Connect with us

Business

ከኮንዶሚንየም ጀርባ ያደፈጡ ህገ-ወጥ ድርጊቶች

Published

on

ከኮንዶሚንየም ጀርባ ያደፈጡ ህገ-ወጥ ድርጊቶች

ከኮንዶሚንየም ጀርባ ያደፈጡ ህገ-ወጥ ድርጊቶች | አሳዬ ደርቤ በድሬ-ትዩብ

1. እጣ ውስጥ የማይካተቱ ቤቶች
በየካ-አባዶና በቦሌ-አራብሳ ሳይቶች ብትሄዱ ለባለእጣዎች ከሚተላለፉት ባለሶስት መኝታ-ቤቶች ይልቅ እጣ ውስጥ ያልተካተቱና ለተጠቃሚዎች ያልተላለፉት ይበዛሉ፡፡

አብዛኛው የከተማ ህዝብ በመኖሪያ ቤት እጦትና የኪራይ ዋጋ ውድነት እየተንገፈገፈ ባለበት ሰዓት እነዚህ ሸረሪት ሰፋፊ ቤቶች ለማንና ለምን እንደተቀመጡ ማጣራት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህም ‹ይመለከተናል› የሚሉ የህዝብ ሚዲያዎች ወደ ስፍራው ሄደው እነዚህን ባለቤት አልባ ቤቶች ቢመለከቱና ማጣራት ቢያደርጉ ከጀርባ የሆነ ህገ-ወጥ ተግባር ማግኘታቸው አይቀርም እላለሁ፡፡

2. አግሮ-ስቶን
ወትሮ ሲባል የምንሰማው ‹‹የእነ ቶሎ ቶሎ ቤት ግድግዳው ሰንበሌጥ›› ነበር፡፡ አሁን ላይ ይሄ አባባል ‹‹የእነ ቶሎቶሎ ቤት ግድግዳው አግሮ-ስቶን›› በሚል ተተክቷል፡፡

‹‹አግሮ-ስቶን›› ማለት መንግስት የሰራቸውን ኮንዶሚንዬሞች ለባለእጣዎች እስኪያስረክብ ድረስ የውስጥ ግድግዳ በመሆን የሚያገለግል የግንባታ-ማቴሪያል ነው፡፡ ችግሩ ግን በዚህ ማቴሪያል የሚሰራ ግድግዳ ቀለም የማይቀበልና የሚሰነጣጠቅ በመሆኑ በተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭና ተወዳጅ መሆን አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ የኮንዶሚንዬም ቤት የደረሳቸው ሰዎች ወደ ግንባታ ከመግባታቸው በፊት የመጀመሪያ ተግባራቸው የሚሆነው ይሄን አግሮ-ስቶን በማፍረስ በብሎኬት መተካት ነው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ በቤቶች ልማት የማይፈቀድ በመሆኑ…. አግሮስቶኑን ከማፍረስህ በፊት ለብሎኩ ጥበቃዎችና ተቆጣጣሪዎች እስከ አምስት ሽህ ብር የሚደርስ ገንዘብ ሸጎጥ ማድረግ ግደታ ነው፡፡ አለበለዚያ ቤትህን ያሽጉታል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የቤቶቹ ባለቤቶች በአግሮስቶን የተከፋፈለ ቤት ውስጥ ከመኖር ይልቅ የፈጀውን ያህል ወጭ አውጥተው በብሎኬት መቀየርን ይመርጣሉ፡፡

እናም ይሄንን የግንባታ ማቴሪያል ማፍረሱና በብሎኬት መተካቱ… ባለእጣዎችን ለከባድ ወጭ እየዳረገ ያለ ከመሆኑም በላይ አግሮ-ስቶኑ ከታሰበለት አገልግሎት ይልቅ የአካባቢ ብክለትን እያመጣ ቢሆንም… በመንግስት በኩል ግን የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ ቤቶቹ ለባለ-እጣዎች በተላለፉ ማግስት የዚህ ማቴሪያል እጣ-ፈንታ በየመንገዱና በየብሎኩ ዙሪያ ፈራርሶ መውደቅ ቢሆንም… መንግስት ለዚህ ጥቅም-አልባ ማቴሪያል በርካታ በጀት ማፍሰሱን ተያይዞታል፡፡

ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከተጠቃሚዎቹ ይልቅ ለአምራቾቹ ዘላቂ ጥቅም ከማሰብ የመጣ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ሃቁ ይሄ ከሆነ የአግሮ-ስቶን አምራቾቹ ጠቃሚ ላልሆነ ነገር ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን ከሚጨርሱ ይልቅ… መንግስት ለዚህ ማቴሪያል መግዣ የሚመድበውን በጀት ዝም ብሎ ቢሰጣቸው መልካም ይመስለኛል፡፡

3. የፊኒሽንግ ስራ
መንግስት ለዚህ የግንባታ ምዕራፍ ማከናወኛ በርካታ ሚሊዮን ብር ይመድብና ጨረታ አውጥቶ ለተቋራጮች ይሰጣል፡፡
ይሄ የሚሆነው ግን እጣ ለወጣላቸው ሰዎች ግድግዳና ጣሪያ ካስረከበ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም እነዚህ ሰዎች ከዛሬ ነገ የፊኒሽንግ ስራው ይሰራልና እያሉ ሲጠባበቁ ኤጀንሲውና ኮንትራክተሩ በሚያደርጉት የጀርባ ስምምነት የፊኒሽንግ ስራው ሳይጀመር ከአንድ ዓመት በላይ አንዲቆይ ይደረጋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ተስፋ የቆረጡ የኮንደሚንዬም ባለቤቶችም… በኪራይ ቤት መበዝበዝ ሲሰለቻቸው በመንግስት ሊሸፈን ለሚገባው የፊኒሽንግ ስራ… እስከ አምሳ ሺህ ብር በማውጣት በራሳቸው ገንዘብ ስራውን በማጠናቀቅ ወደቤታቸው ይገባሉ፡፡

በመጨረሻም ከ90 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑት ሰዎች በራሳቸው ገንዘብ ስራውን አጠናቀው ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ተሰውሮ የነበረው ኮንትራክተር በሲኖትራክ አሸዋውን ጭኖ ከተፍ ይላል፡፡ ከዚያም በተለያዩ ምክንያቶች ያልተጨረሱ ጥቂት ቤቶችን እንደ ነገሩ አጨማልቆ ከሰራ በኋላ ከሳይት ተቆጣጣሪዎች ጋር በመመሳጠር የሁሉንም ቤቶች የፊኒሽንግ ስራ ሰርቶ እንዳጠናቀቀ ተደርጎ ክፍያ እንዲፈጸምለት ይደረጋል፡፡ ይሄ ክፍያ በሚሊዮን ብር የሚቆጠር ሲሆን ተቋራጩ ያለምንም ልፋትና ወጭ ክፍያውን ላስፈጸሙለት ተቆጣጣሪዎችና ኃላፊዎች የሚጠበቅበትን ያህል ለግሶ የቀረውን በሳምሶናይቱ አጭቆ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡

4. ለተጠቃሚዎች የማይተላለፉ ብሎኮች
ይሄን የታዘብኩት በየካ-አባዶ ኮንዶሚንየም ሲሆን… ሳይቱ ለባለእጣዎች ከተላለፈ ከሁለት ዓመት በላይ ሁኖታል፡፡ ይሁንና ወደ ሳይቱ መግቢያ አካባቢ ባሉ ‹ግንባር ቦታዎች› ላይ በግራና በቀኝ ግንባታቸው ቀስ በቀስ እንዲከናወን የተፈረደባቸው በርካታ ብሎኮች ይታያሉ፡፡ እናም ከሌሎች ብሎኮች በተለየ የእነዚህን ህንጻዎች ግንባታ ለማጠናቀቅ ከሁለት ዓመታት በላይ ማስፈለጉ ጉዳዩ የማረሳሳት እንጂ የመጓተት አይመስልም፡፡

5. የኮንዶሚንየም የንግድ ቦታዎች
በሁሉም ሳይቶች በሚገኙ ብሎኮች ላይ ከስር ያሉት ቤቶች ለንግድ አገልግሎት በጨረታ የሚሸጡ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ቤቶቹ በካሬ ሜትር ከሃያ ሽህ ብር በላይ የሚሸጡ ሲሆን ለመንግስት የሚያስገቡት ገቢ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ ለህብረተሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ነው፡፡

ሆኖም ግን መንግስት እኒህን ሱቆቹን በጨረታ ለመሸጥ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ስለሚፈጅበት በሳይቱ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለከባድ እንግልትና ወጭ ሲዳረጉ ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ቦሌ-አራብሳን መውሰድ ይቻላል፡፡ እናም መንግስት እነዚህን ሱቆች ረስቷቸው ከሆነ ብናስታውሰው አይከፋም እላለሁ፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close