Connect with us

Ethiopia

የ36 ሰዎች አገር፤ ኢትዮጵያ

Published

on

የ36 ሰዎች አገር፤ ኢትዮጵያ

የ36 ሰዎች አገር፤ ኢትዮጵያ
(መላዕክነሽ ሽመልስ በድሬቲዩብ)

እዚህ አገር ላይ፣እዚህ ኢትዮጵያ በተሰኘ ምድር ላይ፣እዚህ መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርበት የዓለም ክፍል ውስጥ፣ ከሁሉም የላቁ 36 ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ 36 ሰዎች በሚሊዮኖች ላይ ስልጣን ያላቸው፣በጦሩም በደኅንነቱም፣በኢኮኖሚውም በፖለቲካውም ጉዳይ የሚወስኑ ናቸው፡፡

ሰዎቹ ከሚኒስትሮች ምክርቤትም፣ከሕዝብ ተወካዮች ምክርቤትም፣ከፌደሬሽን ምክር ቤትም፣ከኢሕአዴግ ምክርቤትም ይበልጣሉ፡፡እነዚህ 36 ሰዎች በስም የሚታወቁ፣ እከሌ እከሌ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡የነዚህ ሰዎች ውሳኔ ነው-የአገሪቱን ሁለ-ነገር የሚወስነው፡፡

ፈታ አድርገን እንመልከተው፤
የኢሕአዴግ ኮሙዩኒስታዊ ዓመል መገለጫው እዚህ ጋር ይጀምራል፡፡ አወቃቀሩ ኮሙዩኒስታዊ ነው፡፡ ግንባሩ፣በአራት ድርጅቶች የተመሰረተ ነው፡፡ ዲኢሕዴን፣ኦሕዴድ፣ብአዴንና ሕወሓት የዚህ ግንባር ምሰሶዎች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ብሔራዊ (ክልላዊ) ድርጅት፣ ጠቅላላ ጉባዔ (General Assembly) ፣ማዕከላዊ ኮሚቴ (Central Committee) ፣ ሥራ-አስፈጻሚ ኮሚቴ (Poliute Bureau ) በተባሉ አደረጃጀቶች የተዋቀረ ነው፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው 45 ሰዎችን ማዕከላዊ ኮሚቴ አድርጎ ይመርጣል፡፡ ከእነዚህ 45 አባላት ዘጠኝ ሰዎች ይመረጣሉ፡፡ዘጠኙ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው፡፡ሥራ አስፋጻሚ አባላት ይባላሉ፡፡ አራቱም ድርጅቶች (ደኢሕዴን፣ኦሕዴድ፣ብአዴንና ሕወሓት) ዘጠኝ ዘጠኝ የሥራ አስፈጻሚ አባላት አሏቸው፡፡በድምሩ 36 ማለት ነው፡፡

እነዚህ የጋራ ሊቀመንበር አላቸው፡፡ሊቀመንበሩ የአገሪቱ ጠቅላይሚኒስትር የሚሆንበት እድል አያጠራጥርም፡፡ይህ ነው እንግዲህ አገሪቱን ‹የ36 ሰዎች ናት› የሚያስብላት፡፡እነዚህ ሰዎች ተሰባስበው ውሳኔ ያሳልፋሉ፡፡ውሳኔያቸውን አለመቀበልም ሆነ ለመተግበር ማዘግየት ያስወነጅላል፡፡
እነዚህ ሰዎች የሚያመጡት የውሳኔ ሀሳብ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች፣ በሁሉም ቦታዎች ፣ በሁሉም ተቋማት፣… ገቢራዊ ይሆናል፡፡ ሚኒስትርም ሆነ የክልል ቢሮ ኃላፊ ይህንን

አልቀበልም ማለት አይችልም፡፡ ሰማዩም ምድሩም 36 ሰዎች በአንድ አዳራሽ ውስጥ ሆነው ላሳለፉት ውሳኔ ይገዛል፡፡ለዚያም ነው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለጉባኤ ተቀመጠ ሲባል ውሳኔው በጉጉት ሲጠበቅ የሚከርመው፡፡

36ቱ ሰዎች የሚወስኑት ውሳኔ መቀሌም ላይ ሞያሌም ላይ ገቢራዊ ነው፡፡ 36ቱ ሰዎች ያሉትን ነገር መንዜም ዶርዜም መቀበል አለበት፡፡ሰሞኑን ቁጭ ብለው እየተወያዩ ያሉትም እነዚህ ሰዎች ናቸው(በርግጥ የቀድሞ ሥራ-አስፈፃሚ አባላትና ታጋዮች በግብዣ እየተሳተፉ ነው)፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትርም ከ36ቱ ውስጥ ብቻ?
አሸማቃቂው ነገር እዚህ ጋር ነው፡፡በኢሕአዴግ የግንባርነት ዘመን ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚኖራት ወይ ከደቡብ ክልል አለያም ከኦሮሚያና አማራ ወይ ደግሞ ከትግራይ ብቻ ነው፡፡ ስትፈርጥ ብትውል ሱማሌ ጠቅላይ ሚኒስትር አይኖራትም፤ የአፋር ሰው ፕሬዚዳንት አይሆንም፤ ወይም ከጋምቤላና ጉሙዝ የመጣ ሰው አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ገብቶ መሪ አይሆንም፡፡ይህ በሕግና በአሰራር የተደነገገ ነው፡፡

አስገራሚው ነገር በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ከአራቱ ክልሎች ውጭ የሆኑት መስተዳድሮች (አፋር፣ሱማሌ፣ሐረሪ፣ጋምቤላ፣ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣አዲስ አበባና ድሬዳዋ) ምንም ዓይነት ሕጋዊ ውክልና የላቸውም፡፡ ሕጋዊ በሆነ ሁናቴ ባልተሳተፉበት፣ሐሳብ ባልሰጡበት፣ባልደገፉትና ባልተቃወሙት ውሳኔ የመገዛት ግዴታ አለባቸው፡፡ በሌላ አገላለጽ ከ36ቱ ሰዎች ውስጥ ታዳጊ የሚባሉትን ክልሎችና ሁለቱን ከተማ መስተዳድሮች የሚወክል ተሳታፊ የለም፡፡ይሁን እንጂ 36ቱ ሰዎች ያሉትን ነገር ይፈጸማሉ፡፡የአጋር ፓርቲነት ሥራ ይህ ነው፡፡ያልተሳተፉበት ጉባዔ ያሳለፈውን ውሳኔ መቀበል፤ያልተወከሉበት ስብስብ ያለውን ተቀብሎ ማስተጋባት!!

የነገው አደጋ…!
በአሁኑ ሰዓት ይነስም ይብዛም ሰላም ያለው በነዚህ ታዳጊ በሚባሉትና በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ ሕጋዊ ውክልና በሌላቸው ክልሎችና ከተሞች ነው፡፡ ኢሕአዴግ በተዋቀረባቸው ክልሎች በአንጻሩ ሰላም ከደፈረሰ ዘንድሮ አራተኛ ዓመቱን አስቆጥሯል፡፡አስገራሚው ነገር በነዚህ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከነበሩት ጥያቄዎች ግዝፍ ነስቶ የነበረው በፌደራል ያለን ውክልና አነስተኛ ነው-የሚል መሆኑን ነው፡፡ የምጣዱ እያለ የሰፌዱ ተንጣጣ ማለት ይህ ነው፡፡

ሱማሌም ሆነ አፋር፣ጋምቤላም ሆነ ጉሙዝ፣ድሬም ሆነ አደሬ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሆን በሕግና በአሰራር ተደንግጎ ፣ ከነዚህ ክልሎችና መስተዳድሮች የሚመጣ ሰውም ለመሪነት አትታጭም ተብሎ ጎንደርና ወለጋ ፌደራላዊ ውክልናዬ አንሷል ብሎ ተቃውሞ ያሰማል፡፡ ሱማሌና አፋር ይህንን ሲሰማ ምን እንደሚል ፈጣሪ ይወቅ!!

የሆነው ሆኖ ነገ ለአገር አንድነት አደጋ ሊሆን የሚችል ነገር የሚያቆጠቁጠው ከነዚህ ክልሎች መሆኑን ለመገመት ነብይ መሆን አይጠይቅም፡፡ እነዚህን ክልሎች ከፌደራሉ ፖለቲካ የሚያገል አሰራር ተተግብሯል፡፡አሰራሩ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ያሉበት ከመሆኑ በዘለለ ሁለት ዓይነት ጥያቄዎችን ይወልዳል፡፡በአንድ በኩል በፌደራሉ ላይ መወሰን አትችሉም፤ጠቅላይ ሚኒስትርም አትሆኑም ከተባልን ኢትዮጵያ ትቅርብን ሊሉ ይችላሉ፡፡በሌላ በኩል፣‹‹ሕጋዊ ውክልና የለንም››፣ ‹‹በ36 ሰዎች ውሳኔ አንመራም፤ እኛም እንወከል›› ብለው በሚያነሱት ጥያቄ መሰረት አሁን በኢሕአዴግ ክልሎች ላይ እንደምናየው ያለ ግጭት ሊቀሰቅስ ይችላል፡፡

መፍትሔ፤
ይህንን አሰራር ለማስተካከል የመፍትሔ ቁልፉ ያለው በኢሕአዴግ ኪስ ውስጥ ነው፡፡ለዚህ የሚሆኑ ሁለት አማራጮችም አሉት፡፡አንደኛውና ለሌሎች ችግሮቹም ማቃለያ የሚሆነው ሁነኛ መድሐኒት ውሕደት ነው፡፡ራሱን ከግንባርነት አውጥቶ ወደ ፓርቲነት ማምጣትና ከጥምረት ወደ ውሕደት ማሳደግ፣ ከመፍትሔዎች ሁሉ የሚቀድም ነው፡፡ይህንን ሲያደርግም ‹‹ታዳጊ ክልሎች፣አጋር ፓርቲዎች…›› ወዘተ እያለ የሚጠራቸውንና የሚያገልላቸውን መስተዳድሮች የውሕደቱ አካል ማድረግ ይገባዋል፡፡

ሁለተኛው መፍትሔ፣ ኢሕአዴግ አሁን ባለው መዋቅሩ እነዚህን ክልሎች አካታች የሚያደርግ አሰራር መዘርጋት ነው፡፡በሌላ አገላለጽ፣ በራሱ በግንባሩ ውስጥም ቢሆን አባል እንዲሆኑ ማድረግ ይገባል፡፡ይህ ካልሆነ ለአገር አንድነትም ሆነ ሰላም አደጋ የሆነ ነገር ሊከሰት ይችላል፡፡

እኛም እንዲህ እንላለን ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ የ36 ሰዎች አገዛዝ ይብቃሽ!!›› DireTube

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close