትም የአገር ጠላት ነው በሚል ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ወሰነ፡፡ላለፉት አስር ዓመታትም ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከእስላማዊ የሽብር ቡድን ለመጠበቅ ተዋደቁ፡፡የተቃውሞ ኃይሎቹ በአንጻሩ ‹‹ወያኔን ለመጣል ከአልሸባብም ጋር ቢሆን እንሰራለን›› ብለውን አረፉት፡፡የኢትዮጵያን ሶማሊያ መግባትም አወገዙት፡፡እነ አሜሪካ ስንት ሺህ ማይል ተጉዘው የመጡት ችግሩ ስላሰጋቸው አይደለም ወይ? ሌሴቶ ጦር የላከችው ከጅግጅጋና ድሬዳዋ የበለጠ ለአልሸባብ ቅርብ ሆና ነው ወይ? ቢያንስ ነፍሰጡርን በአንቡላንሷ ውስጥ የሚገድልን የሽብር ቡድን እንኳ የጋራ ጠላት አድርገን መፈረጅ እንዴት ያቅተናል?

ግብጽ ለብዙ ምዕተዓመታት የኢትዮጵያ ነገሥታትን ለማዳከም ዘመኑ የሚፈቅደውን ጨዋታ ሁሉ ስታደርግ የኖረች ሃገር ናት፡፡ኢትዮጵያ በውጭ ኃይል በተወረረችባቸው ሁሉም ጦርነቶች ጀርባም አለች፡፡ይህንን የምታደርገው ታሪካዊ ጠላቷን ለማጎሳቆልና የአባይ ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ነው፡፡ይቺ ሃገር ‹ኤርትራ መጥታ ጦር አሰፈረች› ሲባል፣‹‹ወያኔ አለቀለት፤ አልሲሲ ጀግና›› እያሉ መዘመር ምን የሚሉት ኋላቀርነት ነው?

በበኩሌ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ያልተሳካበት አንዱ ምክንያት ቢያንስ ሕዝቡ በታሪኩም ይሁን በገጠመኙ ጠላት ያደረጋቸውን አካላት ተቀብሎ ያለማስተናገዱ ይመስለኛል፡፡

ለምሳሌ የኢሳያስ አገዛዝ በተሳሳተ የፖለቲካ ሒሳብ ኢትዮጵያን ሲወርር ያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሆ ብሎ የተነሳው ጠላት መሆኑን ስላወቀ ነው፡፡ታዲያ ወንድምና እህቱን በባድመና በሽራሮ፣በፆረና እና በቡሬ…የገበረ ሕዝብ፣ ኢሳያስ ለኢትዮጵያ የምጨነቅ መሪ ነኝ ቢለው የሚሰማው ነገር እየታወቀ የኢሕአዴግ መንግሥት ተቃዋሚዎች ‹‹ጀግናው ኢሳያስ ሆይ ስለኛ የምታስብ ፕሬዚዳንት…›› ማለታቸው ምን ሚሉት ፖለቲከኛነት ይሆን?

ሞቅ ሲል ‹‹ለኢትዮጵያ የመቶ ዓመት የቤትሥራ ሰጥተናታል››፤ሲቀዘቅዝ፣ ‹‹አንቀጽ 39 እንዳይካተት ታግለን ሕወሓት እምቢ አለ›› የሚል መሪ እንዴት ነው የአገርና የሕዝብ ጠላት የማይሆነው? ‹‹ለኢትዮጵያ ሥኬት ስል እንቅልፍ የለኝም›› ሲልስ እንደወረደ የምንቀበለው የትኛው የስሜት ሕዋሳችን ቢጎድልብን ነው?

ከአምስት በላይ የመገንጠል ዕቅድ ያላቸውን የፖለቲካ ቡድኖች እያሰለጠነ ያለ ሰው ስለኢትዮጵያ አንድነት ስል ዋጋ ከፍያለሁ ቢል እንዴት ታምኖ ነው የጋራ ጠላት መሆን የሚያቅተው?

ኢሕአዴግን አንድ ሚሊዮን ጊዜ እንጥላው፣መሪዎቹም አስር ሺህ ጊዜ ቅፍፍ ይበሉን፣መንግሥትም እንደ አባ ጨጓሬ ይኮስኩሱን፣…ቢያንስ ግን ሻዕቢያን፣አልሸባብንና ግብጽን የአገር ጠላትና ሥጋት አድርጎ የማያስብ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ምን የሚሉት ኋላቀርነት ይሆን ?

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close