Connect with us

Africa

‹‹ብላቴናው›› ኃይለማርያም ደሳለኝ

Published

on

‹‹ብላቴናው›› ኃይለማርያም ደሳለኝ |

‹‹ብላቴናው›› ኃይለማርያም ደሳለኝ | አስመረት ከአራት ኪሎ

የምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች የቀለም ነገር እንደሚቸግራቸው ከዚህ በፊት በድሬቲዩብ ላይ “የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች የትምህርት ደረጃ” አንብበን ነበር፡፡ከአቶ ኡሁሩ ኬኒያታና ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሌላ የተማረ መሪ በቀጣናው እንደሌለም ጽሁፉ ተንትኗል፡፡ይህም በየአገራቱ ውስጥ ማኅበረ-ፖለቲካዊ ችግር እንደሚያደርስ ጠቆም አድርጓል፡፡ በዚያ ጽሁፍ ውስጥ እስከ ማስተርስ ከተማሩ (በእርሳቸው አገላለጽ ቀለሜ ተማሪ) ሁለት የአካባቢያችን መሪዎች መካከል አቶ ኃይለማርያም ከሁለቱ እንደ አንዱ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

አሁን ደግሞ ከአካባቢው አቻዎቻቸው ጋር ሲነጻጸሩ ሌላ ክብረወሰን የሚያሻሽልላቸው ሌላ እውነት ተገኝቷል፡፡ምን ? ዕድሜ!!
አዛውንት መሪዎች በበዙበት የምሥራቅ አፍሪካ ከባቢ ውስጥ አቶ ኃይለማርያም ብላቴና ናቸው፡፡ብላቴናነት አንጻራዊ ነው፡፡ አቶ ኃይለማርያምም ከነ ኢሳያስ፣ አልበሽር፣ ፋርማጆ፣ ጊሌህ፣ሳልቫኪር፣ ኡሁሩ ወዘተ አኳያ ሲታዩ ልጅ ናቸው፡፡እንዴት?

ከኢሳያስ እንጀምር ፤
የትንባሆ ነጋዴው አቶ አፈወርቂ አብርሃና የቤት እመቤቷ ወይዘሮ አዳነች በርሄ ኢሳያስ የተባለውን ልጃቸውን ከአስመራ ወጣ ብላ በምትገኘው አባ ሻውል መንደር የወለዱት ጥር 25 በ1938 ዓመተ ምኅረት ነበር፡፡25 ዓመት ታግሎ ኤርትራንም ከኢትዮጵያ ገንጥሎ ሀገር መምራት የቻለው ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ቀናት በኋላ የ72ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ያከብራል፡፡(በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የተጠቀሱት የዘመን አቆጣጠሮች ሁሉም የኢትዮጵያ ናቸው)

ከሳልቫኪር አኳያ እንያቸው
ባለ ባርኔጣው ሰው ደቡብ ሱዳንን ‹‹መምራት›› ከጀመሩ፣ ዘንድሮ ሰባት ዓመት ደፈኑ፡፡በሱዳን ውስጥ ባሕረ ኤል ግሃዛል በተሰኘ ቦታ መሥከረም 2- 1944 የተወለዱት ሳልቫኪር ማያርዲት የ66 ዓመት ባለጸጋ ናቸው (ስንት መቶ ሺህ ሕዝብ በሚያልቅበት አገር 66 ዓመት መኖር እኮ ብርቅ ነው)፡፡

ባለበትሩ አልበሽርስ
ዑመር ሐሰን አልበሽር፣በጥር 1 – 1936 ሲወለዱ ሰባተኛው የሱዳን ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ብሎ የጠበቀ ማን ይኖር ይሆን ?! ሶስት አስርታትን ለሚጠጋ ጊዜ የአገሪቱ መሪ የሆኑት ባለበትሩ አል በሽር የ74 ዓመት ሻማ ያበሩት ባለፈው ማክሰኞ ነበር፡፡

ኢሁሩ ኬኒያታ
ታዋቂው የነጻነት ታጋይ ጆሞ ኬኒያታ ከአራተኛ ሚስታቸው በ1954 ዓ.ም በናይሮቢ የወለዱትን ልጃቸውን ኡሁሩ ሲሉ ስም አወጡለት፡፡በሁለተኛ ዙር ምርጫ በድጋሚ አሸንፈው አገር እየመሩ ያሉት ኡሁሩ ባሳለፍነው ጥቅምት 18 – 56 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡

መሃመድ አቡዱላሂ ፋርማጆ፣
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ከሆኑ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ዓመት ይሆናቸዋል፡፡በአገራቸው መዲና በ1955 ዓ.ም የተወለዱት እርሳቸው፣ ‹ፋርማጆ› የሚል ቅጽል ሥም አላቸው፤አይቡ እንደማለት ነው፡፡ሰውዬው የንግሥና በዓላቸውን ካከበሩ ከሳምንታት በኋላ በመጋቢት ወር 56ኛ ሻማቸውን ይለኩሳሉ፡፡

ዑመር ጊሌህ
የጅቡቲው ሰው፣ድሬዳዋ ነው የተወለዱት፡፡አንዳንዶች ስማቸውን አጠር አድርገው IOG ይሏቸዋል፡፡Ismael Omar Gulleh ከሚለው ረጅም ሥማቸው ላይ የተወሰደ ምኅጻር ነው፡፡ሕዳር 20- 1939 በድሬዳዋ የተወለዱት ጊሌህ ዘንድሮ 71ኛ ዓመታቸውን ደፍነዋል፡፡

ኃይለማርያም ደሳለኝ ቦሼ
ከላይ ከተዘረዘሩት ጎረቤት መሪዎች አንጻር በዕድሜ ትንሹ እኒህ ኢትዮጵያዊ ጠቅላይሚኒስትር ናቸው፡፡በወላይታ ዞን ቦሎሶሶሬ ቀበሌ ውስጥ በሐምሌ 11-1958 የተወለዱት አቶ ኃይለማርያም፣ 52 ዓመታቸው ነው፡፡

ከዚህ አኳያ፣ከኢሳያስ አፈወርቂ በ20 ዓመት፣ ከአልበሽር በ22 ዓመት፣ ከጊሌህ በ19 ዓመት፣ ከሳልቫኪር በ14 ዓመት፣ ከኡሁሩና ፋርማጆ በአራት ዓመት ያንሳሉ፡፡ ለዚያም ነው ‹‹ብላቴናው ኃይለማርያም›› ማለቴ!!

ከአካባቢው ሰዎች አንጻር በእድሜ ያነሱ መሆናቸው ግልጽ ቢሆንም በፖለቲካ ሕይወት ውስጥ ያሳለፉት ጊዜም ያኑ ያህል አነስተኛ ነው፡፡ አብዛኞቹ ጎረቤቶቻቸው ወይ በትጥቅ ትግል ፖለቲካዊ ልምድ ያካበቱ፣ወይም ረዘም ላሉ ዓመታት በምክትል ፕሬዚዳንትና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት እየተማሩ ወደ መሪነት የመጡ፣አለያም በዲፕሎማትነት ተሞክሮ የቀሰሙ፣ያም ካልሆነ በአገሪቱ ጦር ውስጥ ዘለግ ያሉ ጊዜያትን አሳልፈው ፖለቲካን የተለማመዱ ናቸው፡፡

ጎረቤቶቻቸው ይህንን ሁሉ በሚያደርጉበት በዚያ ዘመን አቶ ኃይለማርያም የኢንጅነሪንግ ተማሪና መምኅር ነበሩ፡፡የፖለቲካ ልምድ ማነስ ደግሞ የአገርንና የዓለምን ሁለንተናዊ መንገድ ቃኝቶ ሕዝብን ለመምራት አስቸጋሪ እንደሆነ ፖለቲካል ሳይኮሎጂስቶች ያስጠነቅቃሉ፡፡

ለማንኛውም ግን በዕድሜም ሆነ በፖለቲካ ተሳትፎ፣ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ቦሼ ከምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች አንጻር ብላቴና ናቸው፡፡ DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close