Ethiopia
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ‘የፀረ ሽብር አዋጁ ሰብዐዊ መብቶችን የጣሰ ነው’ ይላሉ

ኢህአዴግ እና አስራ አምስቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጸረሽብር አዋጁ ዙሪያ የሚያደርጉትን ድርድር ቀጥለዋል። በድርድሩ ኢህአዴግ የጸረ ሽብር አዋጁ አለም አቀፍ የትብብር እና የስምምነት ሰነዶችን መሰረት አደርጎ የወጣ ነው ፤ በአፈጻጸሙ ላይ ያሉ ግድፈቶችን ለማረም ግን እሰራለሁ ብሏል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በበኩላቸው አዋጁ ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ነው ሲሉ ተደራድረዋል፡፡
ኢህአዴግ እና ተቋዋሚ ፓርቲዎች በሀገሪቱ የጸረ ሽብር አዋጅ 652/2001 ዙሪያ ለሁለት ጊዜ ያክል ያደረጉት ድርድር ወደ አንድ የጋራ መስማማት ሳያደርሳቸው ተጠናቋል፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይም ደግመው ለመምከር ለሚቀጥለው ሳምንት ሀሙስ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ በሁለተኛው የድርድር መድረካቸው ገዢው መንግስት የጸረ ሽብር አዋጁ የጎላ ችግር የለበትም ፤ ለሀገሪቱ ደህንነት ሲባልም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ባይኖር እንኳን አዋጁ ስራውን መቀጠል ይኖርበታል ሲል ተሟግቷል፡፡ አያይዞም የአዋጁ አተገባበር ላይ መንግስት ስላለበት ክፍተት ካልሆነ በቀር ስለአዋጁ ህልውና መደራደር ፈጽሞ የማይታሰብ ነው ሲል ሀሳቡን በግልጽ አስቀምጧል፡፡
ተደራዳሪዎቹ በፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 ላይ “አሉን” ያሏቸውን አራት የማሻሻያ፣ ስድስት የሚሰረዙና አምስት የሚጨመሩ የአዋጁ የድርድር ሃሳቦች ላይ ማብራርያ አቅርበዋል። በዚህም ኢህአዴግ የሽብር ድርጊት በባህሪው ካለው ውስብስብነት፣ የወንጀሉ አደገኛነት እና ጊዜ የማይሰጥ ከመሆኑ አኳያ ፀረ ሽብር ህጉ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያሟላ፣ ሊሰርዝ እና ሊሻሻል የሚያስችል ህጋዊ መሰረት ያለው ምክንያት እንዳላገኘበት ምላሽ ሰጥቷል።
በዚህም ኢህአዴግ መሰረዝ አለባቸው የተባሉትን አራቱን እና መሻሻል አለባቸው ተብለው የቀረቡትን ስድስት የአዋጁን አንቀፆች በተመለከተ ያልተቀበለበትን ምክንያት አብራርቷል። በአዋጁ ላይ መጨመር አለባቸው በተባሉት አምስት የአዋጁ አንቀጾች ላይ ግንባሩ እንደሚስማማ እና በአብዛኛው ተግባራዊ እየሆኑ ያሉ መሆናቸውንም አብራርቷል። መኢብን ፈንድ የማቋቋሚያ እና ተከሳሾች በማወቅ እና ባለማወቅ የፈፀሙትን ጥፋት የማጣራት ሂደትን በተመለከተ ጥያቄ አቅርቧል። ኢህአዴግ ከፈንድ ጋር በተያያዘ የሚታይ ጉዳይ ካለ እናየዋለን፤ “በማወቅ እና ባለማወቅ ፀረ ሽብር ህጉን ተላልፈው የሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ አዋጁ የሚሻሻልበት አሳማኝ ምክንያት የለም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ፀረ ሽብር አዋጁ “ከአገሪቷ ህገ-መንግስት ጋር ይጣረሳል፣ ህገ-መንግስታዊ መሰረትም የለውም እንዲሁም ራሳቸውን ነፃ ታጋዮች ብለው የሰየሙ ለምን አሸባሪዎች ይባላሉ” የሚል ጥያቄ በኢራፓ በኩልም ቀርቧል። “አዋጁ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የለውም ማለት በፍፁም የተሳሳተ እና በምክንያታዊነት ያልተደገፈ ነው” ሲል ኢህአዴግ ማብራሪያ ሰጥቶበታል።
ማንኛውም ግለሰብ ይሁን ድርጅት የውጭ እና የአገር ውስጥ ዜግነት ይኑረው በሽብርተኝነት ድርጊት ተሳትፎ ከተገኘ በፀረ ሽብር አዋጁ ጉዳዩ እንደሚታይ እና ስያሜም እንደሚያገኝ ገልጸዋል። በመሆኑም ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ ኦጋዴን ነፃ አውጪ ይሁን ሌሎች አሸባሪ የሚለውን ስያሜ በኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ስያሜው የተሰጣቸው ድርጅቶች መሆናቸውን ግንባሩ አስታውቋል። ኢህአዴግ በገዳ ስርዓት አራማጅ በኩል የቀረበውን የማሻሻያ እና የመቀነስ የድርድር ሃሳብም እንደማይቀበል ይፋ አድርጓል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ተደራዳሪ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች መንግስት ቃል በገባው መሰረት በእስር ቤት የሚገኙ የፖቲካ እስረኞችን በአስቸኳይ እንዲለቀ ጥያቄ አቅርበው የነበረ ሲሆን የኢህአዴግ ተወካይም የድርጅታቸውን የቀደመ አቋም በመድገም ኢትዮጲያ ውስጥ የፖለቲካ እስረኛ የሚባል ነገር እንደሌለ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ተወካዩ ማንም ሰው የየትኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ስለሆነ እስር ቤት አልገባም ፤ ለእስር ሚዳርገው በህገመንግስቱ ላይ የተቀመጠውን ህግ ተላልፎ መገኝት ነው ብለዋል፡፡
አክለውም መንግስት በቅርቡ በእስር ላይ የሚገኙ እና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ የፖለቲካ አመራሮችን እፈታለሁ ማለቱ ግለሰቦቹ ወንጀለኞች ሳይሆኑ በፖለቲካ አቋማቸው የታሰሩ ናቸው ማለት እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ ኢህአዴግ ይህን ያደረገውም በሀገሪቱ ያለውን የፖለቲካ ምህዳር ለማስፋት በማለም እንደሆነ ብቻም ሊሰመርበት ይገባል ነው ያሉት፡፡
ፀረ ሽብር አዋጁ መሻሻል፣ መሰረዝና መጨመር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ፓርቲዎች ተጨማሪ ድርድር ለማድረግ ለጥር 3 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዘው ተለያይተዋል።
-
Ethiopia2 days ago
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አዳዲስ ተሿሚዎች ታውቀዋል
-
Entertainment4 days ago
አርቲስት ሰላም ተስፋዬ ተሞሸረች
-
Ethiopia22 hours ago
ለሜቴክ እና ለኢንሳ አዲስ ዋና ዳይሬክተሮች ተሾሙ
-
Ethiopia4 days ago
ከህገ-መንግስቱ የተኳረፉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ!
-
Art and Culture2 days ago
በወርቅ የተሞላው ነገር ግን በሴጣን የተከበበው ተራራ
-
Ethiopia1 day ago
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሶስት ቁልፍ ቦታዎችን ለኦህዴድ መስጠታቸው ጠቃሚ እርምጃ ነው ተባለ
-
Ethiopia24 hours ago
‘የምሞት እየመሰለኝ በጣም ተጨንቄያለው’ ከመሞቱ ሶስት ቀናት በፊት የተናገረው
-
Entertainment22 hours ago
የአርቲስት ታምራት ደስታ የቀብር ሥነሥርዓት ተከናወነ