Connect with us

Art and Culture

‘‘አእምሮአችን አርነት ካልወጣ በቀር፥ በባርነት ውስጥ ነን’’

Published

on

‘‘አእምሮአችን አርነት ካልወጣ በቀር፥ በባርነት ውስጥ ነን’’

‘‘አእምሮአችን አርነት ካልወጣ በቀር፥ በባርነት ውስጥ ነን’’ | ኃይሌ ተስፋዬ በድሬቲዩብ
…………………………………
በጥንት ዘመን ባርነት አንድ የኀያልነት መገለጫ እንደነበር ይታወቃል። ይኸውም፥ ሰው በገንዘብ ሲገዛ፣ በጦርነት ጊዜ ሲማረክ፣ በባርነት ሲወለድ፣ በሌብነትና በራሱ ፈቃድ ባሪያ ሊሆን እንደሚችል ጥንታዊ መጽሐፍት ያስረዳሉ።

ይሁንና እኔ፥ በአርነትና በባርነት መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት እንዳለ አምናለሁ።በመሆኑም ዋጋ የምንከፍልለት ነገር ሁሉ በህሊናችን መዳፍ ስር ብቻ ይገኛል ባይ ነኝ። አንዳንዴ ግን ለነጻነት የሚሆን ሰፊ ቦታ፥ በልባችን ከሌለንና አርነት (ነጻነት) የሚባለውን በሚገባ ተረድተን ወደ ተግባር ካልገባን፣ የምንናፍቃትን የተስፋይቱን ምድር መውረስ አንችልም ብዬ አስባለሁ።

በአፋችንም ‘‘ለአርነት የቆምን ነን’’፥ ‘‘ለህዝባችን አርነት፣ ለኛም የህይወት ብልጥግና እንሰራለን’’ በማለት … የባርነት ጠላቶች እንደሆን በመፈክር ማሰማት ብቻ ወደ አርነት ፍጽሞ አይወስደንም። ይህም ማለት፥ ከባርነትና ከእጅ አዙር ባርነት ጋር ትግል ከማድረጋችን በፊት ለአርነት ያለን የተስተካከለ ቁመናና ለዚያ ነገር ያለን ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ማለት ነው።

ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን፥ለ430 አመት ያህል በግብጽ የባርነትን ገፈት የቀመሱት የእስራኤል ህዝቦች ታሪክ ነው።

የእስራኤል 12ቱ ነገዶች ወደ ግብጽ ለባርነት ሲወርዱ፥ ፈርኦን መጠቀም የፈለገው… አካላዊ የሆነውን ማንነታቸውን በባርነት መያዝ ብቻ ሳይሆን፥ በስነ ልቦና መሳሪያነት አስተሳሰባቸውን መቆጣጠር፣ ማሰርና ማቁሰል ነበር።

በቅድሚያ በባርነት የመያዙ ስኬት ከተሳካለት በኋላ …ከዚያ ግዞት ቢወጡና ቢያፈገፍጉ፥ የሚገጥማቸውን ክፉ ነገር በፊታቸው እየሳለ፣ በቅድሚያ አእምሮአቸውን ያላሽቀው ነበር።

ለምሳሌ፦ከእሱ መዳፍ በእምቢተኝነት ቢወጡ…ከፊታቸው፥ቀይ ባሕር እንዳለ…ቀይ ባሕርን ቢያልፉ…ሚዳማውያን የተባሉ ጠላቶቻቸው እንደሚጠብቋቸው፣ እነርሱንም ቢያልፉ ኢያሪኮ የሚባል ትልቁ ግንብ እንዳለ፣ ኢያሪኮን ቢያልፉ እንኳ ዮርዳኖስ እንደሚጠብቃቸው፣ ወደ ግራም ወደ ቀኝም ቢያፈገፍጉ፥ በትላልቅ ሰንሰለታማ ተራሮች እንደታጠሩ… ፊታቸው ላይ በመሳል ፣ ስነ ልቦናቸውን በከፍተኛ ሁኔታ ይሰልብ ነበር።ይህ የስነ ልቦና ጦርነት ነበር፥ እስራኤልን ለረጅም ዘመን ባርነትን እንደ አርነት ቆጥሮ እንዲቀመጥ ያደረገው።

ከዚህም የተነሳ ‘‘ከማናውቀው አርነት፥ የምናውቀው ባርነት ይሻለናል’’ ‘‘ጥቅም ከሌለው አርነት ፥ጥቅም ያለው ባርነት ይሻለናል’’ የሚል መፈክር በማንገብ በስንፍና ያንን ሁሉ ዘመን እንዲቀመጡ ያደረጋቸው።

ይህ ነው የጨቋኞችና የአምባገነኖች ዋና ግባቸው። አእምሮንና ባለ አእምሮን ለስርአታቸው ማስፈጸሚያ ባርያ ማድረግ።ይህ ፈርኦናዊ አካሄድ ነው። አንዱን ነገድ ከአንዱ እንደሚበልጥ፣ አልያም የኤፍሬም ነገድ፥ ከይሁዳ ነገድ ጋር ምንም አንድነትና ታሪክ እንደሌለው በማሳየት፥ ውስጥ ውስጡን በመቆስቆስ ወደ አርነት የሚደረገውን ግስጋሴ በመከፋፈል፣ ማኮላሸትና በር መዝጋት ነው ስራው።

ይህም ብሶት ፥ በግብጽ አስተዳደር ስርአትና መዋቅር ውስጥ እየኖረ፣ነገር ግን አእምሮው ከባርነት አስተሳሰብ ነጻ በወጣው ሰው፥ በታላቁ ሙሴ መልስ አግኝቷል።…ሙሴ ከግብጽ ሳይወጣ ፥እንዴት አድርጎ ሕዝቡን ከአባቶቹና ከእናቶቹ አገር ‘‘ከነአን’’ እንደሚያስገባ ያውቅ ነበር። ምክንያቱም በአእምሮው አርነት የወጣ ሰው ስለነበር ነው። ይሁንና ሙሴ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ሕዝብ ወደ አርነት እየመራ ቢወጣም ፣አእምሯቸው ነጻ ያልወጣ የአርነት ጉዞ መንገደኞች ተከስተው ነበር። እነዚህ ሰዎች በባርነት ሆኖ መኖርን የሚመርጡና የባርነትና የነጻነትን ልዩነት ጠንቅቀው የማያውቁ ሰዎች ነበሩ።

ስለሆነም የስጋ አምሮት ያነሆለላቸው፣ ከኋላ እየተገረፉ ሆዳቸው እንዲሞላ የሚፈልጉ፣ አእምሮአቸው ነጻ ያልወጣ ሰዎች እንደ ነበሩ መጽሐፍ ይተርክልናል። እንደውም…የግብጽን ነጭ ሽንኩርት፣ ጎመንና ድንች ናፍቀናል፤ ስለዚህ በሙሴ ላይ አለቃ ሾመን፥ ወደ ግብጽ መመለስ ይኖርብናል በማለት የአርነትን ዋጋ ከሆዳቸው ጋር የሚያወዳድሩ አካሎች ነበሩ። በመሆኑምይህም መከፋፈል የአርነት ጉዞ ተጓዦችን ወደ ሚፈልጓት የተስፋይቱ ምድር ለመድረስ ለሚደረገውን ሙከራ እንቅፋት ፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል።

ሁሌ በአርነት ጉዞ ውስጥ፥ ሙሴን በሚመስሉና እነዚህኞቹን ሰዎች በሚመስሉ ሰዎች መሞላቱ ግድ ነው።…በቅድሚያ አእምሮአቸው አርነት የወጣና፣ አእምሮአቸው አርነት ያልወጣ ሰዎች ማሳያና መገለጫ እንደሆኑ ግልጥ ነውና። ሲቀጥል አርነት ለመውጣት ማንም የሚመኘው ሰው ፍላጎት ቢሆንም ቅሉ ፥ያ ልምምድ ‘‘ኑሮ ካሉት መቃብርም ይሞቃል’’ ከሚባለው ከንቱ ሃሳብ የመነጨ፥ አሊያም አምባገነኖች ካሳደሩብን ታላቅ የኀሊና ቁስል የተነሳም ሊሆን ይችላል።
እዚህ ጋር ዶክተር ማይልስ ሙኑሮ ከጻፈው አንድ ምሳሌ ልጠቀም…

ዶክተሩ አንድን ነገር የመልመድን ኃይል ባስረዳበት ወቅት እንዲህ በማለት አስቀምጧል…‘‘አንድ የሳይንቲስት ቡድን፥ አንድ ውሻን በአንድ ችካል ላይ በሰንሰለት አሰሩት። በመቀጠልም ሊደርስበት በማይችልበት ቦታ ምግብ አስቀመጡለት። ውሻውም ወደ ምግቡ ለመድረስ ሲሞክር ማሰሪያው ስለሚወጥረው የሚሰማው ህመም አለ። ወደ ምግቡ ለመድረስ በሞከረ ቁጥር ሕመም ይሰማዋል።

በአራተኛው ሳምንት ላይ ይህ አሰቃቂ ሙከራ ሲታይ፥ ውሻው እንቅስቃሴ ማድረጉን ትቶ የታሰረበት ችካል አጠገብ መቀመጡ ታየ። በዚህ ጊዜ ምግቡን ለማግኘት የሚያደርገው ምንም አይነት ጥረት አልነበረም። በአምስተኛው ሳምንት ሰንሰለቱን ፈተውለት፥ ምግቡን ቀረብ አድርገው አስቀመጡት።

ነገር ግን አሁንም ውሻው የተቀመጠው ችካሉ አጠገብ ነበር። እንሰሳው ወደ ምግቡ ለመቅረብ አልፈለገም። ምንም እንኳን የተፈታ ቢሆንም፣ ምግብ ለማግኘት መጣሩ ከፈጠረበት ህመም የተነሳ፥ ምግቡን መብላት እንደማይችል አምኗል። ’’ በማለት አእምሮአችን ላይ የሚፈጠሩ ነገሮች፥ ከእስራታችን ነጻ እንዳንወጣ እንደሚከለክሉን ያሳየበት ምሳሌ ነበር።

ሁሉ ነገር ያለው ህሊናችን ውስጥ ነው።በርግጥ ካለፉብን ህመሞች የተነሳ ወደ አዲስ እመርታ ለመሄድ እንፈራ ይሆናል ነገር ግን እንደምንም ብለን ህሊናችንን ከተጠቀምንበት የማይከፈል ባሕር፣የማይናድ ተራራ፣ የማይገለበጥ እንቆቅልሽ የለም። ይሄንንም እሳቤ ለግል ህይወታችን፣ ለማኅበረሰብ ንቃትና ለሐገር ህዳሴ ብናውለው ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል። DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close