Connect with us

Art and Culture

ስህተቱ የማን ይሆን?

Published

on

ስህተቱ የማን ይሆን?

ስህተቱ የማን ይሆን? | በያሬድ ነጋሽ በድሬቲዩብ

ከትክክለኛው መንገድ ወጥተን ፤ ቢሆንልን ከምንለው ፣ቢሳካልን ከምንመኘው እና የኛ ቢሆን ከምንወደው ጉዳይ እርቀን ልክ ባልሆነው ፤ ከማንመርጠው ፤ከማንመኘው ፤ከማንፈልገው ስፍራ ስለመዋላችን ጥፋቱ የማን ይሆን?

ሌሎች ስራ ውለው ሲገቡ ፣ በጤንነት ሲመላለሱ ፣ በለስ ሲቀናቸው እና ኑሮ ከአመት አመት አሸወይና ሲሆንላቸው … እኛ ስራ ፈት ለመሆናችን ፣ ከአልጋ ለመዋላችን ፣ ዙሪያው ገደል ሲሆንብን እና ሞትን በሚያስመኝ ኑሮ ውስጥ ለመክረማችን ስእተቱ የማን ይሆን ?
አንገት ያስደፋን ወቅት አልፎ ለሚመጣው የጤንነት ፣ ሰላምና የደስታ አመትስ ምክንያቱ ምንድን ይሆን ?

ከትውልድ እስከ እድገት ሌሎች ሊያዩት የታደሉትን እንዳያይ ሆኖ አይን ሳይኖረው ከአፍንጫ መልስ ግንባር ሆኖ ስለተፈጠረ ልጅ በመጽሀፍ መሰል ጥያቄ ተጠይቋል (ዮወ ምዕራፍ ፱ ) :-

ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበት አመታት ቸርነትና ፈውስን እንዳደረገላቸው እንደአንደኛው ሆኖ ብርሀንን ዳግም እንዲታደል ይሄም አይን የሌው ሰው ከክርስቶስ ጎን ቆሟል ። በወቅቱ ሁሉን ጥለው ክርስቶስን ይከተሉት የነበሩት ሀዋርያት “ይህ ሰው አይን ሳይኖረው ግንባር ብቻ ሆኖ ለመፈጠሩ የእሱ ወይንስ የቤተሰቦቹ ሀጥያት ነው? ” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል ፡፡

ክርስቶስም በምለሹ “የማንም በደልና ሀጥያት ሳይሆን ይልቁን ይህ ሰው በዛች ቅፅበት ግንባር ብቻ በሆነ ፊቱ ላይ ከአፈር አይን አበጅቶ እንደመሰሎቹ ዳግም ብርሀንን ሲያድለው ለሚመለከቱ ሰዎች ሁሉ የፈጣሪ ክብር እንዲገለጥ ነው ” የሚል ምላሽ ሰጥቷቸዋል ፡፡

እንዲህ ነው እንግዴ … በስራ ፣ጤና ፣ሰላም እና ደስታ አጥተህ በር ዘግተህ ለመቀመጥህ በማንም ስህተት ሳቢያ አይደለም ፤
ያሰብነው ፣ያለምነው እና የምንሻው ቀን ሳይመጣ ሁሉ ነገር ያበቃ መስሎ ሲሰማን ይሄም በማንም በደል አማካኝነት አይደለም ፤
በተለያየ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተን ፣ከሰው በታች ሆነን የሚረዳንና የሚደርስልን ያጣን መስለን ስንታይ ይሄም የማናችንም ሀጥያት ውጤት አይደለም ፤ ይልቁን አዲስ ቀን ይመጣና ከሰው በታች አድርጎ የሚረዳን የሌለ ፤የሚደርስልን ያጣን ካስመሰለን ቀን ስንወጣ ለሚመለከቱንና ቀን ጎድሎባቸው የሚረዳቸውና የሚደርስላቸው የሌለ ለመሰላቸው ሰዎች ለሁሉ ቀን እንዳለው ምስክር አድርጎ ሲሾምን ነው እንጂ ።

በደዌ ዳኛ ተይዘን 20 አመት የተኛንበትን አልጋ ተሸክመን በሌላኛው ቀን በጤንነት ስንመላለስ “ታሞ የተነሳ ፈጣሪን እረሳ” የሚለው ተረት እንዲተረትብን አይደለም ፤ ይልቁን ይህንን ያክል ብር ከሌላችሁ እና እዚህኛው ሀገር ካልሄዳችሁ መዳን አትችሉም በሚል የደህንነት በሩ ለተዘጋባቸው ድዌያን የተስፋ ሻማ ለኳሽ አደርጎ ሲሾምህ ነው እንጂ፡፡

እንዴት ይወጣል ከተባለለት የሱስ አረንቋ ውስጥ ስትወጣ መውጣት ያልቻሉት ላይ “እስካሁን እዛው” እያልክ እንድትዘብትባቸው አይደለም ፤ ይልቁን “ሱሰኛ ያርፋል እንጂ ሱሱን አያቆምም” የሚለውን ብሂል ዘልፈህ ለተቀረው አርአያ እንድትሆናቸው እንጂ፡፡

የልጅነት በባዶ እግር ጉዞን ፣ጦም ውሎ አዳርን ፣ ለመፍረስ አንድ ሀሙስ በቀረው ቤት ውስጥ መኖርን ካስገደደህ እና እንደሌሎች እጅህን ፈታ አድርገህ መኖር እንዳትችል ከለጎመህ ድህነት ውስጥ ወጥተህ በሀብት ፣ በስኬትና በዝና ስትናኝ የቀድሞ አንተን መሳዮችን ጨርቃም ብለህ እንድትሳደብ አይደለም ፤ ይልቁን የሰቀቀን ቀናትን ለሚገፉ ፣ያሰቡት ሳይደርስ ተስፋ ለቆረጡ እና ከህይወት ለሞት ለቀረቡ ብዙሀን የአዲስ ቀን መባቻ ሰንደቅ አድርጎ ሲያቆምህ ነው እንጂ፡፡

ጎዶሎው ቀን አልፎ የሞላ እለት ቀን ለጎደለባቸው ሰዎች መልእክተኛ ሆነህ ሳታገለግል ተልኮህን እንድትረሳ ሊያደርጉህ የሚችሉ ሁለት መሰረታዊ ምክንያቶች አሉ ፦

1,አላልፍ ብሎህ አንገት ባስደፋህ ወራት በመርዳት ፋንታ በንቀት ፣ በስድና እና በሌላም ነገር ከችግርህ ብሰው ችግር የሆኑብህ አካላት ያ ቀን ያለፈ እለት በፍፁም ጥላቻ ከመስመር ሊያስወጡህ ይችላሉና ታገስ ።

2, አዳፋህ በበዛ ጊዜ ጓደኝነታቸውን ፣የሰፈር ልጅነታቸውን ፣እህትና ወንድምነታቸውን የነፈጉህ ሁላ ያ ቀን ተለውጦ በስመጥርነትህ ሲተካ የአንተ ሊሆኑ ሊሽቀዳደሙና ከሰው ሁሉ የተለየህ እንደሆንክ ሊነግሩህ ይችላሉና ከዚህም ተጠንቀቅ።

በጠቅላላው በችግር ለመውደቅህ ምክንያቱ የማንም ስህተት አይደለም ፤ ይልቁን ሁሉም በጊዜው አልፎ አዲስ ቀን ሲመጣ በቀድሞ አንተነትህ ላይ ለሚገኙ ሰዎች የተሰፋ መልዕክተኛ በመሆን የፈጣሪ ክብር እንዱገለጥብህ መርጦህ ነው ፡፡
ሰላም! yarednegash756@gmail.com

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close