Connect with us

Africa

ግብጽና ኤርትራ፣ ኢትዮጵያን ሊከብቡ ወይስ ሊያዋክቡ

Published

on

ግብጽና ኤርትራ፣ኢትዮጵያን ሊከብቡ ወይስ ሊያዋክቡ

ግብጽና ኤርትራ፣ኢትዮጵያን ሊከብቡ ወይስ ሊያዋክቡ | አስመረት ከአራት ኪሎ

ያሳለፍናቸው ሳምንታት የአፍሪካ ቀንድን ወታደራዊ ፖለቲካ ያጦዙ ክስተቶች የተሰተናገዱባቸው ናቸው፡፡ የግብጽ ጦር ኤርትራ ሰፈረ፤ሱዳን ከኤርትራ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ዘጋች፤ኢሳያስአፈወርቂ ግብጽ ሄዱ፤ሱዳን ጦሯን ወደ ኤርትራ ድንበር አስጠጋች፤የሱዳኑ ጄኔራል አዲስ አበባ መጥተው ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ተወያዩ፤ሱዳን በምሥራቁ ክፍሏ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች…ይህ ሁሉ ሰሞነኛው የቀንዱ ዜና ነው፡፡

ከዜናው ባሻገር ያለው ጉዳይ ነው ቀልብ የሚስበውና የሚያሳስበው፡፡ግብጽ ወደ አፍሪካ ቀንድ ለመምጣት ስታመነታና ስታቅድ የኖረችው አሁን አይደለም፡፡ይህ የቆየና ነባር ፍላጎቷ ነው፡፡ይህ ፍላጎቷ አንዳንዴ በውስጥ ፖለቲካዋ አለመረጋጋት፣ሌላ ጊዜ በዲፕሎማሲያዊ ‹መግባባት›፣ አልፎአልፎ ደግሞ በቀጣናው ሁነኛ ወዳጅ በማጣት ሳይፈጸም የቀረ ሆኖ ኖሯል፡፡

አሁን ግን ግብጽ ኤርትራ ለመምጣት ሰበብ አግኝታለች፡፡ሰበቧ ሱዳን ነች፡፡የአልበሽር መንግሥት ከቱርክ ጋር ጀምሮታል የተባለው ጠንካራ ሽርክና አሳስቦኛል በሚል በኤርትራ ሳዋ የሚሰፍር ጦር ልካለች፡፡የጦሩ ዓላማ በሱዳን በኩል ከቱርክ የሚሰነዘርን ጥቃት ለመከላከል ነው የሚል የዳቦ ስም ተሰጥቶታል፡፡የቤት ስሙ ግን ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሰንዝር፤ሕዳሴ ግድብንም አውድም የሚል ላለመሆኑ ዋስትና የለም፡፡

ቱርክና ግብጽ፣ ሱዳንና የሕዳሴ ግድብ
የግብጹ ፕሬዚዳንት ወደ ሥልጣን የመጡት ከወታደሩ ሰፈር ነው፡፡ፊልድ ማርሻልነታቸውን ውልቅ አድርገው ቶክሲዶ የለበሱት የተመረጠ መንግሥት ፈንቅለው ነው፡፡ በ2014 (እ.ኤ.አ) የፈነቀሉት የሙስሊም ብራዘርስ ሁዱ የሙሃመድ መርሲ መንግሥት ደግሞ በቱርክ ይደገፍ ነበር፡፡ እናም የምደግፈውን መንግሥት ፈንቅለሃል በሚል በአልሲሲ መንግሥት ላይ ቱርክ ቂም ቋጥራለች፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ነው እንግዲህ ቱርክና የግብጽ ጎረቤት የሆነችው ሱዳን ተወዳጅተው የደሴት ሥጦታ እስከመቀባበል የደረሱት፡፡

ሱዳን ሱአኪን የተባለች ደሴት በመስጠት ቱርክ በቀይ ባሕር ላይ ድርሻ እንዲኖራት አድርጋለች፡፡ይህ የጣይብ ኤርዶሃን መንግሥት ሊወረኝ/ሊፈነቅለኝ ነው ለሚለው የግብጽ አገዛዝ ጥሩ ማስጃ ሆኖለታል፡፡ ኤርትራ የሰፈረው ጦርም ይህንን የሚጠብቅና የሚከላከል ነው ተባለ፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ጉዳይ በሚገባ የታዘቡ ተንታኞች እንደሚሉት ይህ ጦር ሁለት ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡
አንደኛ፤ ዋነኛና ቀዳሚ ሥራው የአልበሽርን መንግሥት መፈንቀል ነው፡፡ለዚያም ነው ጦሩ ከግብጽ እንደመጣ በቀጥታ ሳዋ ያረፈውና ከሱዳን ተቃዋሚዎች ጋር የተገናኘው፡፡ ሳዋ ማለት የኤርትራ መንግሥት ለብሔራዊ ውትድርና ማሰልጠኛ የሚጠቀምበት በጋሽ ባርካ ክልል ውስጥ የሚገኝ የጦር መደብ ነው፡፡ይህ የጦር ሰፈር በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል ኤርትራን ያዋስናል፡፡የግብጽ ጀኔራሎች የዳርፉር አማጽያንን ሳዋ ላይ ሰብስበው ሲያወያዩ የታዩትም በዚህ ቅርብ በሆነ አቅጣጫ ገብተው አልበሽር አስተዳደር ላይ ጥቃት እንዲሰነዝሩና ባስ ሲልም እንዲፈነቅሉ ነው፡፡

ግብጽ ይህንን በአራት ምክንያት አታደርገውም ተብሎ አይጠበቅም፡፡አንደኛ የሃላየብ ክልል ዛሬም ግብጽንና ሱዳንን እያነታረከች ያለች ነዳጃማ ቀጣና ናት፡፡ድንበሯን ሁሉቱም ትገባናለች ባይ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ሱዳን ሙስሊም ብራዘርስ ሁድን ትደግፋለች የሚል ክስ ከግብጽ ይቀርብባታል፡፡ሶስተኛ ሱዳን ከቱርክ ጋር የፈጠረችው ወዳጅነት ለግብጽ አስደንጋጭ ነው፡፡አራተኛ ሱዳን በሕዳሴው ግድብ ላይ የያዘችው አቋም ግብጽን መጎርበጥ ከጀመረ ቆይቷል፡፡ሞልተው ገፍተው ሱዳን ከሶስትዮሽ ድርድሩ ትውጣ፤ሁለታችን ብቻ እንወያይ ሲሉ ኢትዮጵያን ማባበል መጀመራቸውም ለዚያ ነው፤ምንም እንኳ በአዲስ አበባው መንግሥት ውድቅ ቢደረግባቸውም፡፡

ሁለተኛ፤ ኤርትራ የገባው የግብጽ ጦር ሁለተኛው ተልዕኮ፣በአባይ ውሃ ምክንያት ለዘመናት አጀንዳው ካደረጋት ኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ከ60 በመቶ በላይ የተገባደደው የሕዳሴው ግድብ ለግብጽ የሚሊኒየሙ አስደንጋጭ ፕሮጀክት ነው፡፡ በሳዋ የሰፈረው የግብጽ ጦርም በዚህ ፕሮጀክት ምክንያት የሚነካ ጥቅም ካለ እርምጃ የሚወስድ ተጠባባቂ ኃይል ላለመሆኑ ዋስትና የለም፡፡ኢሳያስ አፈወርቂም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ይህንን ተቀብለውታል፡፡(በነገራችን ላይ አል ሲሲ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከ2014 ወዲህ ብቻ ኢሳያስ አምስት ጊዜ ወደ ካይሮ ተመላልሰዋል፡፡መቼም ሲገናኙ ስለ አፍሪካ ቀንድ የአየር ንብረት ለውጥ እንደማይመካከሩ እሙን ነው)
ሥለዚህ በሁለቱም ተልዕኮዎች ኢትዮጵያ ተጎጂ ነች ማለት ነው፡ግብፆች እንዳቀዱት የአልበሽርን መንግሥት ከፈነቀሉት ኢትዮጵያ ላይ ሁለት ጉዳቶች አሉት፡፡በአንድ በኩል በሱዳን ውስጥ በቀጥታ በግብጽ የሚታዘዝ ኃይል ሥልጣን ይይዛል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ የሕዳሴውን ግድብ መገንባት አጥብቆ የሚደግፈውን የኡመር ሐሰን አልበሽርን መንግሥት ታጣዋለች፡፡

የመጀመሪያ ተልዕኮውን ቢያሳካ እንኳ ጦሩ ለሁለተኛው ግዳጅ ራሱን እያዘጋጀ ይቆያል እንጂ ሊወጣ አይችልም፡፡በአጭር አገላለጽ ኤርትራ የገባው ጦር የመውጫ ቀነ-ገደብ (Exit strategy) ያላስቀመጠ ነው፡፡ ቆይታው የሚወሰነውም ከኤርትራ መንግሥት ጋር በሚኖረው ‹ፍቅር› ላይ ይሆናል፡፡አቶ ኢሳያስ ነገ ጠዋት የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝላቸው አሰላለፍ ካጋጠማቸው ግብጽን ጠራርገው የማያስወጡበት ምክንያት የለም፡፡(አቶ ኢሳያስ እንዲህ ያለ አጋጣሚ ተከል አመል ያላቸው ሰው መሆናቸውን የኢሳያስ የኮንዶም ፖለቲካ በሚል ርዕስ የተጻፈውን ጽሁፍ ይመልከቱ)፡፡እናም ግራም ነፈሰ ቀኝ የግብጽ ጦር ሳዋ የገባው ለሙዚቃ ልምምድ አለያም ለኮንሰርት አይደለም፡፡ጥቅሜን ለማስጠበቅ መንግሥታትን እፈነቅላለሁ፤በቅርብ ርቀት ላይ ቆሜ ግድብ እቆጣጠራለሁ ብሎ ነው!!

ከግብፅ መልስ ለኤርትራ ቴሌቭዥን ማብራሪያ የሰጡት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስለ ሰሞነኛው ጉዳይም አንስተዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ “የግብፅ ጦር ኤርትራ የገባው ቱርክ ሶማሊያንና ግብፅን ለመበጥበጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ለማድረግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡የ72 ዓመቱ አዛውንት ከኢትዮጵያ ጋር ለመሥራት ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍላጎት እንዳላቸው ጠቅሰው ፣ለሁለቱ አገራት አለመስማማት ጅቡቲን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ካወረደች፣የኔን ወደብ መጠቀም አቁማ ወደነ አሰብ ታማትራለች በሚል ስጋት ፀባችን እንዲቀጥል ትፈልጋለች ሲሉ በሳቅ የሚያፈርስ መከራከሪያ ይዘው ቀርበዋል፡፡  DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close