Connect with us

Ethiopia

ታሪካዊውን ቤት ያፈረሰው አካል በሕግ እንዲጠየቅ ክስ ተመሰረተ

Published

on

ታሪካዊውን ቤት ያፈረሰው አካል በሕግ እንዲጠየቅ ክስ ተመሰረተ

ታሪካዊውን ቤት ያፈረሰው አካል በሕግ እንዲጠየቅ ክስ ተመሰረተ | አንተነህ ቸሬ

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት የሚገኘውንና በቅርስነት የተመዘገበውን የስመጥሩ አርበኛ የራስ አበበ አረጋይን የቀድሞ መኖሪያ ቤት እንዲፈርስ ያደረገው አካል በሕግ እንዲጠየቅ ለማድረግ ክስ መመስረቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው የሕግ አማካሪ አቶ አበበ ሳህሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ቢሮው በቅርሱ ላይ የተፈፀመውን ሕገ-ወጥ ተግባር ከግምት ውስጥ በማስገባት መረጃዎችን አጠናቅሮ ለየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ልኳል፡፡ ቢሮውም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው ይገኛል፡፡

እንደርሳቸው ገለፃ፣ ቤቱን ያፈረሰው ሙለር ሪል ስቴት ቤቱን ማፍረስ በጀመረበት በሐምሌ 2009 ዓ.ም የከተማ አስተዳደሩ እና የየካ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ባለሙያዎች ስፍራው ድረስ በመሄድ የቤት ፈረሳውን አስቁመውት ነበር፡፡ ድርጅቱም ቤቱን አፍርሶ ዘመናዊ ሕንፃ እንዲገነባ ለከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጥያቄ አቅርቦ ቢሮው ቤቱ በቅርስነት የተመዘገበ ቤት መሆኑን የቅርስ አጠባበቅ አዋጅ 209/1992ን ጠቅሶ በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

አቶ አበበ እንደሚሉት፣ ቤቱን የማፍረስ ስራው እንዲቆም ከተደረገ በኋላ በቀጣይ ሊደረግ ስለሚገባው ስራ ቢሮው እየመከረ ሳለ፣ ድርጅቱ በመስከረም 2010 ዓ.ም በድጋሚ ቤቱን እያፈረሰ ስለመሆኑ በተገኘ ጥቆማ መሰረት እርሳቸውን ጨምሮ ከክፍለ ከተማውና ከወረዳው የተውጣጡ ባለሙያዎች ወደስፍራው ሲደርሱ ቀድሞ ከፈረሰው በተጨማሪ የቤቱ በሮች፣ መስኮቶችንና ጣሪያው አካል በሙሉ ፈርሰው ተመልክተዋል፡፡ ወደ ውስጥ በመግባት ማፍረሱን ለማስቆም ያደረጉት ሙከራም በድርጅቱ የጥበቃ ሰራተኞች ምክንያት ሰይሳካ ቀርቷል፡፡

ከክፍለ ከተማውና ከወረዳው የስራ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ድርጅቱ ቤቱን የማፍረስ ስራውን የሚቀጥል ከሆነ የወረዳው የፀጥታ ኃይሎች ስራውን የሚያከናውኑትን አካላት በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ በመወያየት የባህልና ቱሪዝም ቢሮው ክስ መመስረቱን ገልፀዋል፡፡ የየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያም ከባህልና ቱሪዝም ቢሮው መረጃ ጠይቆ ቢሮውም መረጃዎችን አጠናቅሮ መላኩንም ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በዚህም ቤቱ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብና መንግሥት ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለት ለአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ጽሕፈት ቤት የተፃፈውን ደብዳቤ ጨምሮ፣ ቤቱ በቅርስነት ስለመመዝገቡ የሚያስረዳውንና ሙለር ሪል ስቴት ቤቱን እንዳያፈርስ ቢሮው ምላሽ የተሰጠበትን ደብዳቤዎችንና ሌሎች ተያያዥ መረጃዎች ለክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ መላካቸውንም አመልክተዋል፡፡

‹‹መንግሥት እንክብካቤና ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ከቢሮውና ከቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በተውጣጡ ባለሙያዎች አማካኝነት ተለይተው የተመዘገቡ 440 ቅርሶች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ይገኛሉ፤ ይህ የራስ አበበ አረጋይ የቀድሞ መኖሪያ ቤትም ከነዚህ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፤ የቅርሶቹን ዝርዝር በሚያዚያ 2008 ዓ.ም ለሁሉም ክፍለ ከተሞች ልከናል›› ያሉት አቶ አበበ፣ ቤቱ በቅርስነት የተመዘገበ መሆኑ እየታወቀ እንዲፈርስ መደረጉ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነና ተገቢና አስተማሪ የሆነ እርምጃ እንዲወሰድ ቢሮው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

75 በመቶ የሚሆነው የቤቱ አካል ሙሉ በሙሉ መፍረሱን የጠቆሙት አቶ አበበ፣ ‹‹ድርጊቱ በቅርስ ላይ የተፈፀመ ከባድ ወንጀል በመሆኑ ፖሊስ ምርመራውን አጣርቶ አጥፊውን ለፍርድ ያቀርባል ብለን እናምናለን›› ብለዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በቀጣይ መደረግ ስላለበት እርምጃ እየተነጋገሩ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ራስ አበበ አረጋይ በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በአርበኝነት ተጋድሏቸው ስመ-ጥር ከነበሩት አርበኞች መካከል አንዱ ሲሆኑ የፋሺስት ጦር ተባርሮ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በዙፋናቸው ከተቀመጡ በኋላ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነቶች ያገለገሉና በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎች የተገደሉ ሰው ናቸው፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close