Connect with us

Ethiopia

ለማ እና ኃይለማርያም፣ተለያዩ?!

Published

on

ለማ እና ኃይለማርያም፣ተለያዩ?!

ለማ እና ኃይለማርያም፣ተለያዩ?! | አስመረት ከአራት ኪሎ

ዘንድሮ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ አጀንዳዎች መካከል ለማ መገርሳ ቀዳሚው ናቸው፡፡ ለማ መገርሳን የፌስቡክ አዝማሪ ሁሉ ‹‹ተቀበል›› ሲልላቸው ነው-የሚውለው፡፡እኒህ ሰው ምን ሰርተው ነው እንዲህ ውዳሴ-ለማ የሚደገምላቸው የሚለውን ጥያቄ ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር በማነጻጸር ‹‹ለማና ገዱ ለሕዝባቸው ምን ፈየዱ›› በሚል ርዕስ ሥር ጽፈነው ነበር፡፡

ዛሬ ደግሞ የነገው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ቀጣዩ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር፣…ወዘተ የሚባልላቸውን አቶ ለማ መገርሳን፣ከአሁኑ አለቃቸውና የዛሬው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አገናኝተን እንጻፍ እስኪ፡፡

በርግጥ ለማና ኃይለማርያም ተለያይተዋል፡፡በሌላ ገጹ ካየነው ደግሞ ለማና ኃይለማርያም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ሁለቱም (መለያየታቸውም አንድ መሆናቸውም) ግን ለአገር አይጠቅምም፡፡እንዴት? ቀጥለን እንመልከተው!!

ለማና ኃይለማርያም ተለያይተዋል ስንል…
በርግጥም ሁለቱም መሪዎች የተለያየ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት፡፡በ17 ቀናት ውስጥ የነበራቸውን ‹‹መቋሰል››(ቃሉ የራሳቸው የአቶ ለማ ነው) በተመለከተ ሁለቱም ሰዎች ምን ዓይነት አቋም እንደነበራቸው ባናውቅም መግለጫ በሚሰጡበትም ወቅት ሆነ ከዚያ በፊት የነበራቸውን ሁኔታ ለተመለከተ ሁለቱ ሰዎች መለያየታቸው ይገባዋል፡፡

ልዩነታቸው በአጭር ዓረፍተ-ነገር ሲገለጽ አቶ ኃይለማርያም፣ የአገሪቱና የድርጅቱ ሁኔታ እንዳለ ቢቀጥል (status quo ማስቀጠል) ያሰራናል ከሚሉት ወገን ናቸው፡፡አቶ ለማ በአንጻሩ ኢሕአዴግም ሆነ አገሪቱ የምትሄድበት መንገድ ሊሻሻል ይገባዋል (reformations) ባይ ናቸው፡፡

ልዩነታቸው እዚህ ጋር ነው፡፡አቶ ኃይለማርያም አገሪቱን ከብተና ጫፍ፣ ድርጅቱን ከመፍረስ አፋፍ ያደረሰውን የትናንት መንገድ አትራፊ ነው ብለው ግግም ማለታቸው ሲሆን አቶ ለማ ደግሞ እንደ ፖለቲከኛ ሳይሆን እንደ አክቲቪት የሕዝብን የስሜት አቅጣጫ የያዙ ቋንቋዎችን እየተከተሉ ማሻሻያን (reformation) መናፈቃቸው ነው-የልዩነታቸው ሥረ-መሠረት፡፡

የኃይለማርያም ‹‹ዛሬም እንደ ትናንቱ ፤ ነገም እንደዛሬው›› መንገድ
በርግጥ በአንድ አገርም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት እንኳን በ25 እና 26 ዓመት ቀርቶ በየዓመቱ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አቶ ኃይለማርያም ደጋግመው ከተመላለሱባት ቻይና መማር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳት ሺ የሚመሩት የኤክስፐርቶችና የፖለቲከኞች ኮሚቴ በየዓመቱ ያለውን ዓለማቀፍ ፖለቲካል ኢኮኖሚ አሰላለፍ (Global Political-Economy order) እያጠና ቢያንስ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ይነድፋል፡፡

የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሁኔታዎች ያሉበትን ዙሪያ-ገባ፣ሕዝብ የደረሰበትን ንቃተ ሕሊና፣ፖሊሲዎች ከሕዝብ ፍላጎትና ከዓለማቀፍ ሁኔታዎች ጋር አዛምዶ ፖለቲካዊም ሆነ ኢኖሚያዊ ማሻሻያ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡የኢሕአዴግ ትምኅርት ቤት የሆነችው ቻይና ይህንን ነው የምታደርገው፡፡ፕሬዚዳንቱ ሺ የሚመሩት ኮሚቴም ሥራው ይህ ነው፡፡

‹‹ስታተስ ኮው›› አስቀጥላለሁ ብለው በአቶ መለስ ዜናዊ ስም ሲምሉ የሚውሉት አቶ ኃይለማርያምም መማር ያልቻሉት ይህንን ነው፡፡የዓይን ጭራ ከሚርገበገብበት ፍጥነት በባሰ መንገድ የዓለም ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ሲቀያየር አቶ ኃይለማርያም ግን የትናንቱ ልክ ነው፤እስከነገም ያሰራናል ማለታቸው ብዙ ርቀት አያስኬድም፡፡እንደ አቶ ለማ ካለው ኢሕአዴግ ጋርም ሊያጋጫቸው ይችላል፡፡

የለማ ቃላት
እንግዲህ ለማን ከኃይለማርያም የሚለያቸው፣ ማሻሻያ ያስፈልጋል የሚል አዝማሚያ ማሳየታቸው እንደሆነ ከላይ ተገልጹዋል፡፡ማሻሻያ ማድረግ ያለው አስፈላጊነትም ተብራርቷል፡፡ግራ የሚያጋባው ነገር ግን አቶ ለማ ይዘውት የመጡት መንገድ ነው፡፡በአንድ በኩል ራሱን ኢሕአዴግን ከውስጥ ሆነን ለማሻሻያ እናስገድደዋለን የሚል ይመስላል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በለውጥ አራማጅነት እንቅስቃሴ የማሰባስውን ሕዝብ ይዤ ከኢሕአዴግ እገነጠላለሁ የሚል አዝማሚያም አለው፡፡ቢያቃጥለኝ በማንኪያ ባያቃጥለኝ በእጄ እንደማለት ያለ ነው፡፡

ሁለተኛው ላይ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም አይሆንም ተብሎ የሚጠበቅ ግን አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ቤት ውለው ኢሕአዴግን ለማሻሻል መፈለጋቸውን የሚያሳዩ ምልክቶች ግን ታይተዋል፡፡ከኢሕአዴግ ባሕርይ በተለየ ሁኔታ መግለጫዎችን መሥጠትና ከግንባሩ ተፈጥሮ ጋር የማይገናኙ ቃላትን መጠቀማቸው፣ ከኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ባፈነገጠ ሁኔታ የመንግሥትን ውሳኔዎች ማውገዛቸው (መከላከያን ማውገዛቸውን ልብ ይሏል)፣ከተለመደው የኢሕአዴግ ማዕከላዊነት በተቃራኒ ለፌደራል መንግሥቱ ያለመታዘዝ ወዘተ አቶ ለማን ኢሕአዴግን ለመለወጥ ኢሕአዴግ መሆን ያስፈልጋል የሚያስብላቸው ነው፡፡

ግን ሰውዬው ለውጥ ፈላጊነታቸውን የሚያንጸባርቁበት መንገድ ብሥለት ያለው ፖለቲከኛ የሚያደርገው አይደለም፡፡ለውጥ ፈላጊነታቸው የሚበረታታ ሆኖ ግን ሕዝብ ምን ይፈልጋል በሚል የሚደረግ መሆኑ አይጥምም፡፡ፖለቲከኛ፣ሕዝብ ምን ያስፈልገዋል የሚል ስትራቴጂስት እንጂ ሕዝቡ ምን ይፈልጋል የሚል ስሜታም መሆን የለበትም፡፡ሕዝቡ ምን ይፈልጋል የሚል ፖለቲከኛ፣ እንግሊዘኛው ፖፑሊስት አማርኛው ሕዝበኛ እንደሚለው ያለ ነው፡፡ሕዝብ ወቅታዊ ጥቅሞችንና ስሜቶችን ተከትሎ የሚፈስ ጎርፍ እንጂ ስትራቴጂካዊ ፍላጎቶችን የሚያቅድ ስብስብ አይደለም፡፡አቶ ለማ ይህንን ነው-መለየት ያቃታቸው፡፡

ለውጥ ለምን? ለውጥ እንዴት? ለውጥ መቼ? የትኛውን አማራጭስ መከተል ያዋጣል ?ወዘተ የሚሉትን ተንትኖ ማቅረብ ይገባል፡፡ግን በአዳራሹ ውስጥ የተሰባሰበውን ሕዝብ ሥሜት እያዩ በማስጨብጨብ ፍላጎትን መገምገም ለመንግሥቱ ኃይለማርያምና ለአዶልፍ ሒትለርም አልበጀም፡፡አቶ ለማ የለውጥ አምጪነት መንፈስና እቅድ ካላቸው ይህንን ሥሜት መላቀቅ አለባቸው፡፡ሥሜትና ለውጥ ፈላጊነት አብረው አይሄዱም፡፡

ለማና ኃይለማርያም አንድ ናቸው ስንል…
ሁለቱ ሰዎች ከላይ በተዘረዘረው አኳኋን የተለያዩ ቢሆኑም አንድነታቸው ግን አልጠፋም፡፡አንድ የሚያደርጋቸው ሁለቱም ኢሕአዴግ መሆናቸው ነው፡፡የለማ አድናቂዎች መለየት የሚያቅታቸው ይህንን ነው፤አቶ ለማ መገርሳ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራርና የኦሕዴድ ሊቀመንበር መሆናቸውን፡፡

ኢሕአዴግን ካቆሙ ሰዎች ውስጥ አቶ ለማ መገርሳ ከግንባር ቀደሞቹ ውስጥ ናቸው፡፡ዛሬም አለቃቸው አቶ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ ዛሬም አቶ ለማ ለአቶ ኃይለማርያም የመታዘዝ ኢሕአዴጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡

ለዚያም ነው አቶ ኢሕአዴግን እየጠሉ አቶ ለማን መውደድ ይቻላል ወይ ስንል የምንጠይቀው፡፡ወደድንም ጠላንም ለማ መገርሳ ኢሕአዴግ ናቸው፤ለዚያውም የኢሕአዴግ ቁንጮ!! DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close